የሜቴክ ሰራተኞች አራት መኪኖች አቃጠሉ

Views: 1261

የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቢሾፍቱ ባስ መገጣጠሚያ ሠራተኞች የተገባልን የደሞዝ ጭማሪ ይፈፀምልን በሚል ምክንያት ከሦስት ሳምንት በፊት አራት አውቶቡሶችን አቃጠሉ።

ከ 10 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ያሉት ድርጅቱ በተደጋጋሚ የደሞዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ለሠራተኞቹ ቃል ቢገባም መፈፀም አልቻለም። በዚህ ምክንያት ተጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው ፋብሪካው የተነሳ በተቃውሞ ግርግር መካከል ነው፣ መኪኖቹ በእሳት የተያያዙት።

ተገጣጥመው ሊሸጡ የተዘጋጁትን አራት አውቶቡሶች በሚቃጠሉበት ወቅት እሳቱን ለማጥፋት ሠራተኛው መረባረቡን፤ ነገር ግን መኪኖቹ ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን የዐይን እማኞች ገልጸዋል። የሜቴክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መሐመድ እድሪስ ለአዲስ ማለዳ የድርጊቱን መፈጸም አረጋግጠው እስከ አሁን ግን በጉዳዩ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው የለም ብለዋል።

‹‹ይሄንን ድርጊት በተቋሙ ላይ አሉታዊ አመለካከት እንዲፈጠር የሚፈልጉ አካላት የፈጸሙት እንጂ የድርጅቱ ሠራተኞች ያደረጉት ነው ብለን አናምንም›› ሲሉም ተናግረዋል። ‹‹ነገር ግን ማንም ያድርገው ማን፣ ድርጊቱ ለድርጅታችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው›› ብለዋል። አውቶቡሶቹ ላይ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ሲተመንም 3.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነም ተናግረዋል።

ሜቴክ 73 ቢሊዮን ብር እዳ እንዳለበት የገለጹት ኃላፊው፣ በድርጅቱ ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ለችግሩ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ለባሰ ችግር እንደሚዳርገው እና የተፈፀመውም ድርጊት ወንጀል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ድርጅቱ አቅም አንሶታል በሚልም ሠራተኞች ዝቅተኛ ደሞዝ እንዳላቸው በመታመኑ፣ ደሞዝ ለመጨመር መታሰቡ ለሠራተኞቹ ተነግሮ ነበር። እንደ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልጻ፣ በእዳ ውስጥ ያለ ተቋም ሲያዝ የመጀመርያ ሥራ የሚሆነው ያለውን እዳ መቀነስ እንጂ ተጨማሪ እዳ ማምጣት መሆን የለበትም።

ኃላፊው አክለው እንዳሉት፣ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ማስተዳደር ከሚችለው ውጪ በጣም ብዙ ተልዕኮዎችን ያቀፈ ሆኖ በመቆየቱ፣ ለሠራተኞቹ ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቷል። ድርጅቱ እንደ አዲስ ሲዋቀር ዋነኛ ሥራው ያደረገው የሠራተኛውን ድልድል በእውቀት ደረጃው በመመዘን የመዋቅር ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደነበረም ተናግረዋል። አምራች ያልሆነ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሠራተኛን ይዞ መቆየት ያለፈው አመራር ድክመት ነበርም ብለዋል።

በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘውን የአውቶሞቲቭ መገጣጠሚያ ጨምሮ ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎችን ያጠቃለለው ሜቴክ፣ የደሞዝ ጉዳይን በተመለከተ ሌላ ተቋም እንደሚፈፅም ተናግረዋል።
ኃላፊው ጨምረውም ይሄ ችግር ከኹለት ወር በላይ ይቀጥላል ብለው እንደማያስቡ አንስተው፤ በአጭር ጊዜ ወደ መፍትሄው ለመድረስ ኮሚቴ ተመሥርቶና እና አዲስ አደረጃጀት ተዋቅሮ መጠናቀቁን ገልፀዋል። አያይዘውም እንደ አዲስ የሠራተኞቹ ምደባ ተደርጎ፣ አዲስ የደሞዝ እርከን ወጥቶለት እየተስተካከለ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ይሄ ካልሆነ ተቋሙ ካሉት ኢንዱስሪዎች ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ መምጣቱ የሚያጠራጥር ነው ሲሉ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com