የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ትዕዛዝ ተሰጠ

0
978

ምዝገባው በዘርፉ ያለውን ሀብት ለማወቅ ይረዳል ተብሏል

በኢትዮጵያ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅትነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ያላቸውን ሀብት እንዲያስመዘግቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ትዕዛዝ ሰጠ።
በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዐዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት የተመዘገቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባዘጋጀው ቅጽ መሠረት ሀብታቸውን መዝግበው ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እንዲያሳውቁ ባለሥልጣኑ አሳስቧል።

ሀብታቸውን ለባለሥልጣኑ የሚያስመዘግቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ታኅሳስ 30/2013 እንዲያሳውቁ ጊዜ የተሰጣቸው ሲሆን፣ የሀብት ምዝገባ ዓላማው የመረጃ አያያዝን በማዘመን፣ የክትትልና ድጋፍ ሥራ ለማቀላጠፍ መሆኑን የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላልኝ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ሀብታቸውን የማስመዝገብ ግዴታ ያለባቸው በባለሥልጣኑ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ኹሉም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚያስተዳድሯቸውን ንብረቶች ለታለመላቸው ዓላማ መዋላቸውን ለመከታተልና ድጋፍ ለማድረግ የተደራጀ የሀብት ምዝገባ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።

ባለሥልጣኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ሀብት የመረጃ አያያዝ በማዘመን ንብረቶቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ የክትትልና ድጋፍ ሥራ እንደሚሠራ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያላቸውን ሀብት በዕምነት ማስመዝገብ እንዳለባቸው የጠቆሙት ፋሲካው፣ ያላቸውን ሀብት የማያስመዘግቡ ድጅርቶች ካሉ ባለሥልጣኑ ከዚህ በፊት ከቀረቡለት ሪፖርቶች እና በመስክ (ፊልድ) ምርመራ እንደሚያረጋግጥ ጠቁመዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሕዝብ የሚሠሩ የሕዝብ ሀብት መሆናቸውን የሚገልጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዐዋጅ ቁጥር 1113/2011 ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በዐዋጁ መሠረት ያላቸውን ሀብት የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው ብለዋል። ያለውን ሀብት የሚደብቅ ወይም የማያስመዘግብ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ካለ ማኅበረሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በየዓመቱ ‹ፋይናንሽያል› ሪፖርትና ያላቸውን ሀብት ለባለሥልጣኑ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የአሁኑ የሀብት ምዝገባ አሠራርን ለማዘመን መሆኑን ተመላክቷል። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን የተሠጠው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በሕዝብ ንብረት የሚሰበሰብ ሀብት ለሕዝብ ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥ እና በዘረፉ እንደ አገር ምን ያክል ሀብት እንዳለ ጥቅል መረጃ ባለመኖሩ መረጃ ለማሰባሰብና ለማጠናቀር የደርጅቶች ሀብት ምዝገባ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጿል።

ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከሚያስመዘግቧቸው ሀብቶች መካከል አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለ ተሸከርካሪ፣ አገልግሎት የማይሰጥ ተሸከርካሪ፣ የተሸጠ ተሸከርካሪ፣ ከሌላ ድርጅት የተላለፈ ተሸከርካሪ፣ ቋሚ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ እንዲሁም የደርጅቶች ቋሚ ንብረት የሆነ እንደ ሆስፒታል፣ ክሊኒክ፣ ትምህርት ቤት፣ ቢሮና ጋራጅ የመሳሰሉት ይገኙበታል።

በኢትዮጵያ ከሦስት ሺሕ 500 በላይ አገር አቀፍ እና የውጭ አገር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተመዝግበው በሥራ ላይ ይገኛሉ። የሲቪል ማኅበረስብ ድርቶች በጤና፣ በትምህርት፣ እና በሌሎችም በተለያዩ ዘርፎች ለማኅበረብ ጥቅም የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here