በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ሕይወታቸው ካጡባቸውና በርካታ የአገር መሠረተ ልማቶች ከወደሙባቸው፣ እንዲሁም ከተፈናቀሉባቸውና ለችግር ከተጋለጡባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ነች።
በቅርቡ የህወሓት ታጣቂ ኃይሎች ከፈፀሙባት ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ በተጨማሪ፤ በተደጋጋሚ በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሱ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በሚያደርሱባት ጥቃት በዜጎች ሞት፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት እና ዝርፊያ ጭምር እጅጉን ስትታመስ የቆየች የአገራችን ከተማ ነች-አጣዬ!
ከተማዋ በቅርቡ በህወሓት ታጣቂዎች ከተፈፀመባት ወረራ ማግሥት፣ አሁን ያለችበት ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝንና ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ የሚያስፈልግ መሆኑን ወደከተማዋ አቅንታ የነበረችው አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።
ከሰሞኑ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራና አፋር ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና የአማራ ሚሊሺያዎች ባደረጉት የተቀናጀ የጥቃት ዕርምጃ በአማራና በአፋር ክልል የሚገኙና በወረራ ተይዘው የነበሩ በርካታ ከተሞችን ሙሉ ለሙሉ ነጻ በማውጣት፣ ወደ ትግራይ በመገስገስ ላይ እንደሚገኙ ይነገራል።
በጥምር ኃይሉ የተቀናጀ ዕርምጃ ነጻ ከወጡ ከእነዚህ ከተሞች መካከልም፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ሥር የምትገኘውና የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ዋና መቀመጫ የሆነችው የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ትገኝበታለች።
መቼም የአጣዬ ከተማን ቀደምት ውበትና ድምቀት፣ የነዋሪዎቿን መልካም መስተንግዶና ፍቅር በቅርብ የሚያውቅ ሰው፣ የከተማዋን አሁናዊ ሁኔታ ሲያይ ከልቡ ማዘኑ፣ የጦርነትን አስከፊነትን፣ የጥፋት ኃይሎቹን ርህራሄ ቢስነትና ክፉትን በደንብ መገንዘቡ የማይቀር ነው። ምክንያቱም አጣዬ ከተማ ለመናገር በሚያዳግትና በሚከብድ መልኩ በጦርነቱ ምክንያት እጅጉን ተጎድታለችና ነው።
በአራት ዓመት ውስጥ ለሰባት ጊዜያት ያህል በጦርነትና ሽብር ስትታመስ የከረመችው ይህች ከተማ፣ በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ መሠረተ ልማቶቿ የወደሙባት፣ ነዋሪዎቿ የህወሓትና ሸኔን ኃይሎችን ጥቃት በመፍራት እስካሁን ድረስ በሥጋት የሚኖሩባት፣ ቀን ቀን ከተማ ውስጥ እየዋሉ ማታ ማታ ጫካ የሚያድሩባት ከተማ ሆናለች።
ለተፈናቃዮች እና በጦርነቱ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ላጡ ዜጎች ተብሎ ከተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፍ አድራጊ ግለሰቦችና ተቋማት የሚመጣው ዕርዳታም፣ በተለያዩ የመንግሥት አመራሮች፣ የድጋፉ አስተባባሪዎችና ሌሎች አካለት እየተመዘበረ ዕርዳታው በአግባቡ ለማኅበረሰቡ የማይደርስባት ከተማ እየሆነች መምጣቷንም የከተማዋ ነዎሪዎች በከፍተኛ ምሬት ይናገራሉ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት የህወሓትና የኦነግ ሸኔ ኃይሎች በጥምረት ያወደሟት ይህች ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦቿንም በታጣቂዎቹ ርህራሄ አልባ ጥቃት ምክንያት አጥታለች።
አዲስ ማለዳ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውራ በተመለከተችባቸው አጋጣሚዎች ኹሉ፣ በከተማዋ የሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ፣ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ በታጣቂ ኃይሎቹ ጥቃት መውደማቸውን ታዝባለች።
የአጣዬ መሰናዶና ኹለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ አጣዬ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ፣ የኤፌሶን ቅርንጫፍ ንግድ ባንክ፣ ወጋገን ፣ ቡና፣ ዳሽን፣ አቢሲኒያ እና ሌሎት ባንኮች እንዲሁም ሆቴሎች፣ ወርቅ ቤቶችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፤ ተዘርፈዋልም።
ከተማዋ በጥምር ኃይሉ ነጻ ከመውጣቷ አስቀድሞ፣ በአየርም ሆነ በምድር በተደረገው ውጊያ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ የህወሓት ታጣቂዎችም ሆነ የከተማው ነዋሪዎች ሬሳ በየመንገዱ ዳር በጅምላ መቀበሩንም አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።
በአንዳንድ አካባቢዎችም እስከ አሁን ድረስ ሬሳቸው ያልተነሳ የህወሓት ታጣቂ ቡድን አባላት በመኖራቸው፣ ከተማዋ የሙታን መንደር መስላ ያ የሚታወቀው መልካሙ ጠረኗ ክፉኛ ተቀይሯል።
በተጨማሪም አዲስ ማለዳ የህወሓት ኃይሎች በከተማዋ በቁዩባቻ ቀናት ውስጥ ለማረፊያና ለሕክምና አገልግሎት መስጫነት ይጠቀሙባቸው በነበሩ አንዳንድ ሕንፃዎችና መኖሪያ ቤቶች ውስጥም የተቆራረጡ አልባሳትን፣ ጫማዎችንና በድን አካላትንም ለማየት ችላለች።
ዘነበ ኃይሌ ይባላሉ፤ በአጣዬ ከተማ የሚገኝ የባለ ሦስት ፎቅ ሕንፃ ባለቤት ሲሆኑ፣ ሕንፃውን ዳሽን ባንክ እና ለሆቴል ሥራ በማከራየት ይተዳደሩ የነበሩ ግለሰብ ናቸው።
የህወኃት ታጣቂዎች ሰኞ ኅዳር 5/2014 አጣዬ ከተማ እንደገቡ፣ ከእርሳቸው ሕንፃ ጎን የሚገኝ መኖሪያ ቤትን ለተጎዱ የታጣቂው ቡድን አባላት ሕክምና መስጫና ማረፊያ አድርገው ሲጠቀሙበት መቆታቸውን ይናገራሉ።
በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥም ሰው እንደተቀበረና ይህም ከባድ የሆነ መጥፎ ጠረን እየፈጠረ እንደሚገኝ የሚናገሩት ዘነበ፣ አሁንም ድረስ በሕንፃቸው ጣራ ላይ የአንድ ሴት ሬሳ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በድን አካሉንም አሳይተውናል። ሬሳውንም አውርዶ ለመቅበር በጣም እንደተቸገሩ ነው የተናገሩት። አክለውም፣ በግቢያቸው ውስጥ አንድ እጅ እና አንድ እግር አግኝተው ወስደው መቅበራቸውንም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳም እስከአሁን ካልተቀበረው ሬሳ በተጨማሪ፣ በግቢው ውስጥ ብዛት ያላቸው የቁስለኛ ማመላለሻ ቃሬዛዎች፣ የተቀዳደዱ ጫማና ልብሶች፣ እንዲሁም የህወኃት ኃይሎች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የተለያዩ ቁሳቁሶችም አሁንም ድረስ እንደሚገኙ ለመመልከት ችላለች።
‘‘የህወሓት ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን እንደሰማሁ፣ ከቤቴ በጓሮ በር በኩል ዘልዬ በመውጣት አመለጥኩኝ” የሚሉት ዘነበ፣ ነገር ግን በሕመም ላይ የነበረ አንድ የአክስታቸውን ልጅን ይዘው መውጣት ባለመቻላቸው ታጣቂዎቹ አግኝተው እንደገደሉባቸው በቁጭት ይገልፃሉ። ሰኞ ዕለት የሞተውን የአክስታቸውን ልጅ ሬሳ ሐሙስ ቀን አግኝተው በከተማዋ በሚገኝ ወንዝ አካባቢ ባለ ድልድይ ሥር እንደቀበሩትም ጨምረው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በከተማዋ የተከሰተው ችግር ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት የሕብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ዋነኞቹ ደግሞ ሕፃናትና ሴቶች ናቸው። በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በሚገኙ ሕፃናት ልጆች ፊት ላይ ከፍተኛ የሆነ የረሀብ፣ የእንግልትና ጦርነቱ ያስከተለው የሥነ-ልቦና ቀውስ በእጅጉን ይነበባል። የሕፃናቱ ሁኔታ አንጀት ይበላል።
ወጣት ሴቶችና እናቶችም በጥፋት ኃይሎቹ ባጡት የቤተሰብ አባል፣ በወደመባቸው ቤት ንብረትና እየደረሰባቸው ባለው እንግልት ምክንያት መራራ ቁጭትና ከፍተኛ ብሶት ውስጥ ገብተዋል።
በተጨማሪም፣ በከተማው አስተዳደር ተሠፍሮ በሚሰጣቸው ከ10 እና 15 ኪሎ ያልበለጠ ስንዴና አነስተኛ የዕለት ደራሽ የምግብ ግብዓት ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር እየተቸገሩ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ በከፍተኛ ምሬት አስረድተዋል።
ከሚመጣው የዕርዳታ እህል እና ቁሳቁስ ሕዝቡ አልወሰደም እንዳይባል ብቻ ተቀናንሶ ይሰጠናል እንጂ፣ ዕርዳታው ለሚገባው አካል ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እየተከፋፈለ አይደለም ይላሉ።
በተደጋጋሚ ከድጋፍ አድራጊዎች ዕርዳታ መጥቷል ተመዝገቡና ይደርሳችኋል ብንባልም፣ እስከ አሁን የደረሰን 1 ሊትር ዘይት እና 15 ኪሎ ስንዴ ነው። ሌላውን ሙሉ ለሙሉ ይደብቁታል፤ ሲመሽም ከመጋዘን አውጥተው ወደ ሌላ ቦታ ያሸሹታል ሲሉም ነው የከተማዋ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን የሚያሰሙት።
በከተማዋ በህወሓት ኃይሎች በተፈፀመው ወረራ ምክንያት ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎች ቁጥርም እጅግ ከፍተኛ ነው። እንደ አብነትም በ1962 ተመሥርቶ በከተማዋ የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው አጣዬ የመሰናዶና የኹለተኛ ደረጃ ት/ቤት በ2014 መጀመሪያ የመስከረም ወር ላይ 2 ሺሕ 958 ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር የቆየ ቢሆንም፣ በኅዳር ወር ላይ ግን በህወኃት ኃይሎች በተፈፀመው ወረራ ምክንያት ሙሉ በሙሉ መውደሙን አዲስ ማለዳ ለመመልከት ችላለች።
በት/ቤቱ የሚገኙ የ‹አይ ሲቲና የዲጂታል ላይብረሪ› ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ኮምፒውተሮች ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት እንዳይሰጡ ሆነው የውስጥ ዕቃቸው በታጣቂዎቹ ተዘርፏል፣ የሪከርድና ማህደር ክፍሎች ውስጥም ከ1962 ጀምሮ የተሰበሰቡ የተማሪ መረጃዎችና በንብረት ክፍሎች ውስጥ የነበሩ ንብረቶች እንዳይጠቅሙ ሆነው መውደማቸውን፣ ወንበሮች መሰባበራቸውን፣ የማስተማሪያ “ፕላዝማዎች” ተነቅለው መወሰዳቸውን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።
በትምህርት ቤቱ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት የወደመ ሲሆን፣ በቀጣይ ሙሉ ጥናት ተደርጎ የማሳወቅ ሥራ እንደሚሠራና ያ እስከሚሆን ግን ከውድመቱ የተረፉትን ወንበሮችና የትምህርት መሣሪያዎች በማሰባሰብ ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ የመማር ማስተማሩ ሒደት እንደተጀመረ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በሪሁን እሸቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የአጣዬ ከተማ የቀድሞ ገፅታ እንዳልነበር ሆኖ የተበላሸ ሲሆን፣ በርካታ ዜጎች፣ የባንክ የጥበቃ ሠራተኞች፣ የሆቴል ባለቤቶች፣ ለፍቶ አደር የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ በጦርነቱ ሳቢያ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ብዙዎች በመብሰክሰክ ስሜት ይናገራሉ።
አሁን ላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ሸሽተው ከተጠለሉባቸው የገጠር ቀበሌዎችና በአቅራቢያቸው ከሚገኙ ድብቅ ጫካዎች በመውጣት ወደ ከተማዋ እየተመለሱ ይገኛሉ። ቢሆንም ግን እሰከ አሁንም ድረስ ያሉበት ቦታ ያልታወቀና ያልተገናኙ ቤተሰቦች መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ለመረዳት ችላለች። በርካታ አረጋውያን ያለጧሪና ቀባሪ፣ ሕፃናትም ያለ አሳዳጊ መቅረታቸውንም ተመልክታለች።
የጦርነት አስከፊነት ትርፉ ሥደትና ሞት መሆኑ ነው። ያንን ሥደትና ሞት ደግሞ የሚቀምሱት ምንም የማያውቁት ንጹኃን ዜጎች ናቸው። ስለሆነም ከማንኛውም ጊዜው በላይ ለእነዚህ ዜጎች በተባበረ ክንድ ልንደርስላቸውና ወገንተኝነታችንን ልናሳያቸው ይገባል።
ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014



