የኢትዮ ቴሌኮም የኮፐር ኬብሎችን በሰረቁ ግለሰቦች ላይ እስከ 12 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ተወሰነ

0
494

ሰኞ ታህሳስ 18/ 2014 (አዲስ ማለዳ) የአዳማ ከተማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ታህሳስ 5 ቀን 2014 በዋለው ችሎት የኢትዮ ቴሌኮም ኮፐር ኬብሎችን በቆረጡ እና ስርቆት በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ እስከ 12 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት መወሰኑ ተገለፀ።

የኢትዮ ቴሌኮም ለአዲስ ማለዳ በላከው መረጃ እንዳስታወቀው ወንጀሉን የፈፀሙት አንደኛ ተከሳሽ ለጋሳ ሀይሉ በ11 ዓመት ፅኑ እስራት፤ እንዲሁም በ2ኛ ተከሳሽ ፉአድ አሚን ላይ ደግሞ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።

በፅኑ እስራት የተቀጡት እነዚህ ተከሳሾች በአዳማ ከተማ ቦሌ ከፍለ ከተማ አርባ ሜትር ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ በግምት ከለሊቱ 8 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት ባለው ጊዜ ላይ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ንብረት የሆኑ የኮፐር ኬብሎችን በመቆራረጥ ይዘው ለመሰወር ሲሞክሩ በአካባቢ ጸጥታ ሀይል እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ አቃቢ ህግ በአዳማ ከተማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ መስርቶ ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው ማድረጉም ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በአዳማ ከተማ ቦሌ ከፍለ ከተማ ጎሮ ቀበሌ ልዩ ቦታዉ ስላሴ ቤተክርስቲያን አካባቢ በግምት ከለሊቱ 8 ሰዓት ላይ አብዱልፈታ ከድር የተባሉ ተከሳሽ የኢትዮ ቴሌኮም የኮፐር ኬብሎችን ሰርቀው ሲሄዱ በአካባቢ ጸጥታ ሀይል በቁጥጥር ሥር ውለው በአቃቤ ህግ በኩል በአዳማ ከተማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ በመመስረት ታህሳስ 5 ቀን 2014 በዋለው ችሎት ተከሳሹ በ7 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።

ኢትዮ ቴሌኮም ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ለፍርድ ላቀረቡ የህግ አካላትን በሙሉ ምስጋናን በማቅረብ፤ የህዝብ ሀብት በሆነውንና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ በሚገባው ኬብል ላይ የሚደርስ ጉዳት በአገር፣ በኢትዮ ቴሌኮምና በቴሌኮምአገልገሎት ተጠቃሚው ማህበረሰብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል።

ስለሆነም ሕብረተሰቡ ይህንንም በመገንዘብ በአካባቢው በሚገኝ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ኢትዮ ቴሌኮም ጥሪውን አቅርቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here