ዕሮብ ታህሳስ 27/2014 (አዲስ ማለዳ) በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ክልል ሕዝብ ያሉበት ችግሮች እንዲፈቱለት ለማድረግ መንግሥት ዝግጁ መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ክልል ሕዝብ ያሉበት ችግሮች እንዲፈቱለት መንግሥት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፣ የትግራይ ሕዝብ ለጥቂት የሥልጣን ጥመኞች ሲባል ልጆቹ እንዳይማገዱ ህወሓትን መቃወም እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።
አክለውም መንግሥት በአገር ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመቀልበስ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ተጠቁሟል።
በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን በከፈተው ጦርነት ለተጎዱ እና ለመከላከያ ሠራዊት በተግባር እየታየ ያለው የወገን አለኝታነት የሚያኮራ መሆኑንም አሳውቀዋል።
ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አርቅርበዋል።
ዳያስፖራውም ለአገራዊ ጥሪው እየሰጠው ምላሽ አኩሪ መሆኑን ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።
መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ይገነዘባል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ችግሮችን ለማስተካከልም የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ወደ ትግራይ ክልል አንዳይገባ መወሰኑን ተከትሎ መከላከያ ሠራዊት የያዛቸውን ቦታዎች ይዞ እና አፅንቶ እንዲቆይ ተደርጓል፤ ከውሳኔው በኋላ ምንም እንቅስቃሴ አልተደረገም ብለዋል።
የትግራይ ክልል ሕዝብ ወደ ቀድሞ ህይወቱ እንዲመለስ ሕዝቡም ሆነ በውጭ የሚኖሩ አካላት በህወሓት የደረሰውን ጉዳት መመከት አለበት ብለዋል።
ለዚህም መተባበር እና ሁሉም የበኩሉን አበርክቶ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳውቀዋል።
ከህወሃት ቡድን ነፃ በወጡ የአፋር እና የአማራ ክልል አከባቢዎች የተጎዱ ሰዎችን ለመደገፍ እና የወደሙ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ወደ መደበኛ ሥራ የመመለስ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአማራም ሆነ በአፋር ክልሎች የዞን አደረጃጀት እና የወረዳ አስተዳደር ወደ ሥራ ገብተዋል፤ የቀበሌ አስተዳደር መዋቅርን ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል።
በተጨማሪም ነፃ በወጡ አካባቢዎች የቴሌኮም፣ የመብራት እና የባንክ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን የማስጀመር ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
ሚኒስትሩ በመግለጫቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላሊበላ እና ወደ ኮምቦልቻ የበረራ ሥራ መጀመሩንም አውስተዋል።
የወደሙ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ተቋማትን የመጠገን ሥራ እየተሠራ መሆኑን እና በዚህም ጥገናቸው አልቆ ሥራ የጀመሩ ተቋማት መኖራቸውን መግለጻቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
ቀሪዎቹን ወደ ሥራ ለማስገባት ሁሉም የተጠናከረ ሥራ በመሥራት ላይ ናቸው ብለዋል።
ትርፍ አምራች አካባቢዎች ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳውቀዋል።
_____________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




