አሰለፍ አሰፋ ይባላሉ። ኑሯቸው በአማራ ክልል የደቡበ ወሎ ዞን መቀመጫ በሆነችው ደሴ ከተማ ሲሆን፣ የ63 ዓመት እናት ናቸው። ደሴ በሰሜኑ ጦርነት ሠለባ ከሆኑ ከተሞች መካከል አንዷ ሆና የጦርነት ጠባሳ አርፎባታል። በዚህም የደሴ ከተማዋ እናት የጦርነት ሠለባ ከሆኑት ሰዎች መካከል አንዷ ናቸው።
ደሴ የጦርነት ዓውድማ መሆኗን ተከትሎ የጉዳት ሠላባ የሆኑት የ63 ዓመቷ የከተማዋ ነዋሪ፣ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ በምግብ አብሳይነት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር። በአሸባሪነት ተፈረጀው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ደሴ ከተማ በገባበት ወቅት የ63 ዓመቷ አዛውንት በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል በሥራ ላይ ነበሩ።
ህወሓት ደሴን ሲቆጣጠር በሥራ ላይ የነበሩ ቢሆንም፣ ከህወሓት መግባት በኋላ መደበኛ ሥራቸውን መቀጠል አልቻሉም። ሆስፒታሉን ለቀው ወደ መኖሪያ ቤታቸው አቀኑ። ህወሓት ሆስፒታሉን ተረከበ፤ የደሴዋ እናት ቡድኑ ደሴን ለቆ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በችግር ቆይተዋል።
ሥራቸውን ማቋረጣቸውን እና የነበራቸውን ንብረት በህወሓት ታጣቂዎች መዘረፉን ተከትሎ፣ በእጃቸው ላይ ምንም ዓይነት ገንዘብና ንብረት የላቸውም። አዛውንቷ ምንም እንኳን ንብረታቸውን ቢዘረፉም በከተማዋ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር ተጠልለው እየኖሩ ነው። በዚህ ኹኔታ ላይ እያሉ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የገና በዓል ደረሰ። ይሁን እንጅ በጊዜዊነት የተጠለሉባቸው ቤተሰቦቻቸውና አዛውንቷ ባሳለፍነው ታኅሣሥ 29/2014 የተከበረውን የገናን በዓል እንደ ከዚህ ቀደሙ ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ በደስታ ሳይሆን፣ በሐዘን ጥላ ሥር ሆነው ነው ያከበሩት።
የደሴዋ እናት በዓሉን በሐዘን ውስጥ ሁነው እንዲያከብሩ ያስገደዳቸው የንብረታቸው መውደም ብቻ አይደለም። አብሯቸው ይኖር የነበረውን በሹፍርና የሚተዳደር የልጅ ልጃቸውን በህወሓት ታጣቂዎች በመነጠቃቸው ነው። የ63 ዓመቷ አያት የልጅ ልጃቸው በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በሹፍርና ተቀጥሮ የሚሠራ የ23 ዓመት ወጣት የነበረ ሲሆን፣ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ያሳደጉት፣ ብቸኛ ልጃቸውና አብሯቸው የሚኖር ቤተሰባቸው ነው።
በህወሓት ታጣቂዎች የተገደለው የ23 ዓመቱ ወጣት ለአያቱ በኑሯቸው የሚጎድለውን የሚሸፍንላቸው እና ተንከባካቢያቸው እንደነበር የሚገልጹት አዛውንቷ፣ ኹል ጊዜ በዓል ሲመጣ በተለይ በገና በዓል በግ ገዝቶ ሥጋ የሚያበላኝ፣ በዓሉን የሚያደምቅልኝ አንድ ልጄ ነበር ይላሉ። “በነፍሰ በላዎች የተነጠኩት የልጅ ልጄ፣ ብቸኛ ልጄ ጥሎለኝ ያለፈው ስጦታየ ነበር። አሁን እሱም ወደ አባቱ ሔዴ፤ እኔም ብቻየን ቀረኹ” ሲሉ አዛውንቷ ሐዘናቸውን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
ለወትሮው በቤታቸው ከጎረቤቶቻቸው ጋር እና ከልጅ ልጃቸው ጋር የገናን በዓል በድምቀት የሚያከብሩት አዛውንት፣ የዘንድሮውን ገና በሐዘን ተውጠው አሳልፈውታል። የጦርነት ጠባሳ ባረፈባት በደሴ ከተማ ቤተሰቦቻቸውን በጦርነቱ ምክንያት ያጡ እና ለዓመታት ያፈሩትን ቤት ንብረታቸውን አጥተው ያለፈውን የገናን በዓል በሐዘን ጥላ ሥር ያከበሩ ወገኖችን አዲስ ማለዳ ቤቱ ይቁጠራቸው እያለች ወደ ሌላኛዋ የጦርነት ሠለባ አልፋለች።
ወልዲያን የአካባቢው ነዋሪዎች “የሰሜን ወሎዋ ኮከብ” ይሏታል። በተራራዎች የተከበበችው የሰሜን ወሎ ዞን መቀመጫዋ ወልዲያ፣ በሰሜኑ ጦርነት ከተጎዱት ከተሞች መካከል ግንባር ቀደምት ነች። ሀወሓት በሰሜን ወሎዋ መዲና ወልዲያ ለአምስት ወራት የቆየ ሲሆን፣ በቆየባቸው ጊዜያት የወልዲያ ሕዝብ ከጦርነት በተጨማሪ ርሃብና ውኃ ጥም ሲፈራረቁበት የቆየ መሆኑን ከተማዋ ነፃ ከወጣች በኋላ ከነዋሪዎቿ የወጡ ድምጾች መስክረዋል።
አበበ ፍቅር የወልዲያ ከተማ ነዋሪ የ30 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ኑሮውን የሚገፋው ከጓደኞቹ ጋር በጋራ በከፈቱት ብረታ ብረት ሥራ ነበር። ይሁን እንጂ ህወሓት ወደ ወልዲያ ሲገባ፣ አበበ እና ጓደኞቹ ሥራቸውንና ንብረታቸውን ጥለው ወደ ደሴ ተፈናቀሉ። አበበ እና ጓደኞቹ ከወልዲያ ተፈናቅለው ደሴ ቢጠለሉም ከወራት በኋላ ደሴም በህወሓት እጅ መግባቷን ተከትሎ፣ አበበ እና ጓደኞቹ ከሰለጠኑ ሕዝባዊ ኃይሎች ጋር ተሠልፈው ህወሓተን ለወራት ሲፋለሙ ቆይተዋል።
አበበ እና ጓደኞቹ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ተሠልፈው ለወራት ሲዋጉ ቆይተው፣ ወልዲያ ነጻ ስትወጣ ወደ ከተማዋ ተመልሰዋል። ወጣቶቹ ወልዲያን ለቀው የሔዱት ህወሓት ወጣቶችን አፈላልጎ ይገድላል መባሉን ተከትሎ በቤተሰቦቻቸው ግፊት ነበር።
ከወራት ቆይታ በኋላ ወደ ቤሰቦቻቸው የተመለሱት አበበ እና ኋደኞቹ፣ የገናን በዓል እንዴት እንዳሳለፉ ለአዲስ አዲስ ማለዳ አጋርተዋል። የወልዲያዎቹ ወጣቶች ወደ ቤተሰቦቻቸው ቢመለሱም፣ ተባብረው የከፈቱት የብረታ ብረት መሥሪያ ሙሉ በሙሉ ተዘርፎባቸዋል። ወጣቶቹ የህወሓት ሠላባ ላለመሆን ለወራት ከወልዲያ ተለይተው በቆዩባቸው ጊዜያት፣ ንብረታቸውን ብቻ አልነበረም ያጡት። የአበበ ታናሽ እህት በህወሓት ታጣቂዎች ታፍና እንደተወሰደች እልተመለሰችም። እንዲሁም የአበበ ጓደኛ የደምሴ በቀለ እህት በህወሓት ታጣቂዎች ተደፍራለች።
ወጣቶቹ ህወሓትን ሽሽት ለወራት ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ቢቆዩም፣ ቤተሰቦቻቸው የህወሓት ሠለባ ከመሆን አልተረፉም። በዚህም ያለፈውን ገናን በወልዲያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማክበር ዕድል ቢያገኙም፣ በዓል እንደወትሮው በደስታ እና በበዓል ድባብ የታጀበ አልነበረም።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገው አበበ የገናን በዓል የሱ እና የጓደኞቹ ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን፣ ብዙዎች በአንድም ሆነ በሌላም በኩል የጦርነቱ ሠላባ መሆናቸውን ተከትሎ ወልዲያ የገናን በዓል ወትሮ ከነበረው የደስታ እና የበዓል ድባብ በተለየ በትካዜ እንዳከበረች ይገልጻል።
ወልዲያ ለአምስት ወራት በህወሓት ተይዛ በቆየችባቸው ወራት የደረሰባት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት የከፋ ነው የሚለው አበበ፣ የወልዲያ ሕዝብ የገናን በዓል ያከበረው በአብዛኛው በሐዘን እና በትካዜ ስሜት ውስጥ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ከህወሓት ነጻ በመውጣቱ እና ተለያይቶ የነበረው ቤተሰብ በመገናኘቱ ከነበረው ጭንቀት እስትንፋስ የሠጠ ኹኔታ መታየቱን ይገልጻል።
ወልዲያ አሁን በህወሓት የደረሰባት ውድመት ሕዝቡን ባዶ እጁን ያስቀረ ነው የሚለው አበበ፣ አሁን ላይ ቀድሞ የግል ሥራ የነበረው ሥራ አልባ ሆኖ ከመንግሥት እና ከለጋሽ ድርጅቶች የሚያገኘውን ድጋፍ እየጠበቀ የሚኖር ሆኗል ይላል። ሁኔታው የገናን በዓል በሐዘን እና በትካዜ ድባብ እንዲያከብሩ ቢያስገድዳቸውም፣ ከቀሪ ቤሰቦቻቸው ጋር ተገናኝተው የችግሩ ተጋሪ በመሆናቸው ደስተኛ መሆናቸውን የሚገልጸው አበበ፣ ወልዲያ ከዚያ ሁሉ ጉዳት በኋላ በቀዘቀዘ ኹኔታም ቢሆን በሠላማዊ እንቅስቃሴዋ ቀጥላለች ይላል።
የገና በዓል በቀዘቀዘ ድባብ በሐዘኔታ ውስጥ ሁነን አሳልፈናል የሚሉት እነዚህ የጦርነቱ ተጎጂዎች፣ ቀጣዩ የጥምቀት በዓልም ተመሳሳ ሆኖ እንደሚያልፍ ይገምታሉ። ያለው የሌለውን እያገዘ በትብብር ቢያልፍም፣ በጦርነቱ ይበልጥ የተጎዱ ሐዘናቸውን የሚያስረሳቸው ባይሆንም እንዲጽናኑ የሚያደርግ ተግባር ላይ መሳተፍ የኹሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014



