በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነና ያለማስያዣ የዲጂታል ብድር ማቅረብ የሚያስችል “ምቹ” የተሠኝ መተግብሪያ በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ እና በክፍያ ፋይናንሽያል ቴክኖሎጂስ በጋራ ይፋ ተደረገ።
በባንኩ እና በክፍያ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ የተበለጸገው መተግበሪያ፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎ (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) የሚንቀሳቅስ የዲጂታል ብድር ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ በተለየ መልኩ ተበዳሪዎች የብድር ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ምንም ዓይነት ማስያዣ ወይም ዋስትና ማቅረብ የማያስፈልጋቸው መሆኑ ተገልጿል።
“ምቹ” የተሰኘው የዲጂታል ብድር አቅርቦት መተግበሪያ፣ በጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ንግድ ላይ የተሠማራውን የሕብረተስብ ክፍል የብድር አግልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ የበለጸገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በተያያዘም ቴክኖሎጂው፣ ለአነስተኛ እና መካካለኛ ንግዶች የመሥሪያ ካፒታል ለመሸፈን እንዲውል የታሰበበት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለተለያዩ ድርጅት ሠራተኞች ለግል ጉዳይ የሚውል የብድር አግልግሎት መሠጠት የሚያስችል መሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ሥራ አስፈጻሚ ደርቤ አስፋው ደንበኞች የሚያገኟቸው የብድር አገልግሎቶች በኹለት እንደሚከፈሉ ገልጸው፣ አንደኛው ዓይነት ማይክሮ ብድር ለጥቃቅን የንግድ ሥራዎች የሚውል ሲሆን፣ ይህም የመንገድ ዳር ንግድ ላይ የተሠማሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የማይክሮ ብድር ከፍተኛ የብድር ጣሪያ 30 ሺሕ ብር ሲሆን፣ በአራት ወራት የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚመለስ መሆኑን ደርቤ ገልጸዋል።
ኹለተኛው ደግሞ፣ ለአነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ ተቋማትን አቅም ማሳደግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚሀ ምድብ የሚሰጠው ብድር እስከ 150 ሺሕ ብር የሚደርስና የመመለሻ ጊዜው እስከ አንድ ዓመት ሊረዝም የሚችል እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
“በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይንም የሰው ሠራሽ ልኅቀትን የሚጠቀም የዲጂታል ብድር መድረክ (ፕላትፎርም) ለአገራችን በማበርከታችን ደስተኛ ነን” ያሉት ደግሞ የክፍያ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂሰ ሥራ አሰፈጻሚ ሙኒር ዱሪ ናቸው። አክለውም አገራችን የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ አንድ ዕርምጃ ወደፊት የሚያራምድ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ቴክኖሎጂው ያለ ማሲያዣ የሚሠጥ ብድርን ለመጀመሪያ ገዜ ያሰተዋወቀ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሙኒር፣ መተግበሪያው በዋስትና ማስያዣ ዕጦት ሥራቸውን ማሳደግ ላቃታቸው በአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ዘርፍ ለተሠማሩ፣ እንዲሁም በመንገድ ንግድ ላይ ላሉ ዜጎቸን የተሻለ አቅም እና ዕድል ይፈጥራል ብለው እንደሚያምኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የባንክ እና ፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት አድም መሐመድ፣ እንደዚህ ዓይነት መተግበሪያ መበልጽጉ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ያለ ማስያዣ እና ዋስተና የሚሠጥ ብድር የመበላሸት ዕድሉ ይሰፋል ብለዋል። ነገር ግን፣ ባንኩ የሚበላሽ ብድርን የሚያስታምምበት ጠንካራ ዕቅድ ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
ያለጥሬ ገንዘብ ግብይት ማካሄድ በተውሰነ መልኩ በከተማ ደርጃ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም፣ በተለየ መልኩ የባንክ ተደራሽነት በሌለባቸው አካባቢዎች እና በሱማሌ ክልል በተሻለ መልኩ ትግበራ ላይ እየዋለ ይገኛል። ምን አልባትም ይህ መተግበሪያ በነዚህ አካባቢ ላይ ስኬታማ ሊሆን ይችላል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የክፍያ ሥራ አስፈጻሚ ሙኒር በበኩላቸው፣ ሥጋት ሊኖር እንደሚችል የታወቀ ቢሆንም፣ ከ10 ዓመት በፊት የተቋቋመው “ታላቅ” የተሠኘ የሞባይል ብድር መተግበሪያ በኬንያ ብቻ ከ20 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ ካሉት ሥጋቶች በላይ ትርፋማ የሆነ ተቋም ሆኗል። ስለዚህ በኛም አገር ስኬታማ የማይሆንበት ምክንያት የለም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014




ብድሩን በተመልከተ ማብራሪያ ቢሰጥ