ከፍራፍሬ ዓይነቶች አንዱ የሆነው ሎሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው እየናረ በአንድ ዓመት ውስጥ ዋጋው በዕጥፍ ጭማሪ አሳየ።
ይህን ተከትሎም በተለይ በአዲስ አበባ ከአንድ ዓመት በፊት አንድ ፍሬ ሎሚ በአምስት ብር ይሸጥ የነበረው፣ አሁን ላይ 10 ብር እንደሚሸጥ አዲስ ማለዳ በተለያዩ ቦታዎች ተገኝታ አረጋግጣለች።
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ አትክልት ተራዎችም እንዲሁ፣ አንድ ኪሎ ሎሚ እስከ አንድ መቶ ኻያ ብር የሚሸጥ ሲሆን፣ በዚህን ያህል ዋጋ የሚሸጠው ሎሚም ጥራቱን ያልጠበቀ፣ ተቆርጦ የቆየ ወይም ፀሐይ መቶት የደረቀ እና መጠኑ በጣም አነስተኛ የሆነ ነው።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አትክልት ሻጮቹ እንደገለጹት፣ አንድ ፍሬ ሎሚ ከአምስት ብር በላይ መሸጥ የጀመረው ከባለፈው ዓመት ጀምሮ (የጥምቀት በዓል ሰሞን) ነው።
በተለይ በበዓላት ወቅት በቀላሉ ገበያ ላይ ማግኘት እንደሚያስቸግር እና ዋጋውም የተጋነነ መሆኑ ነው በሸማቶች የሚነገረው። በተለያዩ የክልል ከተሞችም አንድ ፍሬ ሎሚ ከሦስት ብር እስከ ስምንት ብር እንደሚሸጥ አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
እንዲሁም፣ ሎሚ ዋጋው ከመጨመሩም ሌላ ገበያ ላይ ከፍተኛ ዕጥረት መኖሩ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ዳይሬክተር አብደላ ነጋሽ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባይ እና በሽታ ምርቱን እያጠቃው ስለመጣ እንደ አገር የሎሚ ፍራፍሬ ዕጥረቱ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
አክለውም፣ አርሶ አደሩ የሚጠቀመው የሎሚ ዝርያ ተባይን የመቋቋም አቅሙ ደካማ በመሆኑ የሚገኘው ምርት ውጤታማ አይደለም ነው ያሉት።
በዚህም አርሶ አደሩ ለራሱ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ለንግድ ብሎ እያመረተ እንዳልሆነ አንስተዋል። ሎሚ ምርት ለመስጠት ረዥም ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑም፣ አርሶ አደሩ ያን ያህል ጊዜ ጠብቆ ምርትና ገቢ የማያገኝበት ከሆነ ለማምረት አይገፋፋም ሲሉ ገልጸዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ከኹሉም በፊት ተባይ የሚቋቋም ዘር ለአርሶ አደሩ መቅረብ አለበት ያሉት ዳይሬክተሩ፣ እንደ አገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ያለው የምርምር ትኩረት በጣም ውስን መሆኑን አመላክተዋል።
እስካሁንም የምርምር ሥራዎች የሚሠሩት ቶሎ በሚደርሱ የሰብል ምርቶች ላይ ነው። ለምርምር ተቋማቱም በመንግሥት በኩል በጀት እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ሲደረግላቸው አይታይም። ያለ ምርምር ደግሞ የተሻለ የምርት ውጤት የለውም ሲሉ ተደምጠዋል።
ዳይሬክተሩ ሎሚ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ፍራፍሬዎች ላይም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን አመላክተዋል።
እንደ ማሳያ ያነሱትም ብዙ አርሶ አደሮችን ከገበያ አርቋል ያሉትን የማንጎ ምርትን ነው። ብርቱካንም እንዲሁ በየጊዜው የምርት መጠኑ እየቀነሰ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ችግሩ እንዲፈታ ከተፈለገ የምርምር ሥራ ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ተባይ እና በሽታ የሚቋቋም ዘር ማቅረብ ወይም ከውጭ የተሻለ ዝርያ ማስገባት መፍትሄ ነው ባይ ናቸው።
በዚህ ረገድም ችግሩን ለመፍታት ምንም እየተሠራ አይደለም ማለት ይቻላል፣ ትንሽም በአቮካዶ ምርት ላይ ነው እንቅስቃሴ ያለ የሚመስለው። ይህም ቢሆን በአርሶ አደሩ እና በአጋር አካላት ትብብር ላይ የቆመ ነው ብለዋል።
እንደ አገር በሚመለከታቸው አካላት በኩል ትኩረት ማጣት እና ቸልተኝነት መኖሩን ጥቆማ ሰጥተዋል።
ሎሚ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአማራ እና ደቡብ ክልሎች እንደሚመረት ጠቅሰው፣ ፍሬ የሚገኝበት ወቅት ግን እንደ አየር ንብረቱ እና እንደ ሎሚው ዝርያ ይለያያል ነው ያሉት።
ሎሚ ለዶሮ ማጠበያ፣ ለጁስና ለመጠጥ ቤቶች በግብዓትነት፣ ብሎም ለተለያዩ ጥቅሞችን የሚውል ጠቃሚ ፍራፍሬ በመሆኑ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ እና ዘርፈ ብዙ መሆኑ ይገለጻል።
እንዲሁም፣ ከጥምቀት በዓል ጋርም ለባህላዊ ክንዋኔ ተያያዥነት ያለው በመሆኑ ይበልጥ ተፈላጊነት እንደሚኖረው እና ዋጋውም እንደሚጨምር ይታሰባል።
ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014



