ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ የቡና ዋጋ በኪሎ ከ 200 ብር በላይ ጭማሪ አሳየ

0
2219

ባሳለፍነው ሳምንት ለአገር ውስጥ የሚቀርብ የቡና ዋጋ ከወትሮው በተለየ እና በተጋነነ መልኩ በ 1 ኪሎ ከ 80 ብር ጀምሮ እስከ 200 ብር የሚደርስ ጭማሪ እየስተዋለበት ይገኛል። በመዲናዋም የሚገኙ የቡና አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ቤቶች ላይም ቡና ከተለመደው ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ለማወቅ ተችሏል። የአንድ ስኒ ቡና ዋጋ ከ7 ብር እስከ 15 የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት 20 ብር እና ከዛም በላይ እየተሸጠ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የታወቀችበት የኮፊ አረቢካ ቡና እስከ ደረጃ አምስት የሚሆነው ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ሲሆን፣ ከዛ በታች ያለው ቡና ግን ለአገር ውስጥ ገበያ የሚውል ነው።

ለዋጋ ጭማሪው እንደዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ላይ የተከሠተው የዝናብ ዕጥረት እንደሆነ የቡና ዲጂታል ግብይት ጥናት ባለሙያ አብርሃም አሻግሬ በተለይ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

“ቡና በተፈጥሮው የሚሰጠውን ምርት ለመልቀም ቢያንስ አንድ ዓመት መጠበቅ ሊያሰፈልግ ይችላል ያሉት አብርሃም፣ ከዓመት በፊት 28 ብር ሲሽጥ የነበረው 1 ኪሎ ቡና በአሁኑ ሠዓት ከ 70 ብር በላይ ለአቅራቢዎቹ እየተሽጠ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በየዕለቱ ከ1 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ አገራት እየላከች መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለዓለም ገበያ ከሚቀርቡ የቡና ደርጃዎች በተጨማሪ፣ ከደረጃ አምስት በታች ያሉ የቡና ዓይነቶች በአሁኑ ሠዓት ተፈላጊነታችው እይጨመረ መጥቷል።

ብራዚል በገጠማት የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ቡናን ለዓለም ገበያ በሚፈለገው ልክ እያቀረበች አለመሆኑ የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነቱ እየጨምረ እንዲመጣ ማድርጉ የሚታወቅ ሲሆን፣ አሁን በደቡብ ከልል የተከሠትው የአየር ንብረት ለውጥ ካልተስተካከለ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርበው ቡና ሊቀንስ እንደሚችል ሥማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የቡና አቅራቢ እና ቡና ቤት ባለቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የቡና ገበያ ባለሙያው፣ አገር ውስጥ የቡና አቅርቦት ዕጥረት ቢፈጠር የጥራት መጓደል እንደሚከሰትና ቡናን በገብስ የመተካት ኹኔት እንደሚፈጠር ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ኾኖም ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ያስተላለፈው የ 70/30 መመሪያ ምናልባትም የውጭ (ኤክስፖርት) ንግድ ላይ የተሠማሩ የቡና ላኪዎችን ያዳክማል የሚሉት በቡና ንግድ ላይ የተሠማሩት ግለሰብ፣ ለውጪ ገበያ የሚውለውን ቡና ለአገር ውስጥ ፍጆታ በሕገ ወጥ መንገድ ቢያውሉት የባሰ የቡና ዋጋ ግሽበት ሊያጋጥም እንደሚችል ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን በተያዘው 2014 በጀት ዓመት 280 ሺሕ ቶን ቡና ወደ ውጭ አገራት ለመላክ ያቀደ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ከቡና ንግድ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል።

ባሳለፍነው የ2013 በጀት ዓመት ወደ ውጭ አገር ከተላከ ቡና 907 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የሚታወስ ሲሆን፣ አሜሪካ፣ጀርመን፣ቤልጂየም፣ጃፓን፣ሳዑዲ አረቢያ እና ኮሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ቡና በስፋት ከተላከባቸው አገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ይህ በዚህ እንዳለም፣ የቡና ምርትን ለማሳደግ ያረጁ የቡና ዝርያዎችን ከመጎንደል ጀምሮ፣ አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን ማስፋፋት ላይ ልዩ ትኩረት ሠጥቶ መሠራት እንዳለበት አብርሃም ይናገራሉ። በዚሀም የተሻሻል ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በቅርቡ በቻይና ገበያ ውስጥ ለኢትዮጵያ ቡና ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱ የታወቀ ሲሆን፣ በቻይና በተካሄደ የቀጥታ ሽያጭ ሥነ-ሥርዓት 11 ሺሕ ከረጢት የኢትዮጵያ ቡና በአምስት ሰከንድ ውስጥ መሸጡን የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here