አገልግሎቱ ከኹለት ዓመት በላይ ዘግይቷል
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አምቦ ዞን በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች፣ በዘጠኝ ወር ውስጥ 50 ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ አካላት መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
በምዕራብ ሸዋ አምቦ ዞን ነኖ፣ ዳኖ፣ ጅፋት ወረዳዎች የሚኖሩ የአዲስ ማለዳ ምንጮች የገለጹት፣ እራሳችውን ለመከላከል የሚያስችላቸውን የጦር መሣሪያ ገዝተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈረጀውን የኦነግ ሸኔ ቡድንን ከአከባቢው ለማጥፋት በየጊዜው እየተዋጉ እንደሚገኙ ነው።
ነዋሪዎቹ ራሳቸውን በሚከላከሉበት ጊዜ ለምን ከቡድኑ ጋር ተታኮሳችሁ በሚል ምክንያትና ሠበብ ሠዎችን በማንነታቸው እየለዩለ፣ አንዳንድ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት በንጹኃን ዜጎች ላይ ዲሽቃ፣ ብሬንና ስናይፐር የጦር መሣሪያዎች በመጠቀም ጉዳትና ሞት እያደረሱባቸው መሆኑን የአከባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ነዋሪዎች አክለውም፣ የቤት እንስሳት፣ የግብርና ምርቶችና ሌሎች ሀብቶቻቸውም ጭምር በመንግሥት የፀጥታ አካላት እንደተወሰደባቸው ጠቁመዋል። አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ በአካባቢው በፀጥታ አካላት የሚፈፀሙ ግድያዎች ያልቆሙ መሆናቸውን ያረጋገጠች ሲሆን፣ ነዋሪዎች ለክልሉ መንግሥትና ለሠላም ሚኒስቴር ድምፃቸውን ቢያሰሙም የታደጋቸው አካል አለመኖሩን ገልጸዋል።
ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር አንስቶ እስካሁን ባለው ጊዜ በምዕራብ ኦሮሚያ አምቦ ዞንና በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ሸኔ ቡድን ንጹኃን ዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ግድያና ዝርፊያ እንዳላቆመ አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሠምታለች።
አዲስ ማለዳ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሠጡ ጠይቃ፣ ኮሚሽነሩ ሙሉ መረጃውን አጣርተው ምላሽ ለመስጠት ቀጠሮ አሲዘዋት የነበረ ቢሆንም፣ በቀጠሮዋ መሠረት ጋዜጣዋ ላደረገቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ምላሽ አልሰጡም፡፡ በተጨመሪም፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ መረጃ ለማግኘት አዲስ ማለዳ ያደረገችው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪም አልተሳካም።
ባለፈው ኅዳር ወር የከረዩ አባ ገዳን ጨምሮ 14 የገዳ አባቶች መገደላቸው የሚታወስ ነው።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና ክልሉን የሚያስተዳድረው ብልጽግና ፓርቲ ለአባ ገዳው እና ለገዳ አባቶቹ ግድያ ተጠያቂው “የኦነግ ሸኔ” ታጣቂ ቡድን ነው ማለቱ ይታወሳል።
የኢትዮጽያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፣ ከኹለት ወራት በፊት የተከሰተውን ግድያ ተከትሎ ባደረገው ምርመራ፣ ከግድያው ቀደም ብሎ በአካባቢው በርካታ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይልና መደበኛ የፖሊስ አባላት በታጣቂዎች መገደላቸውን ጠቁሟል።
ኮሚሽኑ በተጨማሪ፣ በሠዎች ግድያ ላይ በሰበሰባቸውና ባገናዘባቸው ማስረጃዎች መሰረት14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በግዳጅ ወደ ጫካ ተወስደው የአካባቢው አስተዳደር ኃላፊዎች ባሉበት ጭካኔ በተሞላበት ኹኔታ በጥይት ተመተው ተገድለዋል ብሏል። ይህም ግድያ ከሕግ ውጪ የተፈጸመ ግድያ ስለመሆኑ በምክንያታዊ ኹኔታ አሳማኝ ሆኖ እንዳገኘው ኮሚሽኑ በሪፖርቱ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014


