በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በደራሼ ልዩ ወረዳ ከባለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ ጀምሮ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከ200 በላይ ሰዎች የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የወረዳው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በአካባቢው ሚያዝያ 17/2014 በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በመንግሥትና በታጣቂ ኃይሎች መካከል በተደረጉ የተኩስ ልውውጦች የሞቱ፣ የቆሰሉና ሸሽተው ወደ ጫካ ገብተው ያልተመለሱ ሰዎች መኖራቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ማለዳ ዘገባውን እስካጠናከረችበት ስዓት ድረስ ከ10 በላይ ሰዎች እንደሞቱ እና ከ200 በላይ ሰዎች እንዲሁ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እና የት እንዳሉ የማይታወቁ ሰዎች መሆናቸውንም ኃላፊው ጠቁመዋል። እስከ አሁን የት እንዳሉ አይታወቁም ከተባሉት ሰዎች መካከል የሞቱ፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና ጫካ ገብተው ያልተመለሱትን እንደሚጨምር ተመላክቷል፡፡
ኃላፊው አክለውም በደራሼ ልዩ ወረዳ በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ቁጥራቸው ያልታወቁ አርሶ ደሮች ከቤት ንብረታቸው ባሻገር የሰብል ምርታቸው እንደተቃጠለ እና ከ24 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎችም ተፈናቅለው ዘመዶቻቸው ጋር ተጠግተው፣ ወደ ጫካ ሸሽተው እና የተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው ይገኛሉ ብለዋል።
በተጨማሪ ከላይ በተጠቀሱት ጊዜያት ሦስት የልዩ ወረዳው የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደተገደሉ እና 14 የመንግሥት አመራር ኃላፊዎች መኖሪያ ቤት እንደተቃጠለ ተገልጿል።
አዲስ ማለዳ ይህን የደራሼ ልዩ ወረዳ መረጃን አግኝታ ዜናው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ ከኹለት ሳምንት በላይ የጤና ተቋማት፣ የባንክ እና የፖሊስ ጽሕፈት ቤት መሥሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚሰጡ ቢሆንም፣ ሌሎች የመንግሥት ተቋማት እና የግል ድርጅቶች ግን እንደተዘጉ ተነግሯል።
በደራሼ ልዩ ወረዳ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ወደ ቀድሞ ሰላሙ ለመመለስ የጸጥታ አካላት በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኝ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የልዩ ኃይል አባላት በአካባቢው እንደሚገኙ ተነግሯል።
በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በመቅረፍ በጸጥታ ኃይሉ በኩል የማረጋጋት ሥራ በመሥራት ሁሉም የመንግሥት እና የግል ተቋማት መደበኛ ሥራቸውን እንዲያስቀጥሉ እየተሠራ ያለበት ሂደት አለ ተብሏል።
በተጨማሪ በተለያዩ ቀበሌዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና የሀይማኖት አባቶችን በማሰባሰብ የውይይት መድረኮችን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ያለበት ሂደት አለ። በደራሼ ልዩ ወረዳ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ማንነታቸው በማይታወቁ ኃይሎች ከሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ባሻገር የአካባቢው ነዋሪ ልዩ ወረዳውን ከሚያስተዳድሩት የመንግሥት አካላት ጋር ወደ ግጭት የሚገቡበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም ተመላክቷል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ደራሼ ዞን ይሁንልን የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም፣ ምላሽ እንዳላገኙ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል መንግሥት በኩል ልዩ ወረዳ እንዲሆን መጽደቁ ይታወቃል። ክልሉ ያጸደቀውን ውሳኔ የሚቃረኑ አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከደራሼ ልዩ ወረዳ ከተማ አስተዳደር ጋር እሰጥ-አገባ የሚገቡበት ጊዜ እንዳለም ተጠቁሟል።
ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014


