ምርጫ 2012ና ስጋቶች

0
1070

ምርጫ 2012 መቃረቡን ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ ይካሄድ ወይስ አይካሄድ በሚለው ዙሪያ ሐሳብ ሲሰጡ የቆዩ ቢሆንም የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው ሕዝብ ግን “ፍላጎቱ ምንድ ነው?” የሚለው ግን ያለተዳሰሰ ሆኖ ቆይቷል።

አዲስ ማለዳ በማህበራዊ ትስስር ገፆቿ አማካኝነት ከ3ሺህ በላይ ሰዎችን ድምጽ በመሰብሰብ እና በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ባደረገችው ቅኝት ብዙኋኑ ምርጫው ይራዘም የሚል ሀሳብ እንዳላቸውታዝባ ስጋት እና ተስፋቸውንም ሰብስባለች። ከዚህም ባሻገር በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ምርምሮችን የሰሩና የብዙ አገራትን ልምድ የቀሰሙ ምሁራንን እና የፖለቲካ ተንታኞች አነጋግረው ኤፍሬም ተፈራ እና ሐይማኖት አሸናፊ ሐተታ ዘ ማለዳን አሰናድተዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል በተያዘለት ቀን ይካሄድ ወይስ ይራዘም በሚል ውዝግብ ውስጥ የቆውን ቀጣዩ አገርዓቀፍ የምርጫ ጉዳይ እልባት አስቀምጧል። በሕገ መንግስቱ መሰረት በጊዜው እንዲካሄድ እንደ ድርጅት ካስቀመጠው አቅጣጫ ባሻገር እንደ መንግስትም ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጅት ይደረጋል ሲል ገዢው ፓርቲ በጉባዔው መዝጊያ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ይህንን መግለጫ ተከትሎም በህዝቡ ፣ በምሁራንና በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ዘንድ የተደበላለቁ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ።ሰንብተዋል።

አዲስ ማለዳ በማህበራዊ ትስስር ገፆቿ አማካኝነት ከ3ሺህ በላይ ጉዳዩ ይመለከተናል ያሉ ሰዎችን ሃሳብ በመሰብሰብ እንደዚሁም በአዲስ አበባ የተወሰኑ ጎዳናዎች ላይ ባደረገችው ቅኝት የብዙኋኑ ሐሳብ ምርጫው ይራዘም የሚል እንደሆነ ታዝባለች። በጎዳና ላይ መጠይቅ ከተሳተፉ 20 ሰዎች መካከል ዘጠኙ አስተያየት መስጠት የማይፈልጉ ሲሆኑ፤ ጭራሽ ምርጫ እንዳለ እንኳን አላውቅም ያለ አንድ ሰውም ገጥሟታል። በጋዜጣዋ የማህበራዊ ትስስር ገፆች (ፌስቡክ እና ትዊተር) ሃሳብ ከሰጡት ሰዎች መካከልም 57.3 በመቶ የሚሆኑት ምርጫው ይራዘም የሚሉ ሲሆኑ ቀሪ 42.7 በመቶዎቹ ደግሞ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መካሄድ አለበት ብለው ያምናሉ።

ምርጫው ይራዘም የሚሉት ወገኖች ቢያንስ ለአንድ አመት ይራዘም የሚል ድምፅ ሰጥተዋል።

ከጥበቃ ስራቸው ሲመለሱ ያገኘናቸው ታየው ከበደ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ቀውሶች መፍትሄ ማግኘት አለባቸው ብለው ያምናሉ፤ እንደሳቸው ገለፃ ከሆነ ከዛ በፊት ምርጫ ከተደረገ አገሪቱ ወደባሰ ችግር መግባቷ አይቀሬ ነው፤ ስለሆነም ይላሉ፣ ምርጫው ቢያንስ ከአንድ አመት ላላነሰ ከሁለት አመት ላልበለጠ ጊዜ ቢራዘም ይሻላል።

የግንባታ ተቋራጭ የሆኑት ቢኒያም ጣሰው በበኩላቸው “አሁን ባለው የብሄር መካከረር ላይ ምርጫ ተደምሮ የሚመጣው ግጭትና አለመግባባት ያስፈራኛል፣ ስለዚህ ምርጫው ለሁለት አመት ቢራዘም እና አሁን ያለው መንግስት ራሱን ቢያጠናክር”የተሻለ እንደሚሆን አስተያየት ሰጥተዋል። ከተወሰኑ ፓርቲዎች ውጪ ያን ያህል ጠንካራ የሚባሉ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ስለሌሉ መጀመሪያ ፓርቲዎቹን እንወቃቸው”ሲሉ ሃሳባቸውን ይገልፃሉ።

ምርጫው ይደረግ ያሉት የአንበሳ አውቶብስ ሰራተኛ ተስፋዬ ደሳለኝ በበኩላቸው “ያልመረጥነው ከሚገዛን፣ የመረጥነው ይግዛን”በማለት ሃሳባቸውን በአጭሩ ይቋጫሉ። “ምንም እንኳን ብዙ ጠንካራ ፓርቲ ባይኖርም ካሉት መሃል የተሻለውን እንመርጣለን”ብለዋል።

በምርጫው ላይ ሕብረተሰቡ ያለው አቋም የተለያየ የሆነውን ያህል ምሁራኑም የተለያየ አቋም አላቸው። የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ውሳኔ በቀጣዩ ምርጫ መካሄድ ላይ ያለው ውጤት ፓርቲው አሁን ባለው ወቅታዊ አቋም ለምርጫ እንደተዘጋጀና ምርጫው እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል የሚሉት በጀርመን አገር ጎቲንገን ዩኒቨርሲቲ የሕገ መንግስት እና የፌደራሊዝም ተመራማሪው በሪሁን አዱኛ (ዶ/ር) ናቸው። ውሳኔው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫው እንዲዘጋጁ እያስታወቀ እና እያሳሰበ ይመስላልም ይላሉ።

“ሆኖም ግን የአገሪቱ የፖለቲካ እና የፀጥታ ሁኔታ በጣም ተለዋዋጭ በመሆኑ የፓርቲው ውሳኔ በቀጣዩ ምርጫ መካሄድ እና አለመካሄድ ላይ ያለው ተፅዕኖ፣ በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ይሆናል”ሲሉ ውሳኔውን እንደ ገዢ ውሳኔ ለመውሰድ እንደሚያስቸግር ይናገራሉ።

በምርጫው ጊዜ ላይ ከሚነሱ ሃሳቦች መካከልም ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በመጥቀስና ምርጫ ሳይካሄድ አሁን ያለው መንግሥት የሚኖረውን ሕጋዊነት በማንሳት፣ በታቀደለት ጊዜ መካሄድ አለበት የሚሉ ሃሳቦች በአንድ በኩል ሲነሱ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ የፀጥታ፣ የሰላም፣ የፖለቲካና ተቋማዊ መደላድሎች የሉም በማለት ይከራከራሉ። በዚህ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ሳይካሄድ የቀረውን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በመጥቀስ ምርጫው መራዘም አለበት የሚሉ ክርክሮች መነሳት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

ከ1983 ወዲህ ከተካሄዱት አገርዓቀፍ ምርጫዎች የመጀመሪያው የሆነው የ1987ቱ ምርጫ ኢህአዴግ ከተቀናቃኝ ፓርቲዎቹ ጋር በገባው እሰጥ አገባ አማካኝነት፣ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ን እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ)ን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ ተገዳዳሪዎቹን ከሽግግር መንግስቱና ከአገር በማስወጣት የተካሄደ ምርጫ ነበር።

በ1992 የተካሄደው ምርጫ ኢህአዴግ በሰፊ ልዩነት አሸናፊ መሆኑ የተነገረበት ሲሆን፤ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠንክረው የወጡበት የ1997ቱ ምርጫም ቢሆን እንደ ጅማሬው የተሳካ ሆኖ መጠናቀቅ ያልቻለና ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ዜጎችን ለስጋት፣ ለእስር እና ለስደት የዳረገ እንደነበር ይታወሳል።

የ2002 ምርጫም የጠነከረ ፉክክር ያልታየበት ሲሆን ኢሕአዴግ 99.6 በመቶ የምክር ቤት ወንበሮችን አጋሮቼ ከሚላቸው ፓርቲዎች ጋር የያዘበትና የተቃውሞው ድምጽ በአንድ ግለሰብ ብቻ የተወከለበት ነበር። ይባስ ብሎ ይህ ውጤት በምርጫ 2007 100 በመቶ የምክር ቤት ወንበሮችን በመያዝ የብሔር፣ ሐይማኖት፣ የሐሳብና ሰፊ የሐሳብ ብዝሃነት ባለበት አገር ውስጥ ገዢው ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደሮችን መቀመጫ 100 በመቶ በመያዝ የህግ አውጪው የአንድ አይነት ድምፅ ብቻ የሚሰማበት ተቋም ሆነ።

ገዢው ፓርቲ የ2007ን ምርጫ ሙሉ ለሙሉ አሸነፍኩ ባለ ማግሽጽ ግን የህዝብ የተቃውሞ እና አመፅ በተለይ በኦሮሚያ ከዛም በአማራ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መምጣት ጀመረ፤ ይህም ለውጥ በኢህአዴግ ውስጥ ጭምር ቦታ እየያዘ በመምጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ እዲያስገቡ አስገደደ። በኢሕአዴግ ውስጥ እየተብላላ የመጣው የለውጥ መንፈስ በተለይ በኦሕዴድና ብአዴን ቅንጅት ለረጅም ጊዜ በሕውሓት ፊት አውራሪነት ሲዘወር የኖረውን የኢሕአዴግን መንግስት ይንጠው ያዘ። የሁለቱ የኢሕአዴግ እህት ፓርቲዎች ጥምርታ ኢትዮጵያ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኦህዴድ መንደር እንድታይ በከፈተው ዕድል መሰረት አቢይ አህመድ (ዶ/ር) በወርሃ ሚያዚያ 2010 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቃለ-መኃላ ለመፈፀም በቁ።

በዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው አዲሱ የፌደራል መንግስት አስተዳደር በርካታ አዳዲስ ለውጦችን ይዞ ብቅ ማለት የጀመረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙ ዕለት ነበር። ከአገር የተባረሩና በትጥቅ ትግል ተሳትፈው የነበሩ ኀይሎች ወደአገር እንዲመለሱና በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲሳተፉ ተደርጓል። በምርጫ 97 ወቅት ከፍተኛ የሕዝብ ተቀባይነት ከነበራቸው የፓርቲ መሪዎች ውስጥ በርካታ ግለሰቦችን የያዘው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ በአገር ቤት ሆነው በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ሆነው በአዲስ መልክ ከወረዳ በጀመረ አደረጃጀት የመሰረቱት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ወደ ፖለቲካው መድረክ መምጣት፤ እና ሌሎችም አዳዲስና ነባር በድምሩ ከ130 በላይ ፓርቲዎች በውህደትና በቅንጅት ህብረት ፈጥረው፣ ለምርጫ ራሳቸውን በማዘጋጀት ሂደት መሆናቸው የ2012ቱ ምርጫ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል።

ይህ ምርጫ ካለፉት በተለየ መልኩ ዲሞክራሲያዊ፥ ነፃ እና ገለልተኛ መሆን አለበት የሚሉት በሪሁን፣ አሁን ባለው አጠቃላይ ሁኔታ የይስሙላ ምርጫ ማካሄድ አገሪቱን ወደ ባሰ ችግር ከቶ እየታየ ያለውን የዲሞክራሲ ጭላንጭል ሊያጠፋ የሚችል ነው ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ቀጣዪ ምርጫ የኢትዮጵያን ችግር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈታ ሳይሆን፣ ዲሞክራሲያዊ አገር ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የሚጥል በመሆኑ፣ ከቀደሙት ምርጫዎች የተለየ ያደርገዋል የሚሉት በሪሁን በመንግስት፣ ገዢው ፓርቲና ሌሎችም የፖለቲካ ኀይሎች ላይ ከባድ ኀላፊነት ስለመጣሉም ያብራራሉ።
“መንግስት ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጋዜጠኞች በነፃነት ስራቸውን እንዲሰሩ ማስቻል ግድ ይለዋል። የሲቪል ማህበራት ከመቼዉም ጊዜ በላይ ስራቸውን በነፃነት እና በገለልተኝነት መከወን እና ምርጫ ቦርድም ያለአድሎ ፓርቲዎችን እና ህዝቡን ማገልገል ይኖርበታል”እንደ በሪሁን ገለፃ።

በተጨማሪም በተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱ ግጭቶት እና ድንገቴ የሰላም መደፍረሶች ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ይኖራል አይኖርም የሚል ጥርጣሬ እንደሚፈጥሩ በተለያዩ አካላት አስተያየት ሲሰጥበት ቆይቷል።

የእስከዛሬዎቹ ምርጫዎች በጊዜያቸው የተካሄዱ ከመሆናቸው ባሻገር ስለምርጫ የሚደነግገው የሕገ መንግስቱ ክፍልም፣ ምርጫ ስለሚራዘምበት ሁኔታም ሆነ አካሄድ ዝርዝር ሁኔታዎችን ያለማስቀመጡ ምርጫውን ለማካሄድ ባይቻል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለተለያዩ ክርክሮች አጋልጦ የሰጠ ነው።

በመሻሻል ላይ ያለው የምርጫ ህጉም ቢሆን ስለምርጫ መራዘም የሚለው ነገር አለመኖሩን የሚናገሩት ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ እና የህግ ምሁር አደም ካሴ (ዶ/ር)፣ ምርጫ በማንና መቼ ይራዘማል የሚለው ግልፅ አይደለም ይላሉ። ፓርላማው የምርጫ ህግ ያወጣል የሚል ስልጣን ስላለው፣ በዛ መሰረት የአካባቢ ምርጫዎችን አራዘመ እንጂ፣ ዝርዝር የህግ-ማዕቀፍ ያልተበጀለት ነገር ግን በግልፅ ሊደነገግ የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ። “ይራዘም እንኳን ቢባል በምን መንገድ፣ በማን ፈቃድና ለምን ያክል ጊዜ የሚለው ከባድ ውዝግብ የሚያስነሳ ነው”ሲሉ በምርጫ ላይ የተለያዩ ፅሁፎችን የፃፉተ አደም ይናገራሉ።

ቀጣዩ ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ የሚለው ክርክር ከሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች አንፃር፣ ከአገራዊ ነባራዊ ሁኔታና ከግል ጥቅም አንፃር እያዩ የሚከራከሩ ወገኖች መኖራቸውን አንስተው ክርክሩም የፖለቲካ መልክ ያለው እና በመራዘም እና ባለመራዘም በሚገኙ የፖለቲካ ትርፎች ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉም ያክላሉ።

እንደ አደም ምልከታ፣ አሁን ምርጫ መካሄድ አለበት የሚሉት ፓርቲዎች በብሄር የተደራጁ ናቸው። እነዚህ ፓርቲዎች በቀላሉ ድጋፍ ማሰባሰብ የሚችሉ በመሆናቸው፣ ሌሎች አማራጭ የፖሊሲ ሃሳብ ያላቸው ፓርቲዎች ሳይጠናከሩ ምርጫው ቶሎ እንዲካሄድ ይፈልጋሉ።

በእንግሊዝ አገር በሚገኘው ኪል ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ እና የፖለቲካ ተንታኙ አወል ቃሲም (ዶ/ር) ምርጫው በታቀደለት ጊዜ መካሄድ አለበት በሚል ገዢው ፓርቲ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመደገፍ “ትንሽ ችግር ቢኖርበት እንኳን የተካሄደ ምርጫ ይሻላል”በማለት “አሁን በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮች ምርጫው በአምስት ዓመት ቢራዘምም እኳን አይፈቱም”ሲሉም ይከራከራሉ። ምርጫው የማይካሄድባቸው ቦታዎች ቢኖሩም በቀጣይ በማሟያ ምርጫ መሸፈን ይሻላል እንደ አወል አስተያየት።

የሽግግሩ ጊዜ ከሰላምና ጸጥታ፣ እንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አንጻር በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱበት እንደመሆኑና ያሉትንም ችግሮች ለማስተካከል እንደመቸገሩ መጠን ሲታይ ምርጫው በተቆረጠለት ጊዜ የማይካሄድ ከሆነ ‹ወደ ዲሞክራሲ በሚደረገው ሽግግር› ላይ ያለንን ተስፋ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል ሲሉም አክለዋል።
“ሽግግሩ ተስፋ የሚጣልበት ስላልሆነ፣ አቅሙም ፈተና ውስጥ በመግባቱ የተለየ ነገር ይመጣል ብሎ መጠበቅ አይቻልም”ይላሉ።

ምርጫ 2012 እና ዝግጅቶቹ
የምርጫው መካሄድ እና ያለመካሄድ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ባይሰጠውም በተያዘለት የጊዜ ገደብ የመካሄድ አዝማሚያዎች እንዳሉ በመገንዘብ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች ይነሳሉ። የዴሞክራሲም ሆነ የሌሎች ተቋማት በቅጡ አለመደራጀትና በመደራጀት ላይ ያሉትም የለውጥ ስራቸውን አለማጠናቀቅ አንዱ እንደሆነ በባለሞያዎች ይነሳል።

ምርጫ ቦርድ
ምርጫውን በበላይነት የሚያስተባብረውና የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2012 ለሚያካሒዳቸው አገር ዐቀፍ ምርጫ፣ ለኹለቱ የፌደራል ከተሞች ምርጫ ማስፈጸሚያ፣ ለሕዝበ ውሳኔ ማስፈፀሚያ እንዲሁም ለሥራ ማስኬጃ በውጪ አጥኚዎች የተጠና የ3.7 ቢሊዮን ብር የበጀት ጥያቄ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ 2.7 ቢሊዮን ብር ፀድቆለታል። ይህም ቦርዱ በታሪኩ የተመደበለት ትልቁ በጀት ነው። በተጨማሪም ከለጋሽ መንግስታትና አለምዓቀፉ ተቋምት ድጋፍ እያገኘ ሲሆን ይህም እስከ አንድ ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ እየተነገረ ነው።

የቦርዱ የኮሚኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለኢዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ዋናው ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ ያለው ዝርዝር የምርጫ እቅድ ማውጣት እንደሆነ ገልፀዋል። የጊዜ ሰሌዳውን የማሰናዳት ስራው ሲጠናቀቅም፣ እያንዳንዱ ስራ በምን ያህል ጊዜ ይጠናቀቃል የሚለው ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ እና የጊዜ ጉዳይ ላይ ለመወሰንም ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ለቦርዱ የተገቡ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፎችን ለማሰባሰብም እየሰሩ እንዳሉ ተናግረዋል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ያሉትን ዝርዝር እቅድ በቦርዱ የሎጂስቲክስ እና የኦፕሬሽን ክፍል በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል። ቦርዱ ይህንን ተመልክቶ ውሳኔ ላይ ሲደርስ ውቴቱን ሳይዘገይ ይፋ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር ወደ 47ሺህ ከማደጉ ባሻገር ምርጫውን እስከዛሬ ከነበረው በተሻለ ጥራት ለማካሔድ መታሰቡ ለበጀቱ ማደግ ምክንያት እንደሆነ ቦርዱ ለምክር ቤቱ አስረድቶ ነበር። ለቀጣይ አገራዊ ምርጫ ከ250ሺህ እስከ ሶስት መቶ ሺህ የሚደርሱ የምርጫ አስፈፃሚዎችን ማሰማራት ሊያስፈልገው እንደሚችልም የቦርዱ ጥናት አመልክቷል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳም ፍትሃዊ ምርጫ የማካሄድ ጉዳይም የቦርዱ ኀላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የመንግስት እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የጋራ ሚና እንደሆነ እና ቦርዱም ከምርጫ በፊት ሙሉ ብቃትና ተዓማኒነት እንዲኖረው ተደርጎ መዘጋጀት አለበት ሲሉ ለአዲስ ማለዳ በጥር 25 ቀን ታትሞ በወጣው 12ኛ እትም ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር።

በቅርቡ አዳዲስ የቦርድ አባላት እና ሰብሳቢ የተሾመለት ምርጫ ቦርዱ የተሻለ ተቀባይነት እንዳለው የሚያወሱት አደም፣ ምርጫውን የመፈፀም አቅም ገንብቷል የሚለው ላይ ግን ጥርጣሬ አላቸው። ቦርዱ ለምርጫው የሚያስፈልጉትን በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ምርጫ አስፈፃሚ ሰራተኞች መልምሎና አሰልጥኖ በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ ማድረስ ይችላል ወይ የሚለው ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበትም ያሳስባሉ።

ተወዳዳሪ ፓርቲዎችንም የማሳመን ስራ ሌላው ስራ ነው ሲሉም ያክላሉ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ በ10 ወር ውስጥ ማሳካት ይችላሉ ወይ? ሲሉም ይጠይቃሉ። ስለዚህ ምርጫውን አወዛጋቢ እንዳያደርገው ያሰጋል፣ ምክንያቱም የህዝብ ተዎካዮች፣ የክልል ምክር ቤቶች፣ የወረዳና የቀበሌ ምርጫዎችም በመራዘማቸው ተፅዕኖውን ከባድ ያደርጉታል ሲሉ ምርጫው በበቂ ዝግጅት መካሄዱ የሚያመጣውን ችግር ያሳያሉ።

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
በቅርቡ አዲስ ኮሚሽነር የተሾመለት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንደ አንድ የዴሞክራሲ ተቋም በምርጫው ሂደት ላይ የራሱ ሚና እንደሚኖረው ከግምት ውስጥ በማስገባት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ኮሚሽነሩ ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ይናገራሉ። ምንም እንኳን ወደ ስራ ከገቡ ጥቂት ሳምንታትን ብቻ ያስቆጠሩ ቢሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ።

“የምርጫ ሂደቱ ሰብዓዊ መብቶችን ያከበረ እንዲሆን ከመስራት ባሻገር፣ ለምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ከሚፎካከሩባቸው መሰረታዊ ነጥቦች መካከል፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አንዱ እንዲሆን ለማድረግም እንሰራለን”ብለዋል። “ ምርጫ ቦርድ አዲስ ያረቀቀውን አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ካጸደቀ በኋላ የምርጫውን ማካሄጃ ጊዜ ገደብ ይፋ ያደርጋል ብለን እንጠብቃለን፣ ከዛም እቅድ አውጥተን ለመንቀሳቀስ ይረዳናል”ይላሉ።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ጠንካራ፣ ገለልተኛ እንዲሁም ነጻ ተቋም እንዳልነበረ የሚናገሩት ዳንኤል፣ ይህንን ለማሻሻል የለውጥ ስራዎችን መጀመራቸውን እና ይህም የተቋሙን ማቋቋሚያ አዋጅ ከማሻሻል እንደሚጀምር ይናገራሉ። ተቋሙን ከመንግስት የገንዘብ ጥገኝነት በማውጣት እና ባጠቃላይም ራሱን የቻለ ለማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩም ያስቀምጣሉ።

የተቋሙ የሰለጠነ የሰው ኀይል በሚፈለገው ደረጃ ተዋቅሯል ወይ የሚለው መታየት እንዳለበት የሚናገሩት ኮሚሽነሩ ለተቋሙ የሚመጥኑ ብቃት ያላቸውን በኮሚሽኑ ውስጥ ያሉትን ሰራተኞች ጨምሮ፣ ለስራው የሚያስፈልገውን የሰው ኀይል በማሰባሰብ፣ በማደራጀትና በማሰማራት ራሱን ማጠናከር ቅድሚያ ይሰጠዋል ብለዋል። ጠቅላላ የሰብዓዊ መብት ስራውን የሚመራ ስትራቴጂ እንደሚዘጋጅም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከእስከዛሬው በተለየም በመጪው ምርጫ ከመንግስት የሚሰነዘሩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ብቻ ስጋት ይሆናሉ ተብሎ እንደማይገመት አፅንኦት ይሰጣሉ፡፡“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመንግስት የተፈፀሙ እንዳልነበሩ ይታወቃል። ነገር ግን የፖለቲካ ቀውሱ የወለዳቸው በመሆናቸው እነዚህን የመብት ጥሰቶች ለማስተካከል በቅድሚያ የፖለቲካ ቀውሱን ማስተካከል ያስፈልጋል”ያሉት ዳንኤል፣ በመጪው ምርጫም በተለይ እንደ ደቦ ፍርድ ያሉ እና ከመንግስት የመይመነጩ ጥሰቶችንም ለመቆጣጠር መታሰቡን ይናገራሉ።

የሲቪል ማህበራት
በያዝነው አመት ተሻሽለው ወደስራ ከገቡ ጥቂት ህጎች አንዱ የሆነው የበጎ አድራጎት እና የሲቪል ማህበራት አዋጁ የሲቪል ማህበራትን በማደራጀት የሚፈጠሩ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ሚና ይኖራዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ በተለያዩ የሲቪል ማህበረሰቡ አካላት ዘንድ ሲነሳ ቆይቷል።

አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ወደ ስራ ከገባበት ከግንቦት ወር መጀመሪያ አንስቶ እሰካለፈው ሳምንት ድረስ ከ370 በላይ አዳዲስ የሲቪል ማህበራት ወደስራ መግባታቸውን የሲቪል ማህበራት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ ይናገራሉ። አዲሱ አዋጅ ከዚህ ቀደም በዴሞክራሲ፣ በመብት፣ በሰላም እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተደራጅቶ መንቀሳቀስን ላይ የነበሩ እንቅፋቶችን በማንሳቱ የምዝገባው ቁጥር መጨመሩን ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም በዓመት ሁለት መቶ የማይሞሉ አዳዲስ የሲቪል ማህበራት እንደሚቋቋሙ የሚገልፁት ፋሲካ በሶስት ወር ውስጥ ግን ከዛ የበለጠ የሲቪል ማህበራት መቋቋማቸውን ይናገራሉ። በአዲሱ አዋጅ መሰረትም በስራ ላይ ያሉ የሲቪል ማህበራት በድጋሚ እንዲመዘገቡ በወጣው መስፈረርት መሰረትም ከአንድ ሺህ በላይ የሲቪል ማህበራት በድጋሚ መመዝገባቸውን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ይህ ቁጥር እንደሚጨምር ግምታቸውን የሚገለፁት ፋሲካው፣ በምዝገባ ላይም ከ30 በላይ አዳዲስ የሲቪል ማህበራት መኖራቸውን ይናገራሉ።

ምርጫን በተመለከተም በሚቋቋሙበት ወቅት በምርጫ ላይ ለመስራት አላማ እንዳለቸው የገለጹ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ በአዋጁ መሰረትም ከምርጫ ቦርድ ፈቃድ ካገኙ በኋላ ወደ ስራ እንደሚገቡ መደንገጉን ይናገራሉ።

“እኛ የህጋዊ ሰውነት ስራ እንሰራለን፣ ነገር ግን የምርጫ ጉዳይ ላይ ለመሳተፍ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ፈቃድ የሚሰጥ ይሆናል”ያሉት ኀላፊው “ማህበራቱ በምርጫ መታዘብ፣ በመራጮች ትምህርት እንዲሁም በፖለቲካዊ ቅስቀሳ ላይ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል”ብለዋል።

በዚህ አላማ ለተመዘገበ ማህበር በአላማው መሰረት እንዲንቀሳቀስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ እና በዚህ አላማ ያልተመዘገቡት ግን ተሳትፎ ማድረግ ስለማይችሉ የቁጥጥር ስራውን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

በአዋጁ መሰረትም ማንኛውም የውጪ የሲቪል ማህበር በምርጫ ትምህርት፣ መታዘብ እንዲሁም የፖለቲካ ቅስቀሳ ላይ መሳተፍ እንደማይችል እና በአገር ውስጥ ቢቋቋሙም በውጪ ዜጋ የተቋቋሙ ማህበራትም ተመሳሳይ ክልከላ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

የፀጥታ፣ የደህንነት እና የፍትህ ተቋማት
ባሳለፍነው አንድ አመት ውስጥ በየአካባቢው ሲከሰቱ በነበሩ ግጭቶች አማካኝነት የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በፀጥታ ኀይሉ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአማራ እንዲሁም በደቡብ ክልሎች በፀጥታ እና ደህንነት ምክር ቤቱ አማካኝነት በተቋቋሙ ኮማንድ ፖስቶች ስር ሆነው እንደነበር፣ የተወሰኑት ደግሞ አሁንም በዚሁ ኮማንድ ፖስት ስር እንደሚገኙ ይታወቀል።

በተጠቀሱት ክልሎች ውስጥ በግልፅ የትኞቹ አካባቢዎች በፌደራል የፀጥታ ኀይሎች ቁጥጥር ስር እንዳሉ፣ መቼ እንደገቡ እና የኮማንድ ፖስቱ እድሜ ሲጠናቀቅም ከመንግስት ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም ደቡብ ክልልን ጨምሮ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም በዚህ ኮማንድ ፖስት ስር ይገኛሉ።

በአለም ላይ ምርጫን ተከትሎ የሚነሱ ግጭቶችን ወደ ህግ ተርጓሚው መውሰድ የተለመደ ተግባር ነው። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ይህ የተለመደ ተግባር ባይሆንም መጪውን ምርጫ ተከትለው ለሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ ሆነው መዋቀር አለባቸው የሚል አስተያየት ተደጋግሞ ይሰማል። ምንም እንኳ የሕገ መንግስት ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ስልጣን ባይኖራቸውም ፍርድ ቤቶችን የማጠናከር ስራ በምርጫዉ የሚነሱ ክርክሮችን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት እንደሚያግዝ ከፓርቲዎች እንዲሁም ከምርጫ ቦርድም ተደጋግሞ ተነስቷል።

የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ማቋቋሚያ አዋጅ እና የዳኞች የስነ-ምግባር ደንቦችን ለማሻሻል ጥረቶች የተጀመሩ ሲሆን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ለመጀመሪያ ጊዜ በጀቱን ለፓርላማ በማቅረብ ከህግ አስፈጻሚው ጫና ነፃ ያወጣኛል ያለውን ስራ ጀምሯል። የአዳዲስ ዳኞች ሹመትም በተያዘው አመት የተሰጠ ሲሆን፣ ሙሉ የለውጥ ስራ ለማከናወን የተለያዩ ጥናቶችን እያካሄደ እንዳለ ገልጿል።

አዳዲስ የክልልነት ጥያቄዎች እና የኢሕአዴግ ውህደት
በሲዳማ ዞን ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያየዘ ለአንድ አመት የቆዩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተደረጉ ሲሆን የክልሉ ምክር ቤትም ጥያቄውን መቀበሉን ተከትሎ ለምርጫ ቦርድ የህዝበ ውሳኔ ጥያቄ አቅርቧል። ቦርዱም በጉዳዩ ላይ የደቡብ ክልል ገዢ የሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ስብሰባ በተጠናቀቀበት ማግስት ባወጣው መግለጫ እስከ ሕዳር 2012 ባለው ጊዜ ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ዝግጅት እንደሚያደርግም አስታውቋል።

የህዝበ ውሳኔ ጥያቄዎችን ተከትሎም በዞኑ በነበሩ ግጭቶች የሰው ህይወት መጥፋቱ እንዲሁም ንብረት መውደሙን ከዞኑ አልፎ ክልሉም በኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆን ያደረገ ክስተት ሆኗል። በክልሉ ካሉ አስር ዞኖች የክልልነት ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ደኢሕዴንም ክልልነት ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚል ጥናት አዘጋጅቶ በውይይት ላይ ይገኛል።

በደቡብ ክልል እየተነሱ ያሉ ክልል የመሆን ጥቄዎች በምርጫው ላይ የራሳቸው ተፅእኖ እንዳላቸው የሚናገሩት በሪሁን የክልልነት ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ እና በስምምነት የሚፈጸም ከሆነ ተፅእኖው የጎላ ላይሆን ይችላል ይላሉ። ካልሆነ ግን የክልልነት ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ምርጫ ማካሄድ ከባድ ሊሆን እንደሚችል እና ይህም ባጠቃላይ አገራዊ ምርጫው ላይ ጉልህ ጫና ሊያሳድር ይችላል ሲሉ ያስረዳሉ።

ኢሕአዴግ አሁን ካለው ግንባርነት ወደ ውህደት ለመምጣት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ ካደረገ ወዲህ ውህደቱ ይሳካል አይሳካም ከሚለው በላይም በፌደራል ስርአቱ ቅርፅ ላይ ጫና ያሳድራል ይህም ለምርጫ ሂደቱ ሌላ የቤት ስራ ይዞ ይመጣል የሚሉም አስተያየቶች ተሰምተዋል።

አደም (ዶ/ር)፣ የኢሕአዴግ ውህደት ካለው ሁኔታ አንጻር በቀላሉ ይሳካል ብለው አያምኑም። ወደ ውህደቱም የሚሄድ ከሆነ በብሄር ፖለቲካውና በብሄር ፌደራሊዝሙ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። እንደ አደም ገለጻ፣ አንደኛ፣ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ የተገነባው ብሄርን መሰረት ባደረገ ፌደራሊዝም ነው። ለምሳሌ ክልሎች የተቋቋሙት በብሄር ነው፤ በአገር ደረጃ እንደ ፓርቲ ቢቋቋሙም በምርጫ ግን ክልላቸውን ወክለው ነው የሚወዳደሩት፤ ስለዚህ ሂደቱ ላይ መሰናክሎች መኖራቸው አይቀሬ ሊሆን ይችላል።

የፖለቲካ ተንታኝ እና መምህሩ አወልም በበኩላቸው ችግር የሚሆነው ከውህደቱ በኋላ በሚኖረው ቅርጽና ይዘት ላይ መሆኑን ያስረዳሉ። ኢሕአዴግ ሌላ ፓርቲ ሆኖ ሲመጣ፣ ይዞት የሚመጣው ፓርቲ ምን ዓይነት ቅርጽ ይዞ ይመጣል የሚለው ትልቁ ጥያቄ መሆን እንዳለበት የሚያስረዱት የህግ መምህሩ፣ በክልሎች ላይ ሲወከሉ በምን መልኩ ነው የሚለው ትልቅ መልስ የሚፈልግ መሆኑን በማስረዳት፣ ውህደቱ በቀላሉ ሊሳካ ይችላል ብሎ ማሰብ እንደሚከብድ ያወሳሉ።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህን ዉህደት የሚረዱበት እና የፖለቲካ ስራቸዉን የሚሰሩበት መንገድ በፈደራል ስርአቱም ሆነ በፖለቲካ ስርአቱ ላይ ትልቅ ተፅእኖ እንደሚኖረው አስተያየታቸውን የሚሰጡት ደግሞ በሪሁን። የበሪሁንን ሃሳብ የሚጋሩት አደም የኢሕአዴግ ውህደት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ዙሩን የሚያከር የተለመደውን የፓርቲ መዋቅር ባህል የሚቀይር ነው ይላሉ። ነገር ግን መሰረታዊ የሆነው በብሄር ላይ የተመሰረተውን የፖለቲካ እና ፌደራሊዝም አወቃቀር ግን የሚለውጥ አይሆነም ያሉት አደም ይህንን ሲያብራሩም ክልሎች ተወቀሩበት የብሄር መሰረት መሆኑን አንስተው ሕገ መንግስቱን የሚነካ ውህደት እንደማይሆን ያስረዳሉ።

ማጠቃለያ
መጪው ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ሁሉንም ያግባባ ነው። ምርጫው በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚፈለገውን ሚና እንዲጫወት ከታሰበ በፌደራል ስርዓት ላይ ያተኮረው ለውጥ ወደ ክልሎች መውረድ አለበት የሚሉ ምሁራን አሉ። ነገር ግን አብዛኞቹ ፓርቲዎች ምርጫውንም ለማሳካት እንደዚሁም የተጀመረውን ለውጥ የሚያደናቅፉ ችግሮች ክልሎች ላይ ነው ያለት ሲሉ ይደመጣሉ። በክልል ያሉት ፓርቲዎች አቋማቸው የጠራ አለመሆኑንና አብዛኞቹም ተመሳሳይ አቋም ያላቸው በመሆኑ በመጪው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ፉክክሩ ላይ ጫና ሊኖረው ይችላል ይላሉ።

የምርጫው መካሄድ ያለመካሄድ እጣ ፈንታም በወቅቱ ካልተነገረ በተለይ በህዝቡ ስነልቦና ላይ ጫና ይኖረዋል የሚሉት አደም ይህንን ለመግለፅ ትክክለኛው ወቅት “ትናንት ነበር”ይላሉ።

በአደም ሃሳብ የማይስማሙት ሶሊያና “በአሁኑ ምርጫ ያለውን ውዝግብ ብረዳም እስከዛሬም የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የሚነገረው መስከረም ወይም ጥቅምት አካባቢ ነው፣ እኛም ያንን ጠብቀን ውሳኔያችንን እናሳውቃለን”ብለዋል።

ምርጫውን ተከትለው የሚነሱ ውዝግቦችን በተመለከተም መተማመን አብሮ ከመስራት የሚመነጭ ነው የሚሉት አደም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከገዠው ፓርቲ አብረው በዚህ የሽግግር ወቅት ላይ መስራት ከምርጫው በኋላ ለሚነሱ ግጭቶች መፍትሄ ያመጣል ይላሉ።

ይህንን አብሮ መስራትም የምርጫውን የውክልና ስርአት በማሻሻል ከ50 በመቶ በላይ ያመጣው ፓርቲ መንግስትን ጠቅልሎ ይውሰድ የሚለው ተቀይሮ የተመጣጣኝ ውክልና ስርዓት መዘርጋት አለበት ይላሉ። ይህም አብላጫ ድምጽ ያላገኙ ፓርቲዎች በተወካዮች ምክር ቤት የተወሰነ መቀመጫ የሚያገኙበትን ዕድል የሚሰጥ እና በሚቀጥለው ምርጫ ተወዳድረን እስክናሸንፍ በመንግስት ውስጥ ድምጽ ይኖረናል የሚለው ዕሳቤ ከተስፋ መቁረጥ የሚመነጩ ግጭቶችን ይቀንሳሉ ይላሉ።

“እስካሁን የልሂቃኑን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፍላጎት እንጂ የህዝቡን ፍላጎት አልሰማንም፣ ለዚህም መገናኛ ብዙሃን የማይተካ ሚና አላቸው”ሲሉ አደም ይናገራሉ።
እንደ አደም ማጠቃለያ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም ማህበራዊ ችግሮች ዛሬ አንዱን ልፍታ የቀረውን ነገ ስላማይባል ጎን ለጎን ያሉትን ችግሮች መልክ ማስያዝ ያሰፈልጋል።

“ምርጫ አዲስ መንግስት ማምጣት ሳይሆን አዲስ ፖሊሲ ማምጣት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፣ ይህም ሁሉም በጋራ የሚያመጣው ለውጥ ነው”ሲሉ ይደመድማሉ።
አወል በበኩላቸው፣ የኢሕአዴግ ውህደት ምርጫውን በማሸነፉና ባለማሸነፉ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ በመኖሩ፣ በስሜታዊነት ከመወሰን ይልቅ፣ በሰከነ መንፈስ መታየት እንዳለበት ይመክራሉ። ምርጫውንም አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ ምርጫውን በማራዘም የሚመጣ አዲስ ነገር ባለመኖሩ፣ በተቆረጠለት ጊዜ ምርጫው እንዲካሄድ አድርጎ፣ ሃገሪቱ የተረጋጋ ስርዓተ መንግስት እንዲኖራት አበክሮ መስራቱ የተሻለ መሆኑን ያመላክታሉ።

ምርጫውን ማድረግም ሆነ አለማድረግ የየራሱ ውጤት ይኖረዋል የሚሉት በሪሁን ምርጫው አይደረግ ከተባለ ደግሞ መንግስት በምን አግባብ ነው የአምስት አመቱ የስልጣን ዘመን ካለፈ በኋላ አገርን የሚያስተዳደረው የሚለው መታሰብ አለበት ይላሉ፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ አሁን አያደረገ ካለው ነገር ምን የተለየ ነገር ማድረግ ይችላል የሚለው በጊዜ ተገድቦ መመለስ አለበት።

“መጪው ምርጫ በሰላማዊ እና በዴሞክራሲያዊ መልኩ ከተደረገ አገሪቱም ሆነ ህዝቦቿ ቃል ኪዳናቸውን የሚያድሱብት፥ የጋራ ራዕይ እና ህልማችውን የሚያስቀምጡበት፥ አገሪቱ አሁን ከገባችበት የፓለቲካ ቅርቃር በዘላቂነት የምትወጣበትን እድል ይፈጥራል”ሲሉ ያጠቃልላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here