የሸኔ ታጣቂ ቡድን ከፍተኛ አመራሮች በሽብር ወንጀል ተከሰሱ

0
972

የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት አመራር የነበሩት እና ከሠራዊቱ ኮብልለው በኤርትራ የኦነግ ሠራዊትን ተቀላቅለው በምህረት ወደ አገር ውስጥ የገቡት ኮለኔል ገመቹ አያናን ጨምሮ ሌሎች 20 ግለሰቦች ከሰኔ 2010 ጀምሮ በግዳጅ ላይ የነበሩ 40 የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትን እና 35 የክልሉን ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ሕይወት እንዲጠፋ ማድረግን ጨምሮ በተለያዩ የሽብር ወንጀሎች ተጠርጥረው ክስ ተመሰረተባቸው።

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት እነ ኪሲ ቂጡማ በሚል በተከፈተው መዝገብ እገታ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እና የፋይናንስ ተቋማትን መዝረፍ፣ ኢ-ሰብኣዊ ድርጊቶችን በመፈፀም እና ትዕዛዝ በመስጠት ተጠርጥረው በቀረቡት ግለሰቦች ላይ 38 የሰው፣ 26 የሰነድ እንዲሁም የፎቶ ማስረጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ማስረጃዎች ተያይዘው ቀርበዋል።

በተለይም ኹለተኛ ተከሳሽ ኮረኔል ገመቹ በጥቅምት ወር በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ ሀሩ ቀበሌ በሚገኘው የሸኔ ታጠቂዎች ወታደራዊ ቤዝ በግምት ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ የአካባቢውን ወጣቶች ወደ ካምፑ አምጥተዋል ያለው ዐቃቤ ሕግ ካልተያዘው አባሪያቸው ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) ጋር በመሆን “እኔ የሸኔ ታጣቂ አመራር ነኝ አይዟችሁ በርቱ” በማለት አመራር ሰጥቷል ሲል ዐቃቤ ሕግ ክሱን አብራርቷል።

በተመሳሳይም ቡድኑ በታኅሣሥ 2011 ባደረሰው ጥቃት ኹለት የፊንጫ ስኳር ፋብሪካን በመጠበቅ ላይ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከተገደሉ እና ሌሎች ኹለት ከቆሰሉ በኋላ ለኹለተኛ ተከሳሽ ኮለኔል ገመቹ የስልክ መልዕክት እንደደረሳቸው እና እሳቸውም “እርምጃው ተገቢ ነው፣ በሽምግልና የሚገኝ ነፃነት የለም” በማለት ገለፀዋልም ተብሏል።

ሰባተኛ ተከሳሽ የሆኑት የመንግሥት ሠራተኛም በሃዋ ገላን ሆስፒታል አንቡላንስ የተለያዩ በኤግዚብትነት ላይ የነበሩ ትጥቆች በቡድኑ ተዘርፈው እንዲወሰዱ አመቻችተዋል በሚል ክስ ተመስረቶባቸዋል።

እንዲሁም 9ኛ ተከሳሽ የቡድኑ የከተማ ውስጥ እርምጃ ወሳጅ ቡድን (አባ ቶርቤ) አባል በመሆን በነቀምቴ ከተማ ካቢኔ አባላት ላይ ግድያ ለመፈፀም ግዳጅ በመውሰድ በታኅሣሥ 16/2011 ሕይወታቸው ያለፈውን የካቢኔ አባል የሆኑትን አብደና ደኑሽን ከአባሪዎቻቸው ጋር በመሆን በነቀምቴ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ገድለዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

በቡራዩ ከተማ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመሆን የተስማሙ አንድ ግለሰብን ከግብረ አበሮቻው ጋር በመሆን እርምጀ ለመውሰድ ወደ ምስክሩ መኖሪያ ቤት ሔደው ነበር የተባሉት 10ኛ ተከሳሽም፣ ከድሪባ (ጃል መሮ) ትዛዝ በመውሰድ ወደ ነቀምት ተመለስዋልም ብሏል፤ ዐቃቤ ሕግ። አክለውም 10ኛ ተከሳሽን ግዳጁ በመጋለጡ አንድ ሰው በቡራዩ እንዲቀመጥ በመስማማት 11ኛ ተከሳሽ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ላይ እርምጃ እንዲወስድ ተደርጓል ያለው ዐቃቤ ሕግ፣ ምስክሩም በጥይቱ ሳይመቱ መትረፋቸውንም ጠቅሷል።

የሸኔ አባል በመሆን የሽብር ድርጊት ለመፈፀም የሚውል አር ቢ ጂ ሰቭን የተባለ ተወንጫፊ የሮኬት ማቀጣጠያ ይዘው ተጓጉዘዋል የተባሉት ደግሞ 13ኛ ተከሳሽ ናቸው። በመጋቢት 16/ 2011 ከቀኑ በሰባት ሰዓት ተኩል ላይ በምዕራብ ሸዋ ዞን፣አምቦ ከተማ፣ ልዩ ቦታው ኬላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በመጥቀስ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ የፖለቲካ ዓላማን ለማራመድ በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እና የአገሪቱን መሰረታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ለማፍረስ የምህረት አዋጁን ወደ ኋላ ትተው በወንጀል ድርጊት ተሳትፈዋል ሲል የድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ክስ መስረቶባቸዋል።

ክሱ አክሎም “ግለሰቦቹ በሸኔ ታጣቂ ቡድን ውስጥ አባል በመሆን ነፃ ኦሮሚያን ለመገንባት በሚል አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን የክልሉን መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ ተንቀሳቅሰዋል፣ በክልሉ በሚገኙ ከተሞችም አባ ቶርቤ ተብሎ የሚጠራውን የከተማ እርምጃ ወሳጅ ቡድን አቋቁመዋልም” ሲልም ወንጀል ተፈፅሟል ያለበትን አግባብ አስረድቷል።

በአጠቃላይም 17 የሚሆኑት ተከሳሾች ሕይወታቸው ካለፈ እና ከቆሰሉ የፀጥታ እና የሲቪል ሠራተኞች ባሻገር በ10 ግለሰቦች እገታ እና ግምቱ ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ ለሚሆን ንብረት ውድመት እና ዘረፋ ተጠያቂ ናቸው በሚል በዋና ወንጀል አድራጊነት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ቀሪ ሦስት ግለሰቦችም የቡድኑን ሐሳብ እያወቁ ገንዘብ በማሰባሰብ እርዳታ ያደረጉ ናቸው፣ በቄለም ወለጋ ዞን በሐዋ ገላን ወረዳ ሥም በሚጠራው ሆስፒታል የሚገኝን አንቡላንስን ለታጣቂ ቡድኑ ዓላማ እንዲውል በማድረግ እና በተለያዩ መጓጓዣ ዘዴዎች ምግብ መድኀኒት እና ሌሎች ስንቆችን ሲያቀርቡ ነበር በሚል በአባሪነት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ ባነሱት የዋስትና ጥያቄ ላይ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ተቃውሞ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ኹለቱን ወገኖች ካከራከረ በኋላ በሽብር አዋጁ መሰረት የዋሰትና መብታቸውን በመከልከል በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳውቸውን እንዲከታተሉ ሲል ወስኗል። ተከሳሾቹም ጠበቃ ይዘው ለመቅረብ በጠየቁት መሰረት በመጨረሻው ቀጠሯቸው ነሐሴ 24/2011 ላይ ጠበቆች አቁመዋል።

ጠበቆቹም ክሱን አንብበው እና ተዘጋጅተው ለቀጣይ ቀጠሮ የክስ መቃወሚያቸውን ይዘው ለመቅረብ ባቀረቡት መሰረት ፍርድ ቤቱ ከእረፍት ሲመለስ ለጥቅምት 12/2012 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here