በመዲናዋ ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 26 ቦታዎች ተለይተው ሊሻሻሉ ነው

0
1594

በመዲናዋ ሰዎች በተደጋጋሚ ለትራፊክ አደጋና ግጭት ተጋላጭ የሆኑባቸው 26 ቦታዎች ተለይተው የማሻሻያ ሥራ ሊሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በትራፊክ አደጋ በሚፈጠር ችግር ለሞት፣ ለከባድ እና ለቀላል የአካል ጉዳት እየተዳረጉ እንደሚገኝ እና በሚፈጠር የተሽከርካሪ ግጭትም በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት እየወደመ ነው።

በተደጋጋሚ ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 26 ቦታዎች በቦሌ መድኃኒዓለም የመንገድ መገጣጠሚያ፣ ጨርቆስ የመንገድ መገጣጠሚያ፣ የናይጄሪያ ኤምባሲ የመንገድ የመገጣጠሚያ በዋናነት ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ በእነዚህ ቦታዎች ከኹለት ሳምንት በኋላ የማሻሻያ ሥራ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርሀኑ ኩማ ጠቁመዋል።

አክለውም ገርጂ መብራት ኃይል፣ እስራኤል ኤምባሲ፣ ሻላ ፓርክ፣ 22 ቶሞካ ኮፊ፣ ሲኤምሲ ሳፋሪ፣ ሰሜን መዘጋጃ፣ እንቁላል ፋብሪካ፣ አስኮ ብርጭቆ ፋብሪካ፣ አስኮ መናኽሪያ፣ ሰባተኛ፣ ልደታ ኮንዶሚኒየም፣ ናሽናል ሞተርስ፣ ሳሪስ አደይ አበባ፣ ቀራኒዮ አንድ እና ኹለት፣ ጎፋ መብራት ኃይል፣ 58 ማዞሪያ ተጠቃሽ ናቸው።

መገናኛ አደባባይ፣ ሜክሲኮ እና ሌሎች አካባቢ የሚገኙ የእግረኛ መሸጋገሪያዎችም ለአደጋው ተጋላጭ ሲሆኑ፣ አደጋውንም ለመቀነስ የማሻሻያ ሥራው እንደሚሠራ ተመላክቷል።
የማሻሻያ ሥራው በርካታ ጉዳዮችን የሚያካትት ሲሆን፣ የትራፊክ ፍሰቱን ከማሻሻል ባሻገር የእግረኞችን ደኅንነት የሚያረጋግጥ፣ ለአካል ጉዳተኞችም ምቹ ተደርጎ የሚሠራ ነው ተብሏል።

በተለዩት ቦታዎች ላይ አደባባዮችን የማስፋት እና የማጥበብ፣ የመንገድ መገጣጠሚያ ቦታዎች ላይ የትራፊክ መብራት የሌላቸው ላይ መትከል እና የተበላሹትን አገልግሎት እንዲሰጡ የጥገና ሥራ ማድረግ፣ እንዲሁም በሕዝብ መጫኛ እና ማውረጃ ቦታዎች ታፔላዎች ይተከላሉ ተብሏል።
በተጨማሪም፣ በተለዩት ቦታዎች ምቹ ያልሆኑ የእግረኛ መሸጋገሪያ የዜብራ መንገዶችን ማሻሻል እና ለአካል ጉዳተኞችም ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እንደሚከናወን ኃላፊው ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በከተማዋ የሚከሰቱ የትራፊክ ግጭት አደጋዎችን ለመቀነስ የሌሊት ዕይታን የሚጨምሩ አንፀባራቂዎችን እየተከለ መሆኑንም ተናግሯል።

በከተማዋ ከሚደርሱ አደጋዎች አብዛኞቹ በምሽት የሚደርሱ መሆናቸው ተመላክቷል። አደጋዎችን ለመቀነስ እየተተከሉ የሚገኙት አንፀባራቂዎቹ በከተማችን በተደጋጋሚ የትራፊክ ግጭት አደጋ በሚከሰትባቸው መንገዶች፣ መጋጠሚያዎች እና ኩርባዎች ላይ ሲሆን፣ ይህም በምሽት የአሽከርካሪዎችን ዕይታ በመጨመር አደጋን የሚቀንሱ ናቸው።

አንፀባራቂዎቹ እየተተከሉ የሚገኙት ከካርል አደባባይ እስከ ልደታ ፀበል ባለው መንገድ እና ከልደታ፣ ሜክሲኮ፣ ለገሃር እስከ ስቴዲዬም ባለው በቀላል ባቡር መንገድ ላይ ነው ተብሏል።
ኤጀንሲው በቀጣይ በሌሎች ቦታዎችም ጭምር በጥናት ላይ በመመስረት ሌሎች ማሻሻያዎችን ጨምሮ የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥ እንደሚሠራ ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በከተማዋ በየወቅቱ የሚደርሰውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመፍታት ሌሎች አማራጮችን በማመቻቸት እየሠራ መሆኑንም ጠቁማል።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here