መነሻ ገጽዜናአቦል ዜና14 ሚሊዮን ዩሮ በጀት የተያዘለት የቡና ልማት ፕሮጀክት ሊጀመር ነው

14 ሚሊዮን ዩሮ በጀት የተያዘለት የቡና ልማት ፕሮጀክት ሊጀመር ነው

የቡና ልማትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርታማነቱን ለማሳደግ 14 ሚሊዮን ዮሮ በጀት የተያዘለት “ኢዩ ካፌ” የተሰኘ ፕሮጀክት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው፣ የቡና ልማትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርታማነቱን ለማሳደግ የሚረዳ በአውሮፓ ኅብረት አማካኝነት 14 ሚሊዮን ዮሮ በጀት የተያዘለት “ኢዩ ካፌ” የተሰኘው ፕሮጀክት በሚቀጥለው ዓመት ይጀመራል።

ኘሮጀክቱን ለመጀመር ቅድሚያ መከናወን ያለባቸው የቅድመ ዝግጅት ሂደቶች አሁን ላይ እየተከናወኑ እንደሚገኙ እና በሚቀጥለው ዓመት ከመጀመሪያዎቹ ወራት ጀምሮ ግን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተመላክቷል።

ኘሮጀክቱ በኢትዮጵያ በሚገኙ አምስት ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ ክልል፣ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ክልል፣ በሲዳማ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ዋና ዋና የቡና አብቃይ በሆኑ 28 ወረዳዎች እንደሚተገበር ተነግሯል።

ኘሮጀክቱ ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ ዋናው ዓላማ በተጠቀሱት ጊዜያት ውስጥ በቡና ማልማት ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች በየጊዜው ሥልጠና በመስጠት ቴክኖሎጂን ተጠቅመው እንዲሠሩ በማድረግ እና የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች በመደገፍ ረገድ ይሠራል ተብሏል።

ከዚህ አኳያም የቡና ልማቱን በቴክኖሎጂ ከመደገፍ ባሻገር ምርታማነቱን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው አዲስ ማለዳ ከባለሥልጣኑ ሰምታለች። በባለሥልጣኑ ስር የሚገኙ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ሥልጠና እንደወሰዱ እና እነዚህ አካላትም በተጠቀሱት ክልሎች በተለያዩ አካባቢ ለሚገኙ ፍላጎት ላላቸው አርሶ አደሮች ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ሥልጠና መስጠት ጀምረዋል ነው የተባለው።

ሥልጠናው በየወቅቱ እንደሚሰጥ እና አርሶ አደሮቹ የቡና ልማትን በምን ዓይነት መንገድ ተጠቅመው ቢሠሩ የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚችሉ ለማሳየት የሚረዳ ነው ተብሏል።

እስከ አሁን ባለው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ እና አርሲ ዞን እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሚዛን አማን ከተማ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ሥልጠና የመስጠት ሂደቶች የተጀመሩ ሲሆን፣ በተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ ሥልጠናውን የማስቀጠል እና የማጎልበት ሥራዎች ቀጣይነት እንዳላቸው ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ ቀደም ብሎ ለማስጀመር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በኮቪዲ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ ቆይቷል ተብሏል። አሁን ላይ የኮቪዲ 19 ወረርሽኝ ለውጦች ማሳየቱን ተከትሎ ቡና የሚያለሙ አርሶ አደሮች ከሚያከናውኑት ሥራ ጎን ለጎን የከርሰ ምድር ውኃን ለማውጧት የሚያግዝ የቴክኖሎጂ መሣሪያን በመደገፍ እና የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት ዘርፉን ለማሳደግ ኘሮጀክቱ እንደሚረዳ ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ ከብራዚል እና ከሌሎች አገራት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስርዓትን በማምጣት ኢትዮጵያም መተግበር ከጀመረች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከቡና የውጭ ምንዛሬ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ይረዳል ነው የተባለው።

ኢትዮጵያ በቡና ምርት ከዓለም አገራት ከአንድ እስከ 10 ከሚገኙ አገራት ተርታ የምትገኝ ሲሆን፣ የውጪ ምንዛሬ ለማግኘትም ለውጪ ገበያ የምታቀርበው ቡና ትልቁን ድርሻ ይይዛል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች