ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛና ትግሪኛ የፌደራል የሥራ ቋንቋዎች ሊሆኑ ነው

0
749

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ የፌደራል ቋንቋዎችን ለመጨመር መታሰቡን እና ከእነዚህም መካከል አፋን ኦሮሞ አንዱ እንደሆነ ገለፁ። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮምኛ ቋንቋ ከሚጨመሩት ቋንቋዎች አንዱ እንደሚሆን ቢናገሩም ሌሎች ይጨመራሉ የተባሉት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የትኞች እንደሆኑ ከመግለፅ ተቆጥበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግርም ተከትሎ ጉዳዩ የተለያዩ አካላት መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ሰንብቷል። አነጋጋሪ ከሆኑት ነጥቦች መካከልም የሚጨመሩት ቋንቋዎች የትኞቹ ናቸው የሚለው አንዱ ነው። በተጨማሪም የፌደራል የሥራ ቋንቋን ለመጨመር ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም በሚል ጉዳይ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ተደምጠዋል።

እንደ አዲስ ማለዳ ምንጮች ከሆነ ከአፋን ኦሮሞ በተጨማሪ የፌደራሉ የሥራ ቋንቋ ለመሆን በዕጩነት ከሚቀርቡት ቋንቋዎች መካከል ሶማሊኛ እና ትግሪኛ ይገኙባቸዋል።

የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ አምስት ንዑስ ቁጥር አንድ እንደሚለው ማናቸውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በእኩልነት የመንግሥት እውቅና ይኖራቸዋል። በኹለተኛው ንዑስ ላይም አማርኛ የፌደራሉ የሥራ ቋንቋ እንደሚሆን ደንግጎ በሦስተኛው ንዑስ እንቀፅ ላይ የፌዴሬሽኑ አባላት የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ በሕግ እንዲወስኑ ሥልጣን ይሰጣል።

በእንግሊዝ አገር በኪል ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት እና ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ወቅታዊ እና ሞያዊ ትንታኔዎችን በመስጠት የሚታወቁት አወል ቃሲም (ዶ/ር) እንደሚሉት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረጉ ግዴታ ላይሆን ይችላል።

“የፌደራል የስራ ቋንቋዎችን ለማካተት የህገ መንግስት ማሻሻያ ማካሄድ አስገዳጅ የማይሆነው ከአማርኛ ውጪ ሌሎች ቋንቋዎች የፌደራሉ መንግስት የስራ ቋንቋ አይሆንም የሚል አረፍተ ነገር ቢኖረው ነበር” ሲሉ ያስረዳሉ። “ነገር ግን ቋንቋው እንዲካተት ለሚወሰንላቸው ተናጋሪዎች አስተማማኝነት ያለው ማረጋገጫ በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ ቢሻሻል መልካም ይሆናል።” ይላሉ።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሕብረ ብሔራዊ አገራት የቋንቋ ጉዳይ ፖለቲካዊ እና ባሕላዊ ጥያቄ በመሆኑ ምክንያት አንዲህ ያሉ ውሳኔዎች መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄ መልስ ተደርገው እንደሚወሰዱም ይናገራሉ። የቋንቋዎቹ መካተት ካለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር በመንግሥት ላይ ከፍተኛ የወጪ ጫና የሚፈጥር በመሆኑ በአጭር ጊዜ የሚሳካ አይመስለኝም ሲሉ ይናገራሉ።

“በእነዚህ አዳዲስ የፌደራል የሥራ ቋንቋዎች ሠራተኞችን መመልመል፣ ማሰልጠን እና ማሰማራት ራሱን የቻለ ጊዜ የሚፈጅ እና ወጪም ይኖረዋል” የሚሉት አወል “የፌደራል መንግሥቱን ፖሊሲዎች፣ ሕጎች ደንቦችና መመሪያዎች በሚጨመሩት ቋንቋዎች መተርጎም እና መተግበር ጊዜ መውሰዱ ስለማይቀር ውሳኔው ከተወሰነ በኋላ ለመተግበር ቀላል አይሆንም።”

የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 49 የፌደራሉ መንግሥት መቀመጫ አዲስ አበባ እንደሆነች ይደነግጋል። ከተማዋ ምንም እንኳን ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግሥቱ ቢሆንም የአዲስ አበባ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ሙሉ እንደሆነ የአንቀጹ ንዑሶች ያስረዳሉ። በተጨማሪም በ1994 የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አንቀጽ ስድስት የከተማዋ የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንደሚሆን ደንግጓል።

አወልም ይህ ውሳኔ ከሚያመጣቸው ዘርፈ ብዙ ለውጦች መካከልም አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር እና ድሬዳዋ መስተዳድር ላይም የሥራ ቋንቋ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ የሚወስደው ጊዜ እና ገንዘብ ቀላል አይሆንም ሲሉ ያስረዳሉ።

ታዲያ እነዚህን ቋንቋዎች በማካተት ሒደት ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮች መኖራቸውንም አወል ይናገራሉ። በተለይም በአንድ ቋንቋ እንኳን ባግባቡ እና በቅልጥፍና አገልግሎት መስጠት የተሳነው የፌደራል መንግሥት መዋቅር ላይ ተጨማሪ የቤት ሥራ የሚጨምር ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ይህም የቋንቋዎቹ መካተት የሚያመጣውን ተስፋ ከተጠበቀው በታች በሆነ ውጤት እንዳይሸፍነው ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ።

በአብዛኛው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ያለው ሠራተኛ ከብቃት ይልቅ በፖለቲካ አቋም እና በትውውቅ የገባ መሆኑ አሁን ለሚታየው ያልዘመነ ቢሮክራሲ ዳርጓል። በተለያዩ ቋንቋዎች የሚመለመሉት አዳዲስ ሰዎች በዚህ መልክ የሚመጡ ከሆነ አገልገሎቱን ከማሻሻል ይልቅ ይበልጥ ወደ ኋላ የሚጎትት ይሆናል ሲሉም ይሞግታሉ።

“ይህ ውሳኔ በተለይም የፖለቲካ ውሳኔ እንደመሆኑ በጥንቃቄ መተግበር አለበት” ይላሉ የሕግ ምሁሩ። “ማንም ቅን የሆነ ሰው ተጨማሪ የፌደራል የሥራ ቋንቋ በመካተቱ ደስተኛ ይሆናል ብዬ ባስብም መሰረታዊ የሆኑ የፖሊስ እና የሕግ ለውጦችን ማምጣቱ ስለማይቀር የተወሰነ ተቃውሞ ማስከተሉ የማይቀር ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።

አሁን ከሚካተቱት ቋንቋዎች ባሻገርም በፌደራል ቋንቋነት የመካተት ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ የሚሉት አወል ጥያቄዎችን በአግባቡ እና በውይይት የመመለስ ልምድ ከማዳበር ባሻገር የአገር ጥቅምንም ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎችን ማካተቱም በመሃል እና በጠረፍ የአገሪቱ ክፍሎች መካከል ያለውን ክፍተት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማስተካከልም ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓትን ከ1987 ጀምሮ መተግበር የጀመረች ቢሆንም ተፈጥሯዊ ሒደቱን ጠብቆ ስርዓቱ እንዳላደገ እና በዴሞክራሲያዊ መልኩ ተተግብሯል ብለው እንደማያስቡም ተናገረዋል። በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከዚህ ቀደም የክልል እና የፌደራል መንግሥታት ክርክሮችን ማድረጋቸው እሙን ቢሆንም ከክርክሩ በኋላ ግን ሁሉም አንድ እና ተመሳሳይ ውሳኔ ተቀብለው ይተገብራሉ ሲሉ ይናገራሉ።

አሁን የሚታየው በክልሎች እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል ያለው ክርክርም አንዳንድ ሰዎች ችግር አንደተፈጠረ አድርገው እንደሚያዩት፤ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ መሰረት ክልሎች የተሰጣቸውን ጠንካራ ሥልጣን መተግበር በመጀመራቸው ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።
አንዳንድ ከክልል የሚነሱ ጥያቄዎች ግን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ያልገቡ እና አንዳንዴም ሕገወጥ ሐሳቦች በመሆናቸው አሳሳቢ ቢሆንም ገና ባልተደላደለ የለውጥ ሒደት ውስጥ የሚጠበቅ እንደሆነ አወል ያስዳሉ። የፌደራል መንግሥቱ ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ለማሻሻል ያመጣውን ሐሳብም ክልሎች ያነሱት ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የቆየ የፖለቲካ ጥያቄ በመሆኑ የክልሎች አቅም ከመጠንከሩ ጋር ተያይዞ መነሳት የለበት ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ዝርዝረር መረጃ ለማግኘት ወደ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የፕሬስ ሴክሪታሪያት ኀላፊ ንጉሱ ጥላሁን በመደወል ተጨማሪ ማብራሪያ ብትጠይቅም ዝርዝር መረጃው እንደሌላቸው ገልጸዋል።

የካናዳው ኦታዋ ዩንቨርሲቲ እንዳጠናው ከሆነ በዓለም ላይ 55 አገሮች ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋ አላቸው። ከእነዚህ ውስጥ 45 አገሮች ኹለት፤ አምስት አገሮች ደግሞ ሦስት የሥራ ቋንቋ ሲኖራቸው፤ ሲንጋፖር ደግሞ አራት የሥራ ቋንቋዎች አሏት። በአፍሪካ ደግሞ 24 አገሮች ኹለትና ከዚያ በላይ የሥራ ቋንቋ ሲኖራቸው ከእነዚህ ውስጥ ሞሪሺየስ፣ ሩዋንዳና ሲሸልስ ሦስት የሥራ ቋንቋ ሲኖራቸው፤ ደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌ ደግሞ እያንዳንዳቸው 11 እና 16 የሥራ ቋንቋዎች አሏቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here