200 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት የቀጨኔ የወንዝ ኘሮጀክት ሊጀመር ነው

0
1846

በዲዛይን ማሻሻያ ሥራ ቆሞ የነበረው 200 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት የ‹አቡየ – ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት ኘሮጀክት› በተያዘው ወር እንደሚጀመር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እንዳሻው ከተማው (ኢ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በከተማዋ አቡየ – ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት ኘሮጀክት በ2014 በጀት ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቶ መሠረት የማንሳት እና አንዳንድ የቅድመ ግንባታ ሥራ ማከናወን ተችሎ ነበር ብለዋል።

ነገር ግን፣ መሻሻል ያለባቸው የዲዛይን ሥራዎች መኖራቸውን ተከትሎ ሥራውን ለማቆም እንደተገደዱ አስታውሰዋል። በኋላም ዲዛይኑ ተጠናቆ ሥራውን ሲያስቀጥሉ፣ የ2014 የክረምቱ ዝናብ ለኘሮጀክቱ ሥራ እንቅፋት ወይም መስተጓጐል ሊፈጥር በሚችልባቸው የወንዙ መስመሮች ለጊዜው ግንባታውን ማከናወን እንደማይቻል ምክትል ቢሮ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በአቡየ ወንዝ ዳርቻ እና በቀጨኔ ወንዝ ዳርቻ በሚገኙ ቦታዎች የሚሠራ የልማት ሥራ ሲሆን፣ በአጠቃላይ አቡየ ቀጨኔ ተብሎ በአንድ ፕሮጀክት የታቀፈ ነው ተብሏል።

ኘሮጀክቱ 1 ነጥብ 2 ኪሎሜትር ርዝመት እንዳለው እና ሥራው ‹ባንትዋሉ ተሰማ› በተሰኘ አገር በቀል ኮንትራክተር አማካኝነት እንደሚከናወን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለውም፣ ኘሮጀክቱ በቀጣይ ስምንት ወራት ማለትም እስከ የካቲት ወር 2015 ድረስ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ብለዋል።

ይህ ኘሮጀክት ሲጠናቀቅ፣ ፅዱ ወንዝ ከመፍጠር፣ አዲስ አበባ ከተማን እንደ ሥሟ ፅዱ እና ውብ ከማድረግ ባሻገር ለማንኛውም ማኅበረሰብም ሆነ ለመዲናዋ ነዋሪ ከሚኖረው ጥቅም ጎን ለጎን በጎርፍ አደጋ ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችንም የመከላከል እድል እንዳለው ተነግሯል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው በተጨማሪ፣ ሸገርን ማስዋብ በተሰኘው ኘሮጀክት ውስጥ በኹለተኛው ክፍል በቀጣይ ኹለት ወራት የሚጀመር የወንዝ ዳርቻ ማስዋብ ሥራ እንዳለም አያይዘው ተናግረዋል። ይህ የወንዝ ዳርቻ ማስዋብ ሥራ ከወዳጅነት አደባባይ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም የሚለማ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት ነው ተብሏል።

ኘሮጀክቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስር እንደሆነ እና በቻይና መንግሥት በተያዘ በጀት የሚከናወን ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ በክትትል እና በቁጥጥር ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል። አክለውም ምን ያህል በጀት እንደተያዘለት ተቋሙ ለጊዜው የሚያውቀው መረጃ አለመኖሩን አመልክተዋል።

ይህ የወንዝ ዳርቻ ማስዋብ ሥራ በሚከናወንባቸው ከወዳጅነት አደባባይ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም አካባቢ በርካታ የግለሰብ ቤቶች መኖራቸውን ተከትሎ፤ ነዋሪዎችን ወደ ሌሎች አካባቢ የማዘዋወር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ እና በሚቀጥሉት ኹለት ወራት ውስጥ የማዘዋወር ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የማስዋብ ሥራው እንደሚጀመር ተገልጿል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለውም፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚከናወኑ የልማት ኘሮጀክቶች በዋናነት የማኅበረሰቡ እንደመሆናቸው መጠን የከተማዋ ነዋሪዎች የልማት ሥራዎች ላይ እገዛ እና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በተጨማሪ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ተሠርተው የሚጠናቀቁ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችን በመንከባከብ እና በመጠበቅ ረገድ ኃላፊነታቸው እንዲወጡ አሳስበዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here