በፌዴራል መንግሥትና ክልሎች እንዲሁም በክልሎች መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ ማናቸውም ዓይነት አለመግባባት ወይም ግጭት በተቻለ መጠን በስምምነት ለመፍታት ጥረት መደረግ እንዳለበት ሕጉ ይመክራል።
ኹለት አካላት ጉዳያቸውን በውይይት ለመፍታት የተቻላቸውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው እና ይህን ለማድረግም በዚህ መዓቀፍ የተመሰረተ ሆነ ሌሎች የግንኙነት አደረጃጀቶች እና አሰራሮችንም መተግበር እንደሚገባም ይወሳል።
ነገር ግን፣ አለመግባባቶች እና ግጭቶችን በስምምነት መፍታት ካልተቻለ ይህ ዓይነት የመንግሥታት ግጭት የመዳኘት ሥልጣን ለተሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መቅረብ እንዳለበትም ሲነገር ይደመጣል።
ሕግን ተከትሎ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት መቅረፍ ባለመቻሉ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ለጉዳዩ መነሻ የሆኑ ችግሮችን ከመነሻቸው ተነስቶ ማስወገድ ባለመቻሉ የፀጥታ መቃወሶች በየወቅቱ ሲነሱ ይታያሉ።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀው እና ተገቢውን መፍትሔ ባለማግኘቱ ከጊዜ ጊዜ የሚያገረሸው መፍትሔ አልባው የአፋር እና የሱማሌ ክልል ግጭት ተጠቃሽ ነው።
ኹለቱ ክልሎች በመሬት ወሰን ምክንያት በየወቅቱ ግጭቶች ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ አለ። ሶማሌ እና አፋር ክልል አዋሳኝ ቀበሌዎች ከኹለት ሳምንት በፊት እንዲሁ ግጭቱ ማገርሸቱ ይታወቃል። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም ኹለቱ ክልሎች ከስምምነት መድረሳቸው ተወስቷል።
ገዳማይቱ፣ እንዱፎ እና ገርበኢሴ በተባሉ አዋሳኝ ቀበሌዎች ይከሰቱ በነበሩ ግጭቶች ሞት እና መፈናቀል ከማስከተል ባለፈ ኹለቱን ክልሎች የቃል እሰጣ አገባ ውስጥ ሲያስገባቸው ቆይቷል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ጅግጅጋ ተገኝተው ከሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ እና ሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ማጠቃለያም ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል የተባለ ስምምነት ላይ ተደርሷል ተብሏል።
በኹለቱ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የተደረገውን ውይይት እና የተደረሱ ስምምነቶችን በሚመለከት ለዶይቼ ቬለ በስልክ አስተያየታቸውን አስረድተው የነበረው የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን፣ በስምምነቱ ቀዳሚው የታጠቁ ኃይሎች ከግጭት አካባቢዎች እንዲወጡ እና የፌዴራል ፀጥታ ኃይሎች በእነዚህ በተለዩ ቦታዎች እንዲገቡ የሚለው መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ኢብራሂም ገለፃ ለረዥም ዓመታት በጋራ በኖረው ህብረተሰብ መካከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በየደረጃው ውይይቶች ይካሄዳሉ ነው የተባለው።
በተለያዩ ጊዜያት ሲከሰቱ በነበሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ላይ የጋራ አቋም መያዙን የጠቆሙት ኢብራሂም፣ ዘላቂ ሰላም በማስፈን በኩል ኹሉም የበኩሉን የሚወጣበት መግባባት ላይ መደረሱንም አስረድተዋል።
በሶማሌ ክልል መቀመጫ ጅግጅጋ በተካሄደው ውይይት የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለምን ጨምሮ የአፋር እና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገኘታቸው አይዘነጋም።
በሌላ በኩል፣ ከውይይቱ ቀደም ብሎ በሶማሌ ክልል ለተከሰተው ድርቅ የሚውል የአስር ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ለሶማሌ ክልል አስረክበዋል።
የአፋር እና የሱማሌ ክልል መንግሥት እና ርዕሰ መስተዳድሮች ችግሮቻቸውን በዘላቂነት ለመቅረፍ በየወቅቱ ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት ተገናኝተው የሚመክሩ ቢሆንም፣ እስካሁን ባሉት ውይይቶች ተግባሩ ግን መሬት ላይ አልወረደም።
አዲስ ማለዳ በኹለቱ ክልሎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለምን መቅረፍ አልተቻለም? በቀጣይስ ምን ሊታሰብበት ይገባል? የሚለውን እና ሌሎች ጥያቄዎችንም ጠይቃለች።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) አባል የሆኑት አሕመድ ሙሐመድ እንደሚሉት፣ በሱማሌ ክልል እና በአፋር ክልል በኩል በተደጋጋሚ ለሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች አንዱ ምክንያት በኹለቱ ክልል መንግሥት በኩል ያለው ትኩረት አናሳ መሆኑ ነው።
ይህ እንዳለ ሳለ ከኹለት በሳምንት በፊት እንዲሁ በኹለቱ ክልሎች በኩል መሬትን ምክንያት በማድረግ የተፈጠረው ችግር አስፈላጊ አልነበረም። የሱማሌ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ከአልሸባብ ኃይሎች ጋር ፍልሚያ ላይ ባሉበት ወቅት የአፋር አስተዳደር እና ልዩ ሃይል የሱማሌ ሕዝብ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል ብለዋል።
በዚህም ምክንያት 200 የሚሆኑ ሕፃናት፣ አባወራ እና ሌሎች ሰዎችም እንደተገደሉ እና በደረሰው አደጋ ፓርቲያቸው ማዘኑን ገልጸዋል።
አክለውም፣ በተደጋጋሚ ለሚያገረሹ እና ለሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት አለመቀረፍ ደግሞ የኹለቱ ክልል መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ አሳብ እንደሌላቸው ያሳያል ብለዋል።
የሱማሌ እና የአፋር ሕዝቦች የተዋለዱ ከመሆናቸው ባሻገር በባህል፣ በቋንቋ ከ50 በመቶ በላይ ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆናቸው እና የአኗኗር ሁኔታቸውም ጭምር ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆናቸው በየወቅቱ ግጭት ውስጥ መግባት የለባቸውም ብለዋል።
አባሉ አክለውም፣ የኹለቱ ክልል ሕዝቦች በቀጣይ የተረጋገጠ ሰላም እንዲያገኙ እና ችግሩ በዘላቂነት እንዲቀረፍ ከታሰበ የሐይማኖት አባቶች፣ የሕዝብ ለሕዝብ ተሰሚነት ያላቸው የባህል መሪዎች፣ ምሁራን ተሰባስበው ችግሩን መፍታት እና የመጨረሻ መፍትሄ እንዲገኝላት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የአፋር ሕዝብ ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ሙሐመድ ዳውድ በበኩላቸው፣ በአፋር እና በሱማሌ ክልል በኩል በመሬት ወይም በድንበር ግጭት ውስጥ ገብተዋል በሚል የሚነሳው የተሳሳተ ነው ይላሉ።
የአፋር ክልል፣ ከአማራ ክልል፣ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከትግራይ ክልል እና ከጅቡቲ ጋር የሚዋሰን ነው።
ሊቀመንበሩ አክለውም፣ የአፋር ክልል የሆነን መሬት የሱማሌ ክልል የማያዋስነውን እንደሚዋሰን በመግለጽ እና የነሱ ግዛት እንደሆነ በማንሳት በየወቅቱ ለመውረር በማሰብ የክልሉ ዜጎች እና የፀጥታ አካላትን ጨምሮ በአፋር ሕዝብ ላይ ጥቃት ለመፈፀም ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
ከዚህ አንፃር የአፋር ልዩ ኃይል እና ዜጎች ራሳቸውን፣ ግዛታቸውን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ልዩ ሃይል በቅርቡም ከሱማሌ ክልል በኩል የፀጥታ ችግር ለመፍጠር እንቅስቃሴ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ የተፈጠረውን ችግር መቆጣጠር መቻሉ ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈ የሱማሌ ክልል ሕዝቦች ላይ በአፋር ክልል መንግሥት እና ሕዝብ በኩል ምንም ዓይነት ጥቃትም ሆነ ግድያ አልተፈፀመም ባይ ናቸው።
በአፋር እና በሱማሌ ክልል በኩል በተደጋጋሚ ለሚፈጠሩ የፀጥታ መደፍረስ የኹለቱ ክልል መንግሥት በሰፊው ተነጋግረው ጉዳዩን በዘላቂነት መቅረፍ አለመቻላቸው ለችግሩ ማገርሸት ተጠቃሽ ነው ይላሉ።
ሊቀመንበሩ አክለውም፣ በየወቅቱ ትንኮሳ ለመፍጠር ከመሞከር በመውጣት የኹለቱ ክልል መንግሥት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተወያይተው ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዘየደ ገብረፃዲቅ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፣ በአፋር እና በሱማሌ ክልል መካከል ግጭቶች የሚፈጠሩበት ሁኔታ እንዳለ ታዝበናል ብለዋል።
ጉባኤው በኹለቱ ክልሎች መካከል ከዚህ በፊት በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በኹለቱም ወገን በኩል ሕፃናት፣ አዛውንቶች እና ሌሎች ሰዎችም ላይ ጉዳቶች ደርሰው እንደነበር አስረድተዋል።
መንግሥት እነዚህን በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲቀርፍ እና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያስቀምጥ ጉባዔው ማሳወቁንም ጠቅሰዋል።
ነገር ግን፣ ትልቁ ሥራ እና የሰላም አቅጣጫ ማስቀመጥ የመንግሥት ቢሆንም፣ አሁንም ችግሮች የሚፈጠሩበት ሁኔታ እንዳለ ታዝበናል ያሉ ሲሆን፣ ችግሩን መንግሥት እንዲፈታ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በቅርቡም በአፋር እና በሱማሌ ክልል በኩል የተፈጠሩ ግጭቶችን በመረጃ ተደግፎ አጣርቶ በቀጣይ ሪፖርቱን ለህብረተሰቡ፣ ለመንግሥት እና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንደሚያሳውቅ ጠቁመዋል።
በአፋር እና በሱማሌ ክልሎች ድንበር አካባቢ ያለው ግጭት የቆየ ሲሆን፣ ከኹለት ዓመት በፊት ጀምሮ ብዙ ሰው የሞተበት የድንበር ግጭት እንደሆነም እሙን ነው። ከዚህ ቀደምም በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች መካከል ንግግር እየተደረገ እንደሆነ ቢነገርም፣ ተተግብሮ ግን እየተመለከትን ነው ለማለት እንደማያስደፍር ሲያነሱ የሚደመጡ አሉ።
የኹለቱ ክልል ሕዝቦች ተመሳሳይ ባህል እንዳላቸው እንዲሁም በጋብቻም ተሳስረው እንደሚኖሩ የሚነገር ሲሆን፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል በልቶ ጠጥቶ ያላደረ ሕዝብ ማጫረስ ተገቢ እንዳልሆነም የሚናገሩ አልጠፉም።
በአፋር እና በሱማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታ ላይ በሚገኙ አደይቱ እና ገርበኢሴ በተባሉት ኹለት የድንበር አካባቢዎች በሚፈጠሩ አለመግባባት ምክንያት የሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ችግሩ በኹለቱ ክልሎች መካከል ከፍተኛ ውዝግብ አስከትሎ እንደነበር የሚታወስ ነው።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ በተጋጋሚ የሰራች ሲሆን፣ በቅርቡም የአፋር እና በሱማሌ ክልል በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች አሉ። ስለጉዳዩ ለማጣራት ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ያደረገችው ጥረት ግን ምላሽ አላገኘም።
ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014



