የሰው ልጆች በሕይወታቸው ጉዞ የሚገጥሟቸውን መሰናክሎች አልፈው ሩቅ ለመጓዝ አርቆ አሳቢ መሆን ይጠበቅባቸዋል። የሕይወት ውጣውረድ በሚገጥማቸው ወቅትም ሆነ በአስተዳደግ ዘመናቸው የሚወስኗቸው ቀላል የሚመስሉም ቢሆኑ ቀጣይ ሕይወታቸው ላይ ተፅእኖ ማሳደራቸው እንደማይቀር ይታመናል። ግለሰቦች በተለያየ እድሜ ክልል ውስጥ ሲሆኑ የሚገጥማቸውን ችግርም ሆነ መልካም አጋጣሚ በጊዜው ካልተጠቀሙ መልሰው እንደማያገኙትም ሲነገር ይሰማል።ይህን ጉዳይ ከጊዜና ውሣኔ አንፃር እንዲሁም ከአረዳዳችን አኳያ ተንትነው የዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ በድሉ አበበ እንዲህ አቅርበውታል።
ለሥራ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ወደ ሐዋሳ ከኹለት የሥራ ባልደረቦቼ ጋራ እየተጓዝኩ ነው። በመሥሪያ ቤት ፒካፕ መኪና። ብዙ ነገሮችን ስናወጣና ስናወርድ ስለነበር ብዙም የተጓዝን ሳይመስለን በአዲሱ የሞጆ ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ከአዲስ አበባ 12፡00 ሰዓት ተነስተን 2፡30 ላይ ዝዋይ ራይት ካፌ ቁርስ በላን። ጥሩ ቁርስና ዕረፍት ከወሰድን በኋላ በአሮጌው መንገድ ወደ መጥፎ ትዝታችን ሻሸመኔ ከተማ እያመራን ሳለ ከፊት ለፊታችን አንድ አይሱዙ መኪና በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራ ባሸበረቀ ቸርኬው ላይ ‹ሳይገባሽ ይረፍዳል› የሚል ጽሑፍ ለኋለኞቹ ያስተላልፋል። አለመገረም አልቻልኩም። ለባልደረቦቼ ነገርኳቸው። ብዙ አወራን። ይሄው ላጋራቹ። ከብዙ በጥቂቱ።
በነገራችን ላይ ከአንድ ቀን በኋላ ሻሸመኔ አንድ ሆቴል ውስጥ፤ ከኔ በፊት እጁን ለመታጠብ የቆመ ግዙፍ ስፖርተኛ ወጣት ተራ ማስቀደሙ ሳያንስ የእጅ ውሃ ቀድቶልኛል። ይቀልዳል እንዴ ብዬም ተጠራጥሬዋለሁ። በመልሱ ላስታጥብህ ስለውም አሻፈረኝ ሲለኝ ‹እንዲህ እንኳ ሥማችሁን አድሱ እንጂ› ብዬ አመስግኜዋለሁ። ምንም አልመለሰልኝም፤ ዝም ብሎኝ ነው የሄደው። እኔን ለሌላ ሐሳብ ሰጥቶ።
እኔም እንደዚህ ያለኝ ይመስለኛል። የዚህ ሹፌር አንኳር መልዕክት አንዱ ጊዜ ነው። ጊዜ ወርቃማ ሀብት ነው። ጊዜ የሚሰጠው አንዴ ነው። ጊዜ አይታደስም፤ መልሶ አይገኝም። ጊዜን ማቆምም አይቻልም። እርስዎ አሁን ይሄን እኔ የጻፍኩትን እያነበቡ ያሉት ጊዜ ስላገኘን ነው።
የመጀመሪያዎቹ ! ሰው ብዙ ዓይነት ነው መቼም። ሰው የጊዜ እስረኛ ነው። ስለዚህ በጊዜው ይወለዳል። በጊዜና ዘመናት መካከል ይኖራል። በጎ ወይም መጥፎ ሥራ ይሠራል፤ ያለማል ወይም ያጠፋል። ሥሙን አጥቶ ይጠፋል አልያም ስሙ ዘመናትን ተሻግሮ በትውልድ ቅብብሎሽና በልጅ ልጅ እንዲጠራ ያደርጋል፤ ለራሱ ለቤተሰቡና ለአካባቢው አልፎም ለአገሩ ሲጠቅም ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ‹ዘመንን ዋጀ› ይባላል።
ዘመንን የዋጀ በዘመናት ፈተናዎችና መከራዎች ውስጥ ተዘፍቆ ራሱም ወድቆ ሌላውን አይጥልም፤ ያነሳል እንጂ። ብርታት እንጂ መሰናክል፤ መፍትሄ እንጂ ችግር አይሆንም። በማወቅም ባለማወቅም፤ በስሜትም በስሌትም ስህተት ውስጥ ቢገባ እንኳን ራሱን ለማረቅና ወደ መልካሙ ለመመለስ ችግር የለበትም።
የሰው ልጅ ስህተት የሚሠራ ፍጡር ስለሆነ ስለትናንትና ስህተቶችና ድካሞች ብቻ እያላዘነና እያለቀሰ አይኖርም፤ ስህተቱን አርሞ ለወደፊቱ ይነሳል እንጂ። መልካምና በጎ ነገር ለመሥራት እንደማይረፍድበት ሁሉ፤ ስህተት ሲሠራም ለማረምና ይቅርታ ለመጠየቅ አያመነታም። ይሄን ዓይነቱን ሰው ይመስለኛል ባለአይሱዚው ‹የገባው አይረፍድበትም› ያለው በሌላ ቋንቋ።
እንዲህ ዓይነቱ ሰው በኔ ዕይታ፤ በ‹የገባው ልክ›ና በ ‹አለመርፈድ› መስፈርት ካየነውና ከለካነው የመጀመርያን ደረጃ ልንሰጠው እንችላለን። ይሄ ሰው ደስተኛና ጸጸት የሌለበት ኑሮ ይኖራል። ምክንያቱም እውነት በሆነውና በገባው ልክ ገብቶት፤ የተሰጠውንም ጊዜ በአግባቡ ተጠቅሞ በወቅቱ መድረስ ከሚገባው ቦታና የሕይወት ደርጃ ደርሷልና። ወደ ኋላ የሚያይበት፤ ሰውን ለመጉዳት የሚያሴርበት ጊዜ የለውም። የራሱን ወርቃማ ጊዜ በወርቃማ መልኩ እየተጠቀመ ነውና።
ለምሳሌ፣ ወቅቱ የእርሻ ወቅት ሆኖ ዝናብም ዘንቦ ግንቦትና ሰኔ ያረሰ ገበሬ መስከረምና ጥቅምት ሰብል ለመሰብሰብ ቢወጣ ያምርበታል። እሱም መቼ መዝራትና መቼ መሰብሰብ እንዳለበት አውቋልና። ሁኔታውና ነገሩ ገብቶታል፤ ወቅቱንም ዋጅቷልና። እነዚህ የራሳቸውንም የማኅበረሰባቸውም፤ የአገራቸውም የዓለምና የብዙ ሕዝቦች መድኅን ብቻ ሳይሆኑ የቀጣዩ ትውልድ ተስፋም ናቸው። ለምሳሌ፣ ማህተመ ጋንዲንና ማዘር ትሬዛን እዚህ ረድፍ ልንመድባቸው እንችላለን። እንዲህ በማለት ‹ዓለሙም ነገር ዓለሙም ገብቷቸዋል፤ በጊዜም አልረፈደባቸውም።› ብለን። ተፈትነው ያለፉ፤ በፈተና የነጠሩ ወርቆች ማብረቅረቅ ልማድ ነውና ያብረቀርቃሉ።
ምሳሌ እንጨምር! አስራዎቹ እድሜ ‹turning point› ነው ይላሉ ሳይንቲስቶቹ። ‹የመታጠፊያ ጊዜ› ነው እንደ ማለት። በዚህ እድሜ ነው ብዙ አሁን ያሉን መልካምና መጥፎ ባህርያትን የምንይዘውና የምናዳብረው። ምሳሌውን ስንለጥጠው ደግሞ፣ በዚህ ዕድሜ ነው የኹለተኛ ደረጃ ተማሪ የሚኮነውና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የሚወሰደው። ይህ ዕድሜ ከፍተኛውና ሁለተኛው ቀጥተኛ የሰው ልጅ ዕድገት የሚከሰትበት፤ ልምድ አልባ ፍቅርና ወሲብ ፍላጎት የሚንርበት፤ የጓደኛ ተጽዕኖ የሚበረታበትና ለቤተሰባዊና ኅብረተሰባዊ እሴቶች ያለው/ያላት ዕይታ የሚላላበት፤ ስሜታዊነትና ትኩስነት ከፍጥነት ጋራ የሚሰግሩበት ዕድሜ ነው።
ፈጣን ውሳኔና ድርጊትም ይከተሉታል ወዘተ። ታድያ ይሄንን ወቅት በአግባቡ በመልካም ሥነ ምግባር እንድናልፈው አባትና እናት፤ ታላቅ ታናሽ፤ ውንድምና እህት፤ ዘመድና ጎረቤት፤ የትምህርት ቤት መምህራንና በየሀይማኖቱ ወንድሞችና እህቶች አባቶችና እናቶች ይመክራሉ፤ ይዘክራሉ። ዕድገታችን ቀጥተኛ እንዲሆን በፍቅርም በቅጣትም ያስተምሩናል።
‹ይሄ ልጅኮ ጎረመሰ›፤ ‹ይቺ ልጅኮ አልታዘዝ አለች›፤ ‹ይሄ ልጅ ፍቅር ይዞታል መሰል ፈዟል›፤ ‹ይቺ ልጅ ደጅ ደጅ አብዝታለች›፤ ‹ያንን ጓደኛህን አልወደደኩትም›፤ ‹ከሱ ጋር ከገጠመ ወዲህ….›፤ ‹ብትሰማኝ ይሻላል፤ ኋላ እንዳይቆጭህ›፤ ‹ብትሰሚኝ ይሻላል፤ ኋላ እንዳይቆጭሽ›፤ ‹ይልቁንስ ብታጠና/ኚ ይሻልሃል›፤ ኋላ እንዳይቆጭህ/ሸ›፤‹ ጨዋታ አይበላ በኋላ› ወዘተ እንባላለን፤ እድሜው ከነፋስም የፈጠነ ሆኖ ምክርን በልብ ለመያዝ አያበቃም እንጂ።
ሥነ ምግባር ያላቸውንና በትምህርት ሞዴል የሆኑትን ተመልከቱ እንባላለን። ‹ምናለ እንደ እገሌ ልጅ ቁጭ ብለህ ብታጠና/ብታጠኚ› የሚል ቤተሰብ የሚበዛበትም ጊዜ ነው። ብዙ ሰሚዎች ያሉትን ያህል ጥቂት ጨዋታ የሚያጠቃው አይጠፋም። የዛን ጊዜ ምክር ቀንቷቸው የሰሙና የተገበሩት፤ ጥሩ ውጤት ያመጣሉ፤ ዩኒቨርሲቲም ይገባሉ። እዚህ ጋራ ሁሉም ወጣት የማይሳካለት በዚህ ብቻ ሳይሆን በብዙ ሌሎች ምክንያትም ሊሆን ይችላል። መፍረድ የኔ ድርሻ አይደለም፤ ተፈጥሮ ሌላ መልስ ስላላት። እነዚህ የወደፊት ሕይወታቸውን በዚህ ወቅት የሚያደላድሉት ግን ሳይረፍድባቸው በጊዜው ገብቷቸዋልና የልፋታቸውን በረከት በደስታ ያጭዳሉ።
ኹለተኞቹ ! እንደዚህ ዓይነቶቹ ደግሞ ገብቷቸው የረፈደባቸው ሰዎች ናቸው። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ከልጅነት እስከ እውቀት ከተፈጥሮ፤ ከራሳቸው፤ ከጓደኞቻቸው፤ ከጎረቤታቸው፤ ከሃይማኖታቸው፤ ከትምህርት ቤትና ከሚያዩት፤ ከሚሰሙት፤ ከሚያነቡት፤ ከሚነኩት ነገር ተረድተው ተንትነው ቀድሞ ገብቷቸዋል። ቀድሞ ስለገባቸው ደስ ቢለንም ግን እንዳይረፍድባቸው ብንመኝም አንድም ራሳቸው ሊቆጣጠሩትና ሊገቱት በሚችሉትና ባቃታቸው በራሳቸው ምክንያት፣ አልያም ከነሱ ውጭ በሆነና ሊቋቋሙትና ሊያሸንፉት በማይችሉት ምክንያት ይረፍድባቸዋል።
በኹለተኛው ማለትም ከነሱ ውጭ በሆነ ምክንያት ለረፈደባቸው አቅማቸውን በሙሉ አሟጠው ተጠቅመው ከሆነ አይፈረድባቸውም። ነገር ግን፣ አንድም በራሳቸው ከውስጥ ከስሜታቸው መታረቅና ራሳቸውንም በጊዜው ማረቅ አቅቷቸው፤ በጥቂት ትዕግስት ይታለፍ የነበረውን ቀላል ችግር እንደ ተራራ የማይገፋ ከሆነ በኋላ እንደገና መልሶ ለማሸነፍ ምንም ጥረት ያላደረጉ ናቸው።
እነዚህ ለመርፈዱ የራሳቸውም እጅ አለበት። የገጠማቸው ችግር ቀላል፤ መካከለኛ ወይም ትልቅ ሊሆን ይችላል። ችግሮቹንም ሊገምቱ፤ ሊያውቁ አልያም ላያውቁ ይችላሉ። ያወቁትን ቀላልና መካከለኛ ችግር ለማሸነፍ እስከ መጨረሻው መታገል ያስፈልጋል፤ ከባዱን ጨምሮ። አንዳንዴ ‹ጦር ሳይሰበቅ› የሚሸነፉ ሰዎች አሉ። ችግርን ማወቅ አንድ ነገር ሆኖ ችግሩን ምንነቱን፤ ምንጩንና መነሻውን ውጤቱንና የሚያስከትለውን የአጭርና የረጅም ጊዜ ተጽዕኖ ከግምት አስገብቶ በተለያየ ስልት መታገል ሲያስፈልግ በቀላሉ እጅ የሚሰጡ፣ ቢገባቸውም እንዲረፍድባቸው በተዘዋዋሪም ቢሆን ፈቅደዋል ማለት ነው። ስለዚህ ችግሩ ገብቶን በራሳችን ስንፈት ወይም እንዝላልነት ካልፈታነውም ገብቶናል ግን ረፍዶብናል ማለት ነው።
በአጠቃላይ አንድ ነገር ችግርም ይሁን ሌላ ስለገባን ብቻ ልንፈታውና ልናደላድለው ወይም ልናበለጽገው አንችልም ማለት ነው። ችግሩ የገባው አራት አማራጮች ይጠብቁታልና። አንድ ችግሩን እያወሩ መኖር፤ ኹለት ችግሩን ለጊዜውም ቢሆን መግታት፤ ሦስት ችግሩን እንዳይደገም እስከወዲያኛው በዘላቂነት መፍታት፤ አልያም ችግሩን አውቆ ነገር ግን በውስጥ አምቆ ምስጢር አድርጎ መዝለቅ።
ከአራቱ አማራጮች አንዱ ነው አንድን ነገር በሰዎች ሕይወት ውስጥ ዳግመኛ ተመልሶ እንዳይከሰትና እንዳይረብሽ የሚያደርግ፤ አንዱ ችግሩን እንደረመጥ ለነገ የሚያሳድር ነው፤ ሌላኛው ዛሬን ጠግቦ ለማደር ቢጠቅምም ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም። ሌላኛው ደባቂ በሌላ ሰው ላይ ወይም በራሱ ሕይወት ዳግም እስኪከሰት ይጠብቃል። ስለዚህ ሦስቱ ችግሩ ካልገባቸው እምብዛም አይሻሉም። ምክንያቱም አንዱ ባለመግለጽ፤ ኹለተኛው ችግሩን በችግርነቱ ከማውራት በቀር ምንም ዘዴ ባለመዘየድ፤ ሦስተኛው ጊዜያዊ መፍትሄ ብቻ በመስጠት ያ ችግር ሳይፈታ እንዲረፍድ ባንድም በሌላም መልኩ አስተዋጽዖ አድርገዋል። በመሆኑም ‹ችግሩ ገብቷቸዋል፤ ግን ረፍዶባቸዋል።› ማለት ነው።
ሦስተኞቹ! ሳይገባቸው ያልረፈደባቸው ናቸው። እነዚህ ከጊዜ ጋራ ስምሙ ናቸው። ጊዜና ሕልውና በመጠኑም ቢሆን ገብቷቸዋል። የሰው ልጅ ጊዜ ነው፤ ጊዜን በሚገባው ልክ ያልተጠቀመ ከሰው ልጅነት ይጎድላልና። እንዲያውም ጊዜ በጣም የገባቸው እየመሰላቸው አንዳንድ ጊዜ ከጊዜ መቅደም ይዳዳቸዋል።
እንዲህ ስል ሰው ጊዜን መቅደም አይችልም እያልኩ አይደለም። ሰው በተሰጠው እድሜ ከሚገባው በላይ የመጣለትን ዓላማ ሊያሳካ ይችላል፤ በተገቢው መንገድ። የተፈጠረለትን ዓላማ (Purpose of life) ሳይረፍድበት በአግባቡና በስርዓቱ ሊያሳካ ይችላል፤ እነሱ ገብቷቸው የፈጠኑ ናቸውና።
ጊዜ ገብቶት የፈጠነና የገባው ነው ከማለት የሚያግደን የለም። አሉ ደግሞ አንዳንዶች፤ ምንም ሳይገባቸው፤ ጉዳዩንም ሳያውቁት ጭረው የሚያበላሹ ወይም ደግሞ ሌሎች እንዲያበላሹ የሚያደርጉ፣ አልያም ሲበላሽ ሳይገባቸው ቀርቶ ከዳር ቆመው የሚያዩ። በማወቅም ባለማወቅም፤ አውቀውም ነቅተውም በሌላም በሌላም ምክንያት ሊሆን ይችላል አንድ መገለጫቸው ግን በቃ ጉዳዩም ነገር ዓለሙም አልገባቸውም፤ ሙሉ በሙሉ። ነገር ግን የገባቸው መስለው ለመታየት የማያደርጉት ነገር የለም። ሌላ መገለጫቸው የማያውቁትን፤ ከራሳቸው ያላነቁትን ምናልባትም የሌሎችን የቤት ሥራ እየሠሩ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ ለያዥም ለገናዥም ያስቸግራሉ። ለውይይትም ለንግግርም አይመቹም። ሳይገባቸው የገባቸው መስለው ይታያሉ። ሲገልጧቸው ግን ከነገሩ የሉበትም። ራሳቸውን ሹመዋልና በዚህ አይቀሩም።
እዚህ ጋራ እንዴት ምንም የማይገባው ሰው ይኖራል? ይሄ ከተፈጥሮ አይጋጭም ወይ? ቢባል፦ እውቀት ያልተሰጠው የሰው ልጅ የለም። ነገር ግን፣ በአንድም በሌላም መልኩ በዚያ ጉዳይ ወይም በሕይወታቸው አጠቃላይ ሁኔታውን ማየት የተሳናቸውን ማለታችን ነው። ስለዚህ በቅጡ ሳይገባቸው፤ ሳይረፍድባቸው አንድ ነገር ለማድርግ ይነሳሉ። መነሳታቸው ባልከፋ። ሳይገባው ሳይረፍድበትም፤ ኹለቱ ሰምሮለት የሚያደርግ ሦስት ውጤት ሊያስከትል ይችላል።
አንዱ ገበቶት ግራ ቀኙን ዐይቶ አመዛዝኖና ወስኖ ስለገባበት በምንም መልኩ ሳይሳካለት ሲቀር ሲሆን፤ ኹለተኛው ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ሲሳካለት ነው። ሦስተኛው ደግሞ ሙሉ በሙሉ ሲሳካለት ነው። ስኬት የመሰለ ነገር ቢኖርም ግን ዘላቂነት የለውም፤ በጊዜ ቅመም አልታሸምና። ምናልባትም እድሜና ልምድ ያነሱት ‹በአቋራጭ የተሳካለት› ይሆናል እንደማለት። አቋራጭ ደግሞ ያልረገጠው መንገድ ስላለ ስኬቱ ሙሉ ነው የሚለው ብዙም ላያስኬድ ይችላል።
ሳይገባቸው ስለፈጠኑ ራሳቸውንም፤ ሌላውንም፤ ባህላቸውንም ማተባቸውንም መርገጥ፤ በ‹በአቋራጩ› መንገዳቸው እስከ መሰዋት ሊደርሱ ይችላሉ። እነዚህ ሳይገባቸው ሳይረፍድባቸው አንድን ጉዳይ ለማሳካት ሁሉንም የሚያደርጉትን ይወክላል። እነዚህ በፍጥነታቸው ልክ ወይም እንዳይረፍድባቸው ካላቸው ጉጉት አንጻር ጉዳዩ እንዲገባቸው ጥቂት ቢጥሩ ነገሮች ይበልጥ ይደላደሉላቸዋል።
አራተኛዎቹ! ነገሩ ገብቷቸዋል። በጣም ገብቷቸዋል። ምን ያህል ካልን? እጅግ በጥቂቱ፤ በጥቂቱ፤ መካከለኛ ወይም በአብዛኛው ገብቷቸዋል ማለታችን ነው። ምንም ካልገባቸው በዚህ ይለያሉ። በእርግጥ ሙሉ በሙሉ ምንም የማይገባው ሰው አለ ማለት አይቻልም። መረዳታቸውን ለውሳኔያቸው ይጠቀማሉ። ምንም ቢሆን ጥቂት መረጃም ይሁን ማስረጃ ወይም መረዳት ስላላቸው በመረዳታቸውና በገባቸው ልክ ይወስናሉ፤ ያደርጋሉ። ሲያደርጉ ከጊዜ አንጻር ሦስት ነገር ይገጥማቸዋል። መቼ ነው መወሰን መቼ ነው ማድረግ ያለብኝ የሚል።
ስለዚህ፣ አንድም ከጊዜው ቀድመው ሊወስኑ ይችላሉ አልያም በጊዜው ወይም ጊዜው ካለፈ በኋላ ሊወስኑ ይችላሉ። ከጊዜ ቀድመው ወስነውም ኹለት ጉዳይ ያጋጥማቸዋል። በክፉው ስለቀደሙ ውግዘት በበጎው ደግሞ ቀድሞ የማድረግ ክብርን ሊያጭዱ፤ በዚያውም ሊታወቅላቸውም ላይታወቅላቸውም ይችላል። በጊዜው ካደረጉ ‹የገባቸው› ልንላቸው እንችላለን። ችግሩ ግን ሦስተኞቹ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ማለት ገብቷቸው ነገር ግን የረፈደባቸው ይሆናሉ። ጊዜው ላይመለስ ነጉዷል፤ እነሱ ግን ያለጊዜው ከረፈደ ለማድረግ ይተጋሉ።
የረፈደበት ያንን ለማካካስ ምን ሊያደርግ ይችላል? (ሀ) በዚህ ጊዜ ባደረኩት ኖሮ የሚል የልቦና ጸጸት (ለ) ከነ አካቴው መተው (ሐ) ከነ አካቴው መተውና ሌላ መንገድ መቀየስ (መ) በጊዜው ያላደረገውን እንደገና ለማድረግ በሚገባው መንገድ ማሳበር/ማቋረጥ (ሰ) በጊዜው ያላደረገውን እንደገና ለማድረግ በማይገባው መንገድ ማሳበር/ማቋረጥ በመጨረሻም የራሱን የቀደመ ማንነት ሊያጣ ይችላል፤ ወይም ሳይለወጥ በዚያው ሊዘልቅ ይችላል፤ ወይም የበለጠ ሊያድግበትም ይችላል።
የመጨረሻዎቹ ! ያልገባቸውና የረፈደባቸው ናቸው። ከላይ እንዳነበብነው እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ነገር ዓለሙ አልገባቸውም። ማለትም ምን፤ ለምንና እንዴት እየሆነ እንዳለ አልገባቸውም። ሙሉ በሙሉ አላዋቂ ናቸው ማለት አይደለም፤ ይሄ ሊሆን አይችልምና። በነገራችን ላይ በዚህ ዘመን ‹መሃይም› የሚባል የለም፤ ወይም ሰውን ‹መሃይም› ብሎ መሳደብም መጻፍም ትክክል አይደለም። ዘመናዊ ትምህርት አልተማረም ማለት ‹መሃይም› አያስብልምና። ምክንያቱ ደግሞ የሰው ልጅ ራሱን በማወቅ በልቦናው፤ ከአካባቢው፤ ከባህሉ ከእምነቱና ከተለያዩ ነገሮች የሚማር ፍጡር ነው።
ስለዚህ እባክዎ ከቃላት ባንክዎ ውስጥ ‹መሃይም› የሚለውን ቃል ከዛሬ በኋላ ይሰርዙ፤ የሰው ልጅ ‹መሃይም› አይባልማ!። በመሆኑም፣ ቀድመን እንደጀመርነው ያልገባቸው ስንል አንድ ጉዳይ ወይም ብዙ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ በአጭሩ ግን እዚህ የምንጠቅሳቸው ሰዎች አልገባቸውም። ባልገባቸው ነገር ላይ ደግሞ አስተያየት ይሰጣሉ። መስጠታቸው መብትም ክፋትም የለውም። ነገር ግን፣ ያልገባው ሰው የሚሰጠው አስተያየት አብዛኛው ትክክል ያለመሆን እድል አለው። ትክክል ካልሆነ ደግሞ የማሳሳት አቅም አለው ማለት ነው። ራስን ደፋር ሲያደርግ ሌላውን ደግሞ ባልሆነ አቅጣጫ በመምራት ያስታልና።
ትክክል ያልሆነ ነገር ትክክለኛ ውጤት ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። ያልገባው እንዳልገባው የማወቅም ያለማወቅም እድል አለው። እንዳልገባው አውቆ ለማወቅ ወይም እንዲገባው የሚጥር አለ፤ ይሄ የመስተካከል እድል አለው። ስለሆነም፣ ለመማር ተግቷልና በሂደት ወደ መረዳት ይደርሳል። እንዳልገባው ያላወቀና በድፍረቱ የጸና ደግሞ ይሳሳታል። የከፋው ችግር ደግሞ ያልገባውም የረፈደበትም ሲሆን ነው። ከዚህ ይሰውረን እንጂ ምን ይባላል!
ይሄን ጊዜ ሦስት ችግር ይገጥመናል። አንዱ አለማወቁ ሲሆን፤ ኹለተኛው አለማወቁን አውቆ ለመማርና ለማወቅ ጥረት አለማድረጉ ነው። ሦስተኛው ደግሞ ጭራሽ የረፈደበት ሲሆን ነው። ይሄ ከባድ ነው፤ ሳይገባን ረፍዷልና። በአጠቃላይ፣ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ለምሳሌ የተፈጥሮ አካል በማጣት፤ በበሸታ፤ በክፉ እድል፤ የመማር እድል በመነፈግ፤ ልምድ በማጣትና በልዩ ልዩ ምክንያቶች መጀመሪያ ላያውቅ በኋላም ላይገባውም ሊረፍድበትም ይችላል፤ ሙሉ በሙሉም ባይሆን። ባልገባው ሁኔታና ነገር ላይ ያልተገባ ሐሳብና ንግግር እንዲሁም ድርጊት ሊፈጽም ይችላል፤ ይሄ ነው እንግዲህ ጉዳቱ። ስለዚህ ሳይገባው የረፈደበት፤ ገብቶት የረፈደበት፤ የረፈደበትና ያልገባው ለጊዜውም ቢሆን መጎዳቱ አይቀርምና ‹ሳይገባሽ አይርፈድ› እህቴ!
የፅሁፉን አዘጋጅ በድሉ አበበን በ [email protected] ኢሜል አድራሻቸው ማግኘት ይችላሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014



