የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መስተጓጎል

0
1030

የኘሮጀክቶች አፈጻጸም መመሪያ በመንግሥት በኩል ራሱን ችሎ የተዘጋጀ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገራት እርዳታ እና ብድር በሚገኝ ገንዘብ የሚጀመሩ የመሠረተ ልማት ኘሮጀክቶች ሲስተጓጎሉ ይታያል።

የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሰፊ እቅድ እና ዝግጅት ሳይደረግባቸው ወደ ተግባር የሚገባባቸው ሂደቶች መኖራቸውን ተከትሎም በተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ የማይጠናቀቁበት እድልም እንዳለ የሚያወሱ አልጠፉም።

ለዚህ ደግሞ ኘሮጀክቶች ከመጀመራቸው አስቀድሞ በጥናት ላይ የተደገፈ ጊዜ እና በጀት መመደብ አለመቻል እንዲሁም ለግንባታ ሂደቶች ማስቀጠያ እና ለተለያዩ የግንባታ ቁሳቁሶች የሚውል ገንዘብ በወቅቱ አለመለቀቁ ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የበጀት እጥረት የሚጀመሩ ኘሮጀክቶች በተያዘላቸው ቀነ ገደብ እንዳይጠናቀቁ በቀዳሚነት እንቅፋት እንደሚሆንም ይነገራል።

ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ ባላቸው ትላልቅ ኘሮጀክቶች ድኅረ ትግበራ ግምገማ ማካሄድ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ቢሆንም በተጠናቀቁ እና አገልግሎት መስጠት በጀመሩ ኘሮጀክቶች የድኅረ ትግበራ ግምገማ የማይከናወኑባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይደመጣል።

ከዚህ ባሻገር መንግሥት የኘሮጀክት አፈጻጸሞችን በተመለከተ ችግሮችን በመለየት እና በማጥራት እንከኖችን ለመቅረፍ በሚረዳ የማሻሻያ ተግባራት ላይ መሥራት ግድ እንደሚለው በጉዳዩ ላይ ሐሳብ የሚሰጡ የዘርፉ ባለሞያዎች ያሳስባሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የመሠረተ ልማት ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ታምራት ገብረመስቀል ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት፣ በርካታ ፕሮጀክቶች የጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸው ወደ ሥራ የሚገቡበት ወቅት ቢኖርም፣ በወሰን ማስከበር፣ በበጀት እና በሌሎች ምክንያቶች የሚጓተቱበት ሁኔታ መኖሩን ይገልፃሉ።

አክለውም የራሳቸው የሆነ የሚጀመሩበት እና የሚጠናቀቁበት ሁኔታ እና የራሳቸው የሆነ በጀት የሚኖራቸው የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት እንዲጠናቀቁ ካስፈለገ ቀደም ተብሎ ከመጀመራቸው በፊት ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች እንዳሉ ተናግረዋል። በዚህም ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ እንቅፋቶችን መቅረፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ለአብነት ከመንገድ ግንባታ ኘሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ለኘሮጀክቶች መጓተት የወሰን ማስከበር ችግር እንደ አንድ ምክንያት እንደሚጠቀስ እና ይህን በተደጋጋሚ ይገጥማል ተብሎ የሚታሰብ ምክንያት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጥር ሥራዎች ከመጀመራቸው ጀምሮ እንቅፋቶቹን መቅረፍ ግድ ይላል የሚሉት ዳይሬክተሩ ናቸው።

በተጨማሪ ችግሮችን በሂደት በመፍታት የትኛውም የመሠረተ ልማት ተቋማት ተቀናጅተው እና ተናበው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። እንዲሁም ከጅምሩ እነዚህን ችግሮች መፍታት ከተቻለ ደግሞ መሠረተ ልማታቸው የሚጓተቱ ኘሮጀክቶችን በጊዜያቸው ማጠናቀቅ እንደሚቻል አስምረውበታል።

ማንኛውም የመሠረተ ልማት ኘሮጀክት ለሕዝብ ጠቀሜታ የሚውል እና ሕዝብን መሠረት አድርገው የሚከናወኑ መሆናቸውን ተረድቶ፣ የማኅበረሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ከላይ የተነሱ እና ሌሎች እንከኖችን በመፍታት ኘሮጀክቶችን በተያዘላቸው ቀነ ገደብ ማጠናቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርህ ተስፋ (ዶ/ር)፣ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በወቅቱ እና በተያዘላቸው ቀነ ገደብ የማይጠናቀቁበት ሂደት እንዳለ አውስተዋል።

ግድቦች፣ የባቡር ሀዲዶች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመሮች፣ መንገዶች፣ ሕንጻዎች እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ኘሮጀክቶችን ጨምሮ በብድር በሚገኝ ገንዘብ እና በጀት ሥራ የሚጀመርበት ሁኔታ እንዳለ እና ኘሮጀክቶች ብዙ ዓመት የሚጓተቱበት ሂደት እንዳለም አያይዘው ጠቁመዋል።

አብዛኞቹ ኘሮጀክቶች ሰፊ እቅድ ሳይያዝላቸው ወደ ተግባር የሚገቡበት ሁኔታ እንዳለም ነው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ያነሱት። ለአብነት የአንድ ክልል መንግሥት ‹በክልላችን ኢንዱስትሪ ፓርክ የለንም› በሚል፣ ነገሩ የፖለቲካ መብት ሆኖ የሚታይበት እድል በመኖሩ፣ ጥያቄ አንስተው ጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚያገኝም ይገልፃሉ። ይህም መሆኑ ሰፊ ዝግጅቶችና ጥናቶች ቀድመው እንዲደረጉ እድሉን ያጠብባል።

ሰፊ ዝግጅት ሳይደረግባቸው ወደ ተግባር የሚገቡ ኘሮጀክቶች በመኖራቸው፣ በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይቋጩ እንቅፋት ከሚሆናቸው ጉዳዮች አንዱ ሆኖ በቀዳሚነት መጥቀስ እንደሚቻል ተናግረዋል። የኮቪዲ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በተከሰተበት ወቅት የተቋረጡና የተስተጓጎሉ ኘሮጀክቶችም እንደነበሩም ሳያስታውሱ አላለፉም።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ አክለውም፣ ኘሮጀክቶች በወቅቱ እንዳይጠናቀቁ የኮንትራክተሮች ገንዘብ አለመከፈል በተጓዳኝ በምክንያትነት እንደሚጠቀስም ተናግረዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመከላከል እንዲቻል፤ ማንኛውም ኘሮጀክት ከመጀመሩ በፊት በምን ያህል ዓመት እንደሚጠናቀቅ እና የገንዘቡ ሁኔታ ምን መምሰል እንዳለበት ገንዘብ ሚኒስቴር ማረጋገጥ አለበት ሲሉ መክረዋል።

በተጨማሪ መንግሥት ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት በተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ ለማጠናቀቅ ቀድሞ ውሳኔ ማስቀመጥ እና ኘሮጀክቶችን ሠርተው የሚያስረክቡ አካላትን በተገቢው መንገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ለሚችሉ ድርጅቶች መስጠት እንዳለበት ባለሙያው አስረድተዋል።

ባለሙያው አክለውም፣ መንግሥት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ቅድሚያ ሊሠሩ የሚገቡ እና መዘግየት ያለባቸውን ፕሮጀክቶች በመለየት ሥራቸውን ለማስፈጸም መሥራት እንዳለበት ይጠቁማሉ።

ከመሠረተ ልማት ግንባታዎች ጋር በተያያዘ በተያዘላቸው ቀነ ገደብ ከማይጠናቀቁት መካከል የመንገድ እና የሕንፃ ኘሮጀክቶችም ተጠቃሽ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ የሕንፃ መሣሪያዎች የመሸጫ ዋጋ በመጨመሩ በመዲናዋ የሚካሄዱ ግንባታዎች እንዲቀዛቀዙ በማድረግ በምክንያትነት እንደሚጠቀስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ያስረዳል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሉጌታ ሊክዲ፣ ከባለፈው ዓመት አንፃር ሲታይ በሲሚንቶ ምርቶች፣ በፌሮ ብረቶች፣ በቆርቆሮ እና በሌሎች በሕንፃ መሣሪያዎች ወይም በእያንዳንዱ ቁሳቁስ ላይ ከኹለት መቶ እስከ ሦስት መቶ ብር ጭማሬ ታይቶ እንደነበር ከዚህ በፊት ለአዲስ ማለዳ መጥቀሳቸው አይዘነጋም።

ዳይሬክተሩ  የሕንፃ መሣሪያዎች የመሸጫ ዋጋ በየወቅቱ እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄዱ የመንገድም ሆነ ሌሎች የሕንፃ ግንባታዎች እየተቀዛቀዙ መሆኑንም ነው አያይዘው ያስረዱት።

ከዚህ ባሻገር የሕንፃ ግንባታ የሚያከናውኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ከገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ ሥራቸውን ለማቆም በመገደዳቸው ለዘርፉ መቀዛቀዝ በተጨማሪ ምክንያትነት እንደሚጠቀስ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ለሕንፃ መሣሪያዎች ዋጋ መጨመር ከውጭ ምንዛሬ ጋር እና ከሌሎች ሕገ ወጥ አሠራሮች ጋር ተያይዞ በምክንያትነት የሚነሳ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ በዚህ ጉዳይ ጥናት ላይ ተደግፎ የሠራቸው ሥራዎች አለመኖራቸው ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ኃላፊነት፣ ይዞታ እና ካርታ ለሚያቀርቡ አካላት የግንባታ ፍቃድ ከመስጠት ጎን ለጎን የክትትል እና ቁጥጥር እንዲሁም የግንባታ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ሥራ እንዲጀምሩ ያደርጋል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈ ባለሥልጣኑ የግንባታ ሥራዎች እንዳይቆሙ የማስገደድ ኃላፊነት የለበትም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በከተማዋ የተጓተቱ እና የቆሙ የሕንፃ ግንባታዎችን የመለየት ሥራ እንደተጀመረ ጠቅሰዋል። እንዲሁም እነዚህ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ሙሉ መረጃ የማሰባሰብ ሂደቶች መጀመራቸውን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ባለሥልጣኑ መረጃውን አሰባስቦ ካጠናቀቀ በኋላ ለኅብረተሰቡ ሪፖርቱን ከማሳወቅ ባለፈ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ዘርፉን ለማነቃቃት የሚያግዝ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተነግሯል።

በተጨማሪ ዘርፉ እንዲነቃቃ እና ወደ ነበረበት እንዲመለስ ከታሰበ መንግሥት ከባለሀብቶች ጋር በጋራ በመሆን የኮንስትራክሽን ቁሳቁሶች የመሸጫ ዋጋን ለማረጋጋት መሥራት እንዳለበት ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

ከመንግሥት ባለፈ ባለሀብቶችም ሆነ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ዘርፉን ለማነቃቃት ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር፣ በከተማዋ በሕገ ወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ የቁጥጥር ሥራዎችን እንዲያከናውኑ እና ለባለሥልጣኑ ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ተጠይቋል። ይህም ሲባል በመዲናዋ  በመንገድ ላይ የግንባታ እቃ የሚያስቀምጡ ድርጅቶች እና አካላትን ጨምሮ ነው የተባለ ሲሆን፣ ይህን አድርገው በተገኙት ላይ የግንባታ ፈቃዳቸዉን እስከመሰረዝ የሚያደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም አውስተዋል።

አስፈጻሚ አካላት የኘሮጀክት አዘገጃጀት ቅድመ ትግበራ ግምገማ፣ ክትትል እና ድኅረ ግምገማ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውም ተነግሯል። በእያንዳንዱ የመንግሥት የልማት ኘሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ተለይተው እና ኃላፊነታቸው ተገልጾ፤ ለቅድመ ትግበራ በሚቀርበው የኘሮጀክት ጥናት ሰነድ ላይ መካተቱ የሚረጋገጥበት ስርዓት መኖር እንዳለበትም ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here