ተፈጥሯዊ ወሊድ እየቀነሰ በቀዶ ጥገና ልጃቸውን የሚገላገሉ እናቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተነገረ።
አዲስ ማለዳ ቅኝት ባደረገችባቸው የሕክምና ተቋማት እንዳረጋገጠችው በቀዶ ጥገና የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን ታዝባለች።
ምጥ በመፍራትም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች አምጠው መውለድ እየቻሉ በቀዶ ጥገና መውለድን የሚመርጡ እናቶች ቁጥር እንደጨመረ የተናገሩት፤ በአበበች ጎበና የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አናንያ ሰለሞን ናቸው።
በአበበች ጎበና የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል ከሚወልዱ እናቶች መካከል አርባ በመቶ የሚሆኑት በቀዶ ጥገና የሚወልዱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይሁንና ሆስፒታሉ ሪፈራል እንደ መሆኑ ይህ ንጽጽር ከ16 ጤና ጣቢያዎች በሪፈር ከሚመጡት እናቶች አንፃር ነው ብለዋል።
እንደ ዶከተር አናንያ ገለጻ፣ በሆስፒታላቸው ማማጥ እየቻሉ የቀዶ ጥገናን ምርጫቸው የሚያደርጉት እናቶች ንፃሬ ከአንድ በመቶ አይበልጥም። ሆኖም ይህ አሃዝ በግል የጤና ተቋማት ላይ ከፍ እንደሚል ገልፀዋል። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መደበኛ ተብሎ የሚወሰደው በአንድ ማኅበረሰብ ውሰጥ ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑት እናቶች በቀዶ ጥገና ሲወልዱ እንደሆነ ገልፀው፣ የመጠኑ ከፍ ማለት ላይ ሳይሆን በወሊድ ወቀት በእናቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን የሕይወት አደጋ መቀነስ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በዚሁ ጉዳይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ እናት፣ በመንግሥት የጤና ተቋማት የእናቶችንና የልጆችን የጤና ሁኔታን ያማከለ የወሊድ ዘዴን የሕክምና ባለሙያዎች መርጠው እንደሚጠቀሙ ገልፀዋል።
በግል የጤና ተቋማት ግን ለእናቶች ምርጫ ቅድሚያ እንደሚሰጥና ኢኮኖሚያዊ አቅሙ ያላቸው እናቶች በቀዶ ጥገና አልያም በመድኃኒቶችና በመሣሪያ የታገዘ የወሊድ ዘዴን የመምረጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም ምክንያቱን ሲያስረዱ፣ በምጥ ወቅት የሚያጋጥመውን ሕመም መፍራትና ለሚወለዱት ልጆች ጤንነት ከማሰብ የተነሳ እንደሆነ ይገልፃሉ።
በተለይ ማማጥ የሚችሉና ለመጀመሪያ ጊዜ የሚወልዱ እናቶች በምጥ ቢወልዱ ይመከራል ያሉን በመንግሥት የጤና ተቋም ያገኘናቸው የጤና ባለሙያ አንተነህ ጌታቸው ናቸው። አንዴ በቀዶ ጥገና የወለዱ እናቶች ድጋሚ ሲወልዱ ድጋሚ ቀዶ ጥገና የማድረግ እድላቸውም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
እርሳቸው በሚሠሩበት የጤና ተቋም የሚደረጉ ቀዶ ጥገናዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመራቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ባለሙያው፣ ለዚህም የጤንነት ሁኔታቸው ከሚያስገድዳቸው እናቶች በተጨማሪ፣ ከዚህ በፊት በቀዶ ጥገና የወለዱና በምጥ ወቅት ያለውን ሕመም በመፍራት ቀዶ ጥገናን የሚመርጡ እናቶች በመበራከታቸው ነው ብለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገርና ትክክለኛውን አሃዝ ለማግኘት አዲስ ማለዳ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮና ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ በስልክ ያደረገችው ሙከራ ባለመሳካቱ ሐሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።
በተፈጥሯዊ ምጥ መውለድ ቶሎ ለማገገም፣ የእናቶች ጡት ወተት እንዲኖረው በማድረግ፣ በወሊድ ወቅት አደጋን ለመቀነስ እንዲሁም በእናትና ልጅ መካከል ያለውን ግንኙነት እና የልጆችን እድገት ጤናማ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014



