መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበትራንስፖርት እጦት ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ እንደተዳረጉ ተጓዦች ተናገሩ

በትራንስፖርት እጦት ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ እንደተዳረጉ ተጓዦች ተናገሩ

ለበዓል ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለመጓዝ የፈለጉ መንገደኞች በትራንስፖርት አቅርቦት ችግር ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ እና እንግልት መዳረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ወደ ደብረማርቆስ ለመጓዝ ከሳምንት በፊት ጀምሮ ትኬት በማፈላለግ ላይ እንዳሉ የነገሩን መስቀል አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የአባይ ባስ ትኬት ቢሮ ያገኘናቸው መላኩ ጌታቸው፣ ቀድመው ትኬት ለመቁረጥ ቢያቅዱም እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል። ከዚህ በፊትም በበዓላት ጊዜ ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ አስታውሰው፣ በአሁኑ ሰዓት ካለው የነዳጅ ዋጋ ጋር ተዳምሮ የትራስፖርት ወጪ ከፍተኛ ሆኗል ብለዋል።

በመደበኛ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ከኹለት መቶ ብር በማይበልጥ ዋጋ መስተናገድ ሲገባቸው በቂ የተሽከርካሪ አቅርቦት ባለመኖሩ ምክንያት በደላሎች እስከ ስምንት መቶ ብር ድረስ እየተጠየቁ እንደሆነም ተናግረዋል። በተለምዶ ልዩ ባስ የሚባሉት ተሽከርካሪዎችም ብዛታቸው ውስን በመሆኑ ያለውን ተጓዥ ማስተናገድ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኙ የልዩ ባስ ትኬት ቢሮዎች አግኝታ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሌሎች ተጓዦችም ተመሳሳይ አስተያየታቸውን አጋርተዋል። ወደ ጎንደር ለመሄድ አስበው ከጅማ እንደተነሱ የነገሩን ሥማቸውን መግለፅ ያልፈልጉ ተጓዥ፣ አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ በተመጣጣኝ ዋጋ መኪና ማግኝት እንዳልቻሉ፤ ይሁንና በተጋነነ ዋጋ አገር አቋራጭ መኪኖች እንዳሉ ደላሎች እንደነገሯቸው ጠቅሰዋል።

በከተማዋ በሚገኙ የሕዝብ ማመላለሻ ተርሚናሎች የመኪና እጥረት እንደሚስተዋል ያረጋገጠችው አዲስ ማለዳ፣ በጉዳዩ ዙሪያ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ሥራ አሰፈጻሚ ታጠቅ ነጋሽን አነጋግራለች። ሥራ አስፈጻሚው ምንም እንኳን አገልግሎቱ የሁሉንም ሕዝብ ፍላጎት ያረካል ባይባልም፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ ስድስቱም የሕዝብ ማመላለሻ ተርሚናሎች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ተጓዦችን ለማስተናገድ እየተሞከረ ነው ብለዋል።

ከሦስተኛው ዙር የሕውሓት ወረራ ጋር በተያያዘ የሰው ኃይልና ሎጂስቲክስ ለማድረስ ወደ ግንባር የሄዱ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ የገለጹት ታጠቅ፣ በሄዱት ተሽከርካሪዎች ምትክም አዲስ አበባ ውስጥ የከተማ ትራንስፖርት  አገልግሎት የሚሰጡ ሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ጠዋት በከተማዋ ውስጥ ከሠሩ በኋላ ለከተማዋ ቅርብ ወደሆኑ ቦታዎች ተሳፋሪዎችን እንዲያጓጉዙ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከተርሚናሎች ውጪ ከመደበኛ ታሪፍ ከፍ ባለ ዋጋ ስለሚያስከፍሉት ተሽከርካሪዎች የተጠየቁት ሥራ አስፈጻሚው፣ ከበዓል ሰሞን በፊትም ተመሳሳይ ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር ጠቅሰዋል። በተለይ የነዳጅ ድጎማ ከተጀመረ ጀምሮ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር የቁጥጥር ሥራ በስፋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ይሁንና አሁንም ጥቆማዎች እንደሚደርሷቸው ጠቅሰው፣ ከጸጥታ አካላት ባሻገር ኅብረተሰቡም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ከተርሚናሎች ውጪ መንገደኞችን የሚጭኑ ተሽከርካሪዎችን በመጠቆምና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲጭኑ በማድረግ ኅብረተሰቡ አግባብ ካልሆነ ወጪና እንግልት ራሱን ማዳን እንደሚገባውም ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ምልከታ በመንገደኞች ተርሚናሎች ከሚታዩ መንገደኞች ጋር ያልተመጣጠነ የመኪና አቅርቦት እንዳለ ስታረጋግጥ፤ በሕገ-ወጥ መንገድ ከተርሚናሎች ውጪ ከመደበኛ የትራንስፖርት ዋጋ እስከ አራት እጥፍ የሚጠይቁ ተሽከርካሪዎችን አግኝታለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች