ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ቁሳቁስና ዩኒፎርም በጊዜው አለማቅረቡ ጥያቄ አስነሳ

0
1261

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በየዓመቱ የሚቀርቡ አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችና ዩኒፎርም መዘግየቱ እንዳሳሰባቸው ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች አስታወቁ።

‹‹ከዚህ በፊት በነበሩ ሦስት ዓመታት መንግሥት ለልጄ የትምህርት ቁሳቁስና የደንብ ልብስ ስለሚሰጠው፣ ዘንድሮም እንደዛው ይሆናል ብዬ በማሰብ ደብተርም ሆነ የደንብ ልብስ ለመግዛት አልተዘጋጀሁም።›› የሚሉት የተማሪ ወላጅ ተስፋዬ ቢተው ናቸው። እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የትምህርት ቁሳቁስም ሆነ የደንብ ልብስ ለልጃቸው አለመሰጠቱ አሳስቦኛልም ብለዋል።

ትምህርት ከተጀመረበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በተለይ ደብተር አስፈላጊ ነው የሚሉት ተስፋዬ፣ እስካሁን ድረስ ልጃቸው አምና ሲማርባቸው ከነበሩ ደብተሮች በተረፉት ገጾች ላይ እየጻፈ በመማር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ተማሪዎች አምና የተጠቀሙበትን የደንብ ልብስ እየተጠቀሙ መቆየት የሚችሉ ቢሆንም፣ ደብተር ግን በቶሎ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል። ልጃቸው በሚማርበት ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራን ትምህርት ሲጀመር፣ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሁሉም ነገር ይሟላላችኋል ተብለው እንደነበር ገልጸው፣ እስካሁን ግን ምንም የተሰጣቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ደብተር እስኪሟላ ድረስ በማለት አራት ደብተሮችን በመግዛት ከፊትና ከጀርባ በመጻፍ እየተማረች እንደሆነ የገለጸችው የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪዋ ፋኖስ በየነ፣ ከትምህርት ቤታቸው የትምህርት ቁሳቁስና ዩኒፎርም እስከ መስከረም 30 ድረስ ይሰጣችኋል ተብለው እየጠበቁ እንደሆነ ጠቅሳለች። አያይዛም አቅም ያላቸሁ ተማሪዎች ደብተር ግዙ እንደተባሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጻለች።

በዚሁ ጉዳይ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡት መምህር ዘመኑ ደስታ በበኩላቸው፣ በተለይ በደብተር አለመሟላት ምክንያት ከትምህርት የሚቀሩ ተማሪዎችም እንዳሉ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት የተጠቀሙበትን ደብተር እንደገና የሚጠቀሙና አዲስ ደብተር የገዙ ተማሪዎችም እንዳሉ መምህሩ ገልጸዋል። ይሁንና ቁሳቁሶቹ በጊዜ አለመሰጠታቸው ለመማር ማስተማሩ አስቸጋሪ የሆኑ ነገሮችን እየፈጠረ እንደሚገኝ አንስተው፣ በተለይ ደብተር በቶሎ ቢሟላ የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የደብተርና ተያያዥ የትምህርት ቁሳቁሶች ዋጋ መናር በበርካቶች ዘንድ ቅሬታን ሲያስነሳ የነበረ ጉዳይ መሆኑ የሚታወስ ነው። ደብተር ከመግዛት ተገላገልን ያሉ ወላጆች አሁን ላይ የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦቱ በመዘግየቱ ደብተር ለመግዛት የተገደዱ አሉ።

ጉሊት ገበያ ላይ ሽንኩርትና ድንች በመቸርቸር ኹለት ልጆቻቸውን እንደሚያሳድጉ የሚናገሩት ወርቄ አባይ፣ ኹለተኛ እና አምስተኛ ክፍል ስለሆኑት ልጆቻቸው ትምህርት ሲናገሩ፣ ‹‹ለልጆቼ ትምህርት ወጪ አለማውጣቴ ያለፉትን ዓመታት ልጆቼ ያለምንም ችግር እንዲማሩ አድርጓል›› ብለዋል። በዚህ ዓመትም መንግሥት ኹሉንም ግብአቶች እንደሚያሟላ እንደሚያምኑ ገልጸው፣ እንደዛ ካልሆነ ግን በዘንድሮ የዋጋ ውድነት ከቀለብ ተርፎ ደብተርና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለማሟላት የሚሆን አቅም እንደማይኖራቸው ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲን ለማነጋገር ለኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አንችነሽ ተስፋዬ በጽሐፍ መልዕክት አሳውቃ በስልክ ለማውራት ብትሞክርም፣ በተደጋጋሚ ‹ስብሰባ ላይ ነኝ፤ ስወጣ እደውላለሁ!› በማለታቸው ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here