ሸገር ዳቦ ፋብሪካ በአንድ ዳቦ 36 ሳንቲም እየከሰረ ለተጠቃሚዎቹ እንደሚያቀርብ የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የምርት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አካለወልድ አድማሱ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የሜድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባል በሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ኩባንያ የሚመራው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ በ2012 ተመርቆ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በቀን 1.3 ሚሊዮን ዳቦ ለተጠቃሚዎች እንደሚያደርስና ለተጠቃሚዎች የሚያደርሰው እያንዳንዱ ዳቦ 36 ሳንቲም እንደሚያከስረው አካለወልድ ተናግረዋል። ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ለትርፍ ያልተቋቋመ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመው፣ መጀመሪያ ከነበረው የዳቦ መሸጫ የዋጋ ማስተካከያ ከተደረገም በኋላ ይህ ኪሳራ ቀጥሏል ብለዋል።
ፋብሪካው ከተያያዥ ኪሳራና የግብዓት አቅርቦት ችግሮች ጋር በተያያዘ ለአንድ ወር የምርት ሂደቱን አቋረጦ ነበር። ከዛም በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ ዳቦ የሚያደርገውን ድጎማ እስከ አንድ ብር ከአስራ አራት ሳንቲም ድረስ ከፍ ማድረጉን ተከትሎ፤ አንዱ ዳቦ ይሸጥ ከነበረበት የአንድ ብር ከኻያ ሳንቲም ዋጋ ወደ ኹለት ብር ከአስር ሳንቲም ዋጋ ከፍ ማለቱ የሚታወስ ነው። ኪሳራውም በዚህ ዋጋ ከሚሸጠው ዳቦ ላይ መሆኑ ታውቋል።
ፋብሪካው በየቀኑ የሚያመርተው የዳቦ ብዛት በተለያዩ ምክንያቶች የሚለያይ ቢሆንም በሙሉ አቅሙ ወደማምረት ለመሸጋገር እየተሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት አካለወልድ፣ የኅብረተሰቡን የዳቦ ፍላጎት ለማሟላት ግን እንደማይቻል ገልጸዋል።
በርካታ ነዋሪዎች ባሏት አዲስ አበባ፣ ሸገር የዳቦ ፋብሪካ ብቻውን የኅብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት ባይችልም የማምረት አቅሙን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ለተጠቃሚዎቹ ተደራሽ ለመሆን ይሠራል ሲሉ አክለዋል። የፋብሪካው የማምረት አቅም በቀን አንድ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺሕ ዳቦ ሲሆን በቅርብ ጊዜያት አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺሕ ዳቦዎችን የማምረት አቅም ላይ እንደሚደርስም ተናግረዋል።
ዳቦዎችን ከማምረትም ባለፈ በየሰፈሩ ተደራጅተው የዳቦ ሽያጩን ለሚያካሂዱት ወጣቶች የማድረሱን ሥራ የሚሠራው ፋብሪካው፣ ዳቦ የሚያጓጉዙ መኪናዎች እጥረትና የመለዋወጭ ችግሮች እንዳሉበት የተሰማ ሲሆን፣ መኪናዎችን በመጨመርና መለዋወጫዎችንም በማሟላት ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ እንደሆነ አካለወልድ ጨምረው ተናግረዋል።
በየሰፈሩ የተቀመጡት አዳዲስ ኮንቴነሮችም ተጨማሪ የሸገር ዳቦ ማከፋፈያ ሱቆችን ከመክፈትና የምርት ማሳደጊያ ከማድረግ አንጻር ሳይሆን፣ ከአገልግሎት ጥራትና ከሌሎች ጉዳዮች አንጻር በከተማ አስተዳደሩ የተቀመጡ መሆኑ ታውቋል። እነዚህ ኮንቴነሮችም ከፋብሪካ የሚመጣውን ዳቦ ንፅህናውን በጠበቀ መንገድ ለገዢዎች እንዲደርስ ለማድረግ እንደሚያግዙም አካለወልድ ተናግረዋል።
ዳቦ በሚሸጥባቸው ሱቆች የገዢዎችን ሰልፎች መመልከት የተለመደ ሲሆን፣ ይህም በርካታ ሸገርን የመሰሉ ፋብሪካዎች እንደሚያስፈልጉ ማሳያ ነው። የከተማ አስተዳደሩ በየክፍለ ከተማው የሚያስገነባቸው የዳቦ ፋብሪካዎችም የኅብረተቡን ፍላጎት ለማሟላት ያግዛሉ ብለዋል።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማገልገል ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በኪሳራም ቢሆን ምርት ማምረታቸውን እንዳላቆሙ የተናገሩት አካለወልድ፣ በዝናብም ተሰልፈው ሸገር ዳቦን የሚጠባበቁ ደንበኞቻቸውን ማገልገላቸው እንደሚያስደስታቸው ተናግረዋል።
በ900 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው ፋብሪካው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ 380 በሚደርሱ ሱቆች ዳቦው ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆን ሲሆን፣ በተቋቋመ አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ 70 ሚሊዮን ብር እንደከሰረ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015



