ሚዛናዊነት

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ሴት ልጅ  የፍትሕ፣ የሚዛናዊነትና የእኩልነት ተምሳሌት ናት። እናት ስትሆን ደግሞ የፍቅርና የአገር።ለልጆችዋ ባላት ፍቅር ምክንያት የእናት ፍቅር ምን ያህል ጥልቅና ንጹህ እንደሆነ እንረዳለን። በተጨማሪም ልጆቿን አሳድጋ፣ አስተምራና ድራ ለወግ ማዕረግ በማብቃቷ በአገር ትመሰላለች። በዚህም ምክንያት በርካታ አገራት በሴት አንቀጽ ይጠራሉ። ልጆቿን በእኩል ዐይን በማየቷና አንዱን ከአንዱ ባለማበላለጧ የፍትሕና የእኩልነት አብነት ናት።

ሚዛናዊነት። ኹለት የተለያዩ ነገሮችን በእኩል ዐይንና አመለካከት ዐይቶና ተገንዝቦ በተመሳሳይ መንገድ ማስተናገድን ይገልጻል። ዛሬ ሐሳቤን መሰንዘር የፈለኩት የጋዜጠኝነት ሙያን ሚዛናዊነት ነው። በተለይ ሴት ጋዜጠኞች በተፈጥሮ የተለገሳቸውን ሁሉንም ልጆች በእኩል ዐይን  የማየት ሚዛናዊነትን ከጋዜጠኝነት ሚዛናዊነት ጋር አዛምደው ሊያስኬዱት ይገባል።

ነገ እሁድ ጥቅምት 13/2015 ‹ኢ−ካሽ የማማከር፣ ሥልጠናና ፕሮሞሽን› ማእከል ለ33ኛ ዙር በጋዜጠኝነት ዘርፍ ያሠለጠናቸውን ሠልጣኞች ያስመርቃል። በርካታዎቹ ሠልጣኞች ሴቶች ናቸው። ከእነዚህ ሴት ሠልጣኞች መካከል ከአዳማና ከሰበታ እየተመላለሱ ሴትነትና የቦታ ርቀት ሳይበግራቸው በጥበብ የጸኑ ይገኙበታል።

እነዚህ ጋዜጠኞችም መረጃ ሰጪውን ከተቀባዩ፣ ሕዝብን ከመንግሥት፣ ችግርን ከመፍትሔ፣ ሐሳብን ከተግባር ጋር ለማገናኘት የተዘረጉ ድልድዮች ሊሆኑ ይገባል። መረጃን ከምንጩ ወደ ሕዝቡና ወደሚመለከተው አካል የሚያስኬዱ መንገዶች ሊሆኑም ይገባል። በተጨማሪም ችግርንም መፍተሔውንም በኹለት ዐይናቸው የሚማትሩ፤ ደቃቅ የምትመስለው ችግር ወደፊት ጉዳቶችን እንደምታስከትል አግዝፈው የሚያሳዩ ዐይንና አጉሊ መነጽር እንደሚሆኑም  ይጠበቃል።

በተለይ በአሁኑ ሰዓት ሚዛናዊነት የሚጎድላቸው የአንድን ወገን ሐሳብ ብቻ የሚያንጸባርቁ መረጃዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን እና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ሲሰራጩ እየተስተዋለ ነው። በዚህ አካሄድ ደግሞ ኹለት ወገኖችን የሚያገናኝ ድልድይ መሆን አይቻልም። ይህን ለመቅረፍ የነገው የኢካሽ ተመራቂ ሴት ጋዜጠኞች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። የፍትሕና የሚዛናዊነት ተምሳሌትነታቸውን ከሙያዊ ብቃት ጋር በማዋሀድ ለውጥ ሊያመጡ ይገባል።

የእናትነት ጸጋቸውን ከጋዜጠኝነት እውቀታቸው ጋር በማቀናጀት ትውልድንና አገርን ማስቀጠል አለባቸው። እናት ሁሉንም ልጆቿን በእኩል ዐይን እንደምታየው ሁሉ ጋዜጠኛዋም ሁሉንም ሕዝብና ተቋም በእኩል ተመልክታ ተገቢውን መረጃና መፍትሔ ልትሰጥ ይገባል። እናት ለሁሉም ልጆቿ ተመሳሳይ ትኩረት እንደምትሰጥ ሁሉ ጋዜጠኛም ለሁሉም ሰው፣ ሐሳብና አቅጣጫ ተመሳሳይ ዕይታና ትኩረት ሊኖራት ያሻል። ይህም አሠራር ሚዛናዊነትን ያሰፍናል።

ይህን ትክክለኛ አሠራርም በስፋት ለማሰራጨት አየጣረ ያለው ኢካሽ የሥልጠና ማእከል ሊመሰገን ይገባል። ሌሎች ተመሳሳይ ተቋማትም ወደሥራው ቢሰማሩ ጋዜጠኝነትንና ጋዜጠኛን የሚያውቅ ባለሙያ መፍጠር ይቻላል። በመጨረሻም ለኢካሽ መሥራቾችና ለጋዜጠኛ አብርሀም ጸሐዬ ያለኝን አክብሮት እየገለጽኩ፣ ለተመራቂ ተማሪዎችም እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ።

ደስታ ሽርካ (ደስታ ጠማኙ)


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here