የኢትዮጵያ ፖስታ የቤት ለቤት የመልዕክት አገልግሎት ሊጀምር ነው

0
1660

ማክሰኞ ኀዳር 13 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ፖስታ ለግለሰቦች የቤት ለቤት የመልዕክት አገልግሎት ለመስጠት የአሰራርና የተያያዥ ጉዳዮች ጥናት እያካሄደ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል፡፡

በተመረጡ አካባዎች የቤት ለቤት የመልዕክት አገልግሎትን ለመጀመር ታስቦ የዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የአትዮ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሐና አርአያሥላሴ፣ የደንበኞችን ፍላጎት በማጥናት አገልግሎቱን ለማስጀመር እንደተወሰነ ተናግረዋል፡፡

ከ700 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት የኢትዮጵያ ፖስታ በቅርንጫፎች ከሚሰጠው የመልዕክት አገልግሎት ባሻገር ግለሰቦችን በየቤታቸው ተደራሽ የሚያደርገው አዲስ አገልግሎቱ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከማሳደግ ጎን ለጎን የሚሰራ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል፡፡ የቅርንጫፎችን ቁጥር በማሳደግም ድርጅቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ተደራሽነት ለማስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ ለድርጅቶች የቤት ለቤት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ አገልግሎቱን ለግለሰቦች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚዋ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያግዙ የሞተር ሳይከሎችና መኪናዎች ግዢ በሂደት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ ለደንበኞቹ የሚያደርሳቸው ተጨማሪ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመጀመር የፍላጎትና የአዋጭነት ጥናት እያከናወነ እንደሆነ የገለጹት ሐና  የደንበኞችን ፍላጎት የሚያሟሉና ድርጅቱ ያሉትን ቅርንጫፎች በመጠቀም የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉትን  የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶችን እንደሚያስጀምር ተናግረዋል፡፡

ለአፍሪካ አገራት ከቻይና ለሚላኩ መልዕክቶችን የትራንዚት አገልግሎት በመስጠት ወደ ተላኩበት አገራት የማድረስ ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎቱን በጀመረ በ24 ቀናት ውስጥ 20 ሺሕ ያህል መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደቻለ ተነግሯል፡፡ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የገበያ ፍላጎት እንዳለ የጠቀሱት ሐና የኢትዮጵያ ፖስታን ገቢ ለማሳደግም ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ በ2015 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት 1.21 ሚሊዮን መልዕክቶችን በማስተላለፍ ከ263 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ገቢ እንደተገኘ የገለጹት ሐና በዚህ የበጀት ዓመት በአጠቃላይ 1.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት እንደታቀደም ተናግረዋል፡፡

ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚላኩ መልዕክቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ለደንበኞች ለማድረስ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የሚከፈሉት የቀረጥ ክፍያዎች ተመን ከወጣላቸው በኋላ በኢትዮጵያ ፖስታ በኩል እንዲከፈሉ የማድረግ ሥራ እንደተሰራ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በአሰራሩ ላይ አስተያየትና ቅሬታ ያላቸው ደንበኞች በኢትዮጵያ ፖስታ የአስተያየት መቀበያ አድራሻዎች ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

በመጋቢት ወር 129ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው የኢትዮጵያ ፖስታ በ2001 በመንግስት የልማት ድርጅትነት እንዲተዳደር የተወሰነ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ በ2013 አሁን የሚጠቀምበትን ስያሜ መያዝ ችሏል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here