“ድራጎን አምላካዊው” የኢትዮጲያ የዘውግ-ፖሊቲካ እና የብሄር-ብሄረሰቦች ቀን!

ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ እንዲትገባ ምክንያት እንደሆነ የሚነገርለት የብሔር ፖሊተካ አሁንም እንደቀጠለ ወን፡፡ ኢትዮጵያን የተጠናወታት የብሔር ፖለቲካ፣ የኢትዮጵያ መከራ መከራ መቀጡሉ አይቀሬ ነው የሚሉ ሀሳቦች ከተለያዩ ምኹራን ይሰማሉ፡፡ መምህር እውነቱ ይታይ ለአዲስ ማለዳ በላኩት ጦማር፣ የዘውግ ፖለቲካ የብዙኃኑን ሕዝብ ገንዘብና ጉልበት ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን ጭምር የሚበዘብዝ ነው ሲሉ እንደሚከተለው አስፍረዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕለ-አድኅኖ ሰማዕቱ አንዲትን ልጃገረድ ከድራጎን አስጥሏት ድራጎኑን ሲገድል ያሳያል። የስዕለ-አድኅኖውን ኹነት በሚተርከው የሰማዕቱ ግድል ታሪክ እንደሚያትተው፣ በመካከለኛው ዘመን በአንዲት አገር የሚኖሩ ሕዝቦች ለሚያመልኩት ድራጎን ሴት ልጆቻቸውን መስዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር፣ በዚህም የተነሣ በአገሪቱ የሚኖሩ ልጃገረዶች አልቀው በመጨረሻም የንጉሡን ሴት ልጅ በመስዋዕትነት ያቀርባሉ. . . ።

በዚህ አምድ ላይ ስለ ቅዱሱ ገድል ለመተረክ አይደለም፣ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሰችው አገር ሕዝቦችና ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው የዘውግ ፖለቲካ ይመሳሰሉብኛል፤ እውነቴን ነው እጅግ በጣም ነው የሚመሳሰሉብኝ።

ከላይ በተጠቀሰችው አገር የሚኖሩ ሕዝቦች ልጆቻቸውን መስዋዕት አድርገው እስከመጨረስ ለድራጎኑ ታማኞች ነበሩ። በሌላ በኩል ደግሞ ድራጎኑ ልጆቻቸውን በሙሉ ዋጥ ስልቅጥ እስከማድረግ አልራራላቸውም።

እንግዲህ እንዲህ ነው፤ ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በዘውግ ፖለቲካ አምልኮት ስር ወድቃ እልፍ ዓዕላፍት ልጆቿን ገብራለች፣ ዛሬም እየገበረች ናት፣ ድራጎን የሆነው የዘውግ ፖለቲካ እስካለ ድረስ ወደፊትም  ልጆቿን ስትገብር ትኖራለች። ድራጎኑ አይራራም. . . እንደዚያው ሁሉ የብሄር ፖለቲካም ርህራሄ የለውም።

የዚያች ሐገር ሕዝቦች አምልኮቱን እንዳላጓደሉበት ሁሉ የዘውግ ፖለቲካ ዘዋሪዎች ካድሬዎቻችን አምልኮታቸውን አላጓደሉበትም። ሕልውናቸውና የማይሞላው ከርሳቸው ከዚህ መስዋዕት ፍርፋሪ የሚቃርም ስለሆነ፣ ለአንዲትም ሰከንድ ቢሆን አምልኮታቸውን አያጓድሉም።

አሁን በዚህ ሰሞን እንኳን ከወደ ወለጋ የምንሰማውና ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የተለመደው ዘርን መሠረት የደረገ ግድያና እልቂት የዘውግ ፖለቲካን አለመራራት የሚያመለክት ነው። ያሳዝናል! እጅግ በጣም ልብ ይሰብራል! መቼም ወለጋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመታረጃና የእልቂት ምድር ሆናለች።

የዘውግ ፖለቲካችን እስካልተወገደ ድረስ በእርግጠኝነት ነገ እያንዳንዷ የአገራችን ከፍል እንደዚህች ምድር የእልቂትና የመታረጃ ሥፍራ መሆናቸው እንደማይቀር ልብ ልንል ይገባል።

ሌላውን ሁሉ ትተን ባለፉት አራት ዓመታት የተፈፀሙ ዘግናኝ እልቂቶች፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች፣ ግጭትና መፈናቀሎች እንዲሁም ከፍተኛ ደም አፋሳሽ የሆኑት (በህወሓት እና በመከላከያና ጥምር ጦሮች መካከል) የተካሔዱት ጦርነቶች እና ሌሎች በርካታ ወንጀሎች መንስዔያቸው አንድ እና አንድ ይሄው የዘውግ ፖለቲካ ነው።

በሌላ በኩል ለዚህ ሁሉ ደንታ ያላቸው የማይመስሉት ካድሬዎቻችን ከድራጎን ለከፋው የዘውግ ፖላቲካችን መስወዕት የሆኑ ሕፃናትና ሴቶችን ጉዳይ ከምንም ሳይቆጥሩ፣ ለዘውግ ፖላቲካቸው ዓመታዊ ክብረ-በዓል ፌሽታና ፈንጠዝያ ሐዋሳ ከተሙ። ኧረ ወገን ወዴት እያመራን ነው? ሰው እንዴት በዚህ ደረጃ ከሰበአዊ-ክብር ይዘቀጣል? አንድ አገርን ለመምራት ቃል ገብቶ ሥልጣን የያዘ ግለሰብም ይሁን ፓርቲ የዜጎች እልቂት እንዴት ትንሽ እንኳን አይገድደውም? ባይገደው እንኳን እንዴት ማስመሰል ያቅተዋል? ማስመሰሉም ይቅር እንዴት ሴቶችና ሕፃናት በሚያልቁበት ምድር ሰው ድግስ ደግሶ የደስታ ክብረ በዓል ያደርጋል? በጣም ብዙ ብዙ???

እዚህ ጋር ሁለት ተፃራሪ እውነታዎችን ‘Paradoxes’ እንረዳለን፡

  1. የዘውግ ፖለቲካ ብዙኃኑን ሕዝብ ገንዘብና ጉልበት ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን ጭምር የሚበዘብዝ ሲሆን
  2. ለካድሬዎቹ ደግሞ የማይገመት የፈንጠዚያ፣ የፌሽታና የስርቆት ምንጭ ነው።

ስለዚህ የዚያች አገር ሕዝቦች ልጆቻቸውን ሁሉ ገብረው እስኪጨርሱ ድረስ የድራጎኑን አምልኮት እንዳላቋረጡ ሁሉ፣ ከሰባዓዊ ክብር የወረዱ የብልፅግና ካድሬዎችም ለዘውግ ፖለቲካ አምልኮታቸውን አያቋርጡም።

በዚህ አጋጣሚ ከዓመት በፊት ለአንድ ሥራ ሐዋሳ ከተማ በሔድኩበት ወቅት ያስተዋልኩትን የዘውግ ፖለቲካ አስቀያሚ ገጽታ ላጋራችሁ። በሥራው ላይ ያገኘኋቸው አንድ ጠንካራ ሴት በሐዋሳ ከተማ ለዓመታት ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትንና የሕፃናት ጥቃትን እንዲሁም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን በማጋለጥና ለፍትሕ በማቅረብ ይታወቃሉ። እናም ስለሥራቸው፣ ስላከናወኗቸው ጥቃቶችን የማጋለጥ ተግባራቸው እና ስላስገኟቸው የፍትሕና የእርምት እርምጃዎች እያወጉኝ ከቆዩ በኋላ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ትዕግስታቸውን የሚፈታተን የሕግ ግድፈት በተደጋጋሚ እየገጠማቸው መቸገራቸውን ገለፁልኝ። እኔም ጉዳዩንና መንስዔውን ጠየቅዃቸው።

ትክዝ ብለው የዘውግ ፖለቲካ መሆኑን ገለፁልኝ፣ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ጠየቅኋቸው። እርሳቸውም አብራሩልኝ። ሲዳማ ክልል ሆኖ ከተደራጀ በኋላ፤ በሐዋሳ ዋና ዋና ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሥራ ኃላፊነቶች በብሔሩ ተወላጆች እንዲያዝና የሌላ ብሔር ተወላጆች ትውልድና እድገታቸው ሐዋሳ ቢሆንም እንኳን ባይተዋርና መጤ ተብለው መፈረጃቸውን ነገሩኝ። እኔም ይህማ በመላ ኢትዮጵያ የምናስተውለው የዘውግ ፖለቲካ ነቀርሳ መገለጫ መሆኑን አረጋገጥኩላቸው። ይህ ብቻ እንዳይመስልህ ብለው ቀጠሉ።

ይህ ብቻ አይደለም በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም አንዲት የዘጠኝ ዓመት ሕፃን ጾታዊ ጥቃት ተፈፅሞባት ጉዳዩን ለፖሊስ ያመለክታሉ፡፡ ክስ ተመስርቶ የፍትህ ሒደቱን ሲከታተሉ እንደቆዩም ነገሩኝ። ሆኖም ባልተጠበቀ ሁኔታ ተጠርጣሪው በነፃ ተለቆ የፍትሕ ሒደቱ እንደተቋረጠ ነገሩኝ። ለምን ብዬ ስጠይቃቸው ተጠርጣሪው የሲዳማ ብሔር አባል እንደሆነና ተጠቂዋ ሕፃን ደግሞ የሌላ ብሔር አባል መሆኗ ብቸኛው ምክንያት እንደሆነ ሲነግሩኝ እጅግ በጣም አዘንኹ።

የዘውግ ፖለቲካችን ከምናስበው በላይ ሰብአዊ መብትና ክብሮችን አደጋ ላይ እየጣለ እንደሆነ ያመለክተናል። ሰው ሰውን ገድሎ፣ ከፍተኛ የስርቆሽ ወንጀሎችን ፈጽሞ፣ ጾታዊ ጥቃቶችን አድርሶ፣ የዘር እልቂትን ፈጽሞ ብሔር በሚባል ሸለፈትና ቅርፊት ውስጥ እየተደበቀ፤ ስለ ሰብአዊ መብት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ዴሞክራሲ አይደለም መናገር  ማሰብ እንኳን አይቻልም።

ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ የዘውግ ፖለቲካ ፍፃሜ የሌለው መሰነጣጠቅ፣ መፈረካከስ፣ እርስ በእርስ መበላላት ውስጥ የሚከት ክፉ ጣዖት መሆኑን፣ አገልጋዩ የሆኑት ከሰባአዊ ክብር የወረዱ ካድሬዎች እንኳን አያውቁም። ዛሬ ላይ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ምንትስ፣ ምንትስ እየተባባልን እየተባላንና ንፁህ ደም ያለ ከልካይ እያፈሰስን ነው። አንድ የማረጋግጥላችሁ እውነታ በዚህ አይቆምም። ነገ ወለጋ፣ ሸዋ፣ አርሲ ምንት ምንትስ እያልን እንቀጥላለን። ድራጎኑ የአገሪቱ ሕዝቦች ልጆቻቸውን እስኪጨርሱ እንዳልራራላቸው ሁሉ የዘውግ ፖለቲካም እርስ በእርስ ተባልተን እስክንጨራረስ እንደማይራራልን ልናውቅ ይገባል።

ካድሬዎቻችንም የሚበሉት ቁርጥና የሚራጩት ውስኪ የወገኖቻቸው ስጋና ደም እንደሆነ እንዲረዱት በአፅንዖት ለማሳሰብ እወዳለሁ። ልብ ይስጠን!

ሕዳር 29/2015 ዓ.ም.

መምህር እውነቱ ይታይህ

ከመሐል አዲስ አበባ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here