ፌዝ : የ “አፍሪቃ አቴንስ” የተባለላት የሞሮኮ ፈርጥ

0
1147

ውድ የአዲስ ማለዳ አንባቢዎች እንደምን ከረማችሁ? እኔ  ኑሮና ብልሃቱን ማሳካት  ፋታ አሳጥቶኝ እዚህ ጋዜጣ ላይ ሳምንታዊ “ማኅበረ ፖለቲካ” አምደኛ መሆን ካቆምኩበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ደኅና ነኝ።

ወደ ጋዜጣዋ ( ሄጄ ስመለስ ከህትመት ወደ ዲጂታል ተቀይራ ወደ ጠበቀችኝ ) አዲስ ማለዳ የመለሰኝ የጉዞ ታሪክ ነው።

ብዙ ሊባልበት በሚችለው ያለንበት ወቅት፣ በዚህ ሁሉ ውዝግብ፣ ግርግር፤ ሐዘን መካከል በቅርብ በተፈጸመው የሞሮኮ ጉዞዬ ያየኋትን የትውልድ ከተማዬን እጅጉን ስለምትመስላት ውቢቱ ፌዝ (ፌስ) ባልነግራችሁ አምሳያዋ ሐረር ራሱ ትቀየመኛለች ብዬም ነው መመለሴ።

በዚህች በ2014 በአገሪቱ በተካሄደው የሕዝብ ቆጠራ መሠረት 1.1 ሚሊዮን ነዋሪዎች እንዳሏት በሚነገርላት  የሞሮኮ ኹለተኛዋ ትልቅ ከተማ የተገኘሁት በአፍሪካ የሚዲያ ሴቶች ስድስተኛው ኮንፈረንስ ለመሳተፍ ነው። ቢሆንም ራሴን ጨምሮ 4 ኢትዮጵያዊያንን ስፖንሰር ያደረገን የስዊድኑ ፎዮ ሚዲያ ኢንስቲቲዩት ደግነት ጨምሮበት አንድ ተጨማሪ ቀን ታሪካዊቱን ከተማ እንድናይ በአስጎብኚ የታገዘ የከተማ ሽርሽር ስላዘጋጀልን ነው።

ፌዝ በሞሮኮ በስተሰሜን፤ ከስመጥሮቹ ከአትላስ ተራሮች ሰሜን ምዕራብ የምትገኝ፣ እነሱ “ፌዝ መክኔስ” የሚሉት አስተዳደር አካባቢ ከተማና፣ አስጎብኛችን በኩራት እንዳነሳት የአገሪቱ የባህል፣ የዕደ ጥበብ፣ የመንፈሳዊነት፣ የመቻቻል ማዕከልም ናት።

ፌዝ ለመድረስ የአውሮፕላን በረራዎች ቢኖሩም ዓለም ዐቀፍ በረራዎች የሚመጡት ወደ ካዛብላንካ ነው። ፌዝ ከካዛብላንካ 246 ኪሎ ሜትር ከዋና ከተማዋ ራባት 189 ከቱሪስት መዳረሻዋ ማራጃድ ደግሞ 387 ኪሎ ሜትር ትርቃለች። ከካዛብላንካ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ተነስቶ ቀጥታ የሚያደርሰውን ባቡር ጨምሮ ሚኒባስና አውቶብስ ግሩም ሆኖ በተሠራው መንገድ (high way) ፌዝ ያደርሷችኋል።

ሥሟን እነሱ ‹‹ኦኤድ ፌዝ›› ከሚሉትና አሮጌው የሚባለው የድሮ ከተማ ዙሪያውን ከተመሠረተበት ፌዝ ወንዝ አግኝታለች። በኢድሪስድ ሥርወ መንግሥት ወቅት ከ8ኛው እስከ 9ኛው ክፍለዘመን እንደተመሠረተች ሲነገርላት ከቱኒዚያ በመጡ አረብ ፍልሰተኞች ምክንያት ‹አረባዊ› የሚባል ባህርይ እንዳላበሷት ስለከተማዋ የተጻፉ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ቀደምት ነዋሪዎችዋ ግን አይሁዳውያንና የበርበር ሕዝቦች ናቸው።

ከተማዋ አስጎብኛችን “የመቻቻል ከተማ” ናት ሲል የነገረን ታሪክ የመጣበት ምክንያት ደግሞ እስራኤል እንደ አገር ስትቋቋም ወደ አገራቸው አብዛኞቹ ቢመለሱም አሁንም ሦስት ሺሕ የሚጠጉ የአይሁድ ዝርያ ያላቸው በከተማዋ እንዳሉ ሰምተናል። በጉብኝታችን ወቅት እንዳየነውም በዕብራይስጥ በትልልቁ የተጻፉባቸውን ተቋማት ጭምር ይዛለች፤ ፌዝ። 99 በመቶ ሕዝቧ የእስልምና እምነት ተከታይ በሆነበት አገር ነው ይህ እውነታ የሚንጸባረቀው።

ከፍተኛ የሚባልላትን እውቅና ያገኘችው ከ13-15 ኛው ክፍለ ዘመን የአገሪቱ የፖለቲካ ማዕከል በነበረችበት ወቅት ቢሆንም በ857 እንደተመሠረተ የሚነገረለት የዓለም የመጀመሪያው ሙስሊም ዩኒቨርሲቲ “ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አልቋራዊን” መገኛም ናት። ይኸው ዩኒቨርሲቲ በአንዳንዶች ከዓለም ረጅም እድሜ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው ይባልለታል፤ (እኔ አይደለሁም፣ ያነበብኩት ሰነድ ነው እንዲህ ያለው።) ይኸው ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋም መስጊድ ሆኖ እንዲያገለግል ሲሆን ያቋቋመችው ፋጢማ አል ፊህሪ የተባለች የአረብ ሴት ናት። ፋጢማ ታዋቂ የተሳካለት የንግድ ሰው የነበረውና ከቱኒዚያ የመጣው አባቷን ሀብት የወረሰች፣ በሀብቱም በከተማዋ ሌጋሲዋን ለመተው የሠራች እንደሆነች ሲጠቀስላት ያቋቋመችው ማዕከል በእስልምናው መሪ መንፈሳዊና የትምህርት ሆኖ መቆየት ችሏል። በ1963 የስቴት ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ሲዋቀረ አሁንም ዓይነተኛ የትምህርት ተቋም ነው።

ዩኒቨርሲቲው የሚገኘው እንደኛው ጀጎል በግንብ ታጥሮ በበሮች ተሰድሮ ከሚገኘው “መዲና” ነው።  የፌዝ መዲና (The Medina of Fez) እንደ ሐረሩ የጀጎል ግንብ ሁሉ ( ከ1981 ጀምሮ) በዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች መዝገብ የሰፈረ ነው። የግንቡን ውስጥ ጠባብ መንገዶች እነሱ በዓለም በእግር ብቻ የሚኬድበት ረጅም መንገድ ሲሉ ይጠቅሱታል። መዲናው  9 ሺሕ 600 ጎዳናዎች፣ 18 ኪሎ ሜትር አጥር እና 11 በሮች ያሉት ነው ።

መዲናው ከከተማዋ መጎብኘት አለባቸው ከሚባሉት ታሪካዊና ዕደጥበባዊ ፋይዳ ያላቸው ቦታዎችን የያዘ ነው። የእኛም ዋነኛ የጉብኝት መነሻ ነው። እኛም በመንገዳችን ቆም ካልንበት “የንጉሡን ቤተመንግሥት ሳታዩ ፌዝን አይቻለሁ ማለት ዘበት ነው” ከሚባልለት የ “ዳር ኤል ማክሃዚን” ቤተመንግሥት ውጪ ዋናው የከተማው ጉብኝታችን በዚሁ “የፌዝ መዲና” ውስጥ ነበር።

ወደ መዲናው ጉብኝት ከማለፌ በፊት ቤተመንግሥቱ ጋር ስንቆም አስጎብኛችን ሐኪም የወቅቱ የሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ የአባቱን ንጉሥ መሐመድ ኹለተኛ ሞት ተከትሎ ወደ ዙፋን የመጣ፣ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈ መሆኑን ነገረን። ንጉሡ ለሴቶች ትምህርት ትኩረት መስጠቱ ለዚህ መወደድ እንደ ምክንያት ሲጠቀስ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚስቱን አደባባይ ይዞ የታየ፣ በደረሰበት ሁሉ አብራው እንድትሄድ ያደረገ መሆኑ በአስጎብኛችን ተጠቅሷል። ሕዝቡም የንጉሥ ሚስት በቲቪ ሲያይ የሱ ሚስት ሳልማ ቤናኒ የመጀመሪያው ናት። አንድ ሚስት ብቻ ያገባ፤ ሕግ ቀይሮ ያለመጀመሪያ ሚስት ፈቃድ ኹለተኛ ሚስት ማግባት ያስከለከለ ነው። አስጎብኛችን ሐኪም “Of course the women would never say yes” ሴቶች ቢሞቱ አይፈቅዱም ብሎ አስቆናል።

የንጉሡ ገድል ስላስደነቀኝ ስለሱ የበለጠ ለማወቅ ብዬ ኢንተርኔት ሳስስ ባለፉት 23 ዓመታት በሥልጣን ላይ ያለው የ59 ዓመቱ ንጉሥ ከፈረንሳዩ ኒስ ሶፊያ አንቲፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሥልጣን ከመያዙ ሦስት ዓመት ቀድሞ በማእረግ በሕግ የዶክትሬት ዲግሪ መቀበሉን ተረዳሁ። ስለሱ በሚያወራው ሁሉ ለሴቶች ክብርና ሥልጣን ስለመስጠቱ የአገሪቱንም የቤተሰብ ሕግ ለሴቶች እንዲስማማ ሆኖ እንዲሻሻል ስለማድረጉ አንብቤያለሁ።ፎቶ: የ “ዳር ኤል ማክሃዚን” ቤተመንግሥት

የፌዝ መዲና የከተማዋ ቀደምት ክፍል ሲሆን (“መዲና” ከተማ ማለት ነው ይላሉ) ፌዝ ኤል ባሊ እና ፌዝ ጀዲድ የሚባሉ ኹለት ትንንሽ ክፍሎች አሉት። ፌዝ ኤል ባሊ ከፍተኛ የሃይማኖትና የባህል ዋጋ የሚሰጣቸው የታዋቂው ቋራዊን ዩኒቨርሲቲና የሞውሊ ኢድሪስ ዛውያ (ለሀይማኖት ትምህርትና ለሌሎች አገልግሎት የሚውል ሕንጻ) የሚገኝበት ሲሆን ኹለተኛው ፌዝ ጀዲድ 185 ኤከር ስፋት ያለውና አሁንም ድረስ ነገሥታቱ የሚጠቀሙበትን ቤተ መንግሥት የያዘ ነው።

መዲናው ብዙ ዛውያዎችና መስጅዶችን እንዲሁም መድረሳዎችን የያዘ መሆኑ ከእኛው ጀጎል ጋር የሚያመሳስለው አንድ ሌላ ነጥብ ነው። የሐረሩ ጀጎል መስጅዶች መያዙ ሲነገርለት የሀይማኖትና የዓለም ትምህርት የሚሰጥባቸው መድረሳዎችም ሞልተውታል።ፎቶ: የመዲናዋን ሰሜናዊ በር

የመዲናዋን ሰሜናዊ በር አልፈን እንደገባን ጠበብ ባሉ መንገዶችዋ ከፈረስ ጋሪና በሰው ከሚገፉ ተሽከርካሪዎች እየተሸዋወድን በስፋት ሥጋ፣ አትክልት፣ አሳ የሚሸጥበትን የምግብ ገበያ ዐየን። በባህላዊ መንገድ ሥጋ እንዳይበላሽ ለማቆየት ስለሚያደርጉበት መንገድ ሰማን። በመቀጠል በውሃ ይሠራል የተባለ ባህላዊ ሰዓት መቁጠሪያን ዐየን። ቀጥሎ ከተማዋ ከተመሠረተች ጀምሮ በቦታው እንደነበር የሚነገርለት የቆዳ መሥሪያ በመዲና ጉብኝታችን ያየን ሲሆን  በመዲናው ውስጥ የሚገኝ ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ ነው።

ተጠባብቀው ተሠርተው በቀጭን አንድ ሰው በሚያሳልፍ ደረጃ ወደላይ እየወጡ የቆዳ ውጤቶችን ከጫማ እስከቦርሳ ያሉባቸው ሱቆች በረንዳቸው ወደ አንድ ወገን ሆኖ ቁልቁል ሲታይ ቆዳ የሚለፋበት ቀለም የሚነከርበት ብዙ ትልልቅ ጉድጓዶች ያሉበት ክፍት የጣራ ላይ ወርክሾፕ የቹዋራ ቆዳ ሥራ ቦታ ያያሉ። አስጎብኛችን ይሄም በዓለም ረጅም እድሜ ያስቆጠረ የቆዳ ጥበብ ቦታ ነው ብሏል። ይሄ ሪከርድ ቢቀር ያየነው ከመቀመጫ እስከ ጃኬትና ቦርሳ ግን ቆዳ ሥራን ሞሮኮዎች ይሥሩት ያሰኛል። ውብ ነው ዋጋው ግን አስደንጋጭ።

ፎቶ: የቹዋራ ቆዳ ሥራ ቦታና የቆዳ ውጤቶች በከፈል

ቀጥሎ ያየነው የነሐስና የብር አንጥረኞች ጌጣጌጥም እንደዛው ድንቅ ነው። ከአላዲን ኩራዝ እስከ ፊልም ላይ የምናየው ድንቅ የሻይ ማንቆርቆሪያ ሞልቷል። ለዋጋው ግን መቶዎች ዶላሮች ይጠይቃል፤ አይቀመስም። ሌላው በመጨረሻ ያየነው የመዲናው ስፍራ አርጋን የሚባለውን በአገሪቷ ብቻ የሚገኘውን ፍሬ በመጠቀም የሚሠራውን ዘይት መጭመቂያ ሥፍራ ነው። የሄድንበት የሴቶች የኅብረት ሥራ ማኅበር የሚመራው ሥፍራ በተፈጥሮ ዘዴ ተጠቅመው የሚሠሯቸውን ከሊፒስቲክ እስከ የፊት ክሬምና ሌሎች የውበት መጠበቂያ ምርቶች ዐይተን ተገርመናል። እዚህም ሌሎችም ቦታዎች የዋጋ ነገር እንዳየነው የፌዝ ነዋሪዎች ከቱሪዝም ቱሩፋት ከፍተኛ የሚባለውን ጥቅም ለማግኘት ቆርጠው የተነሱ መሆኑን ነው።

ሞሮኮ ከ1912-1956 በፈረንሳይ ቅኝ ተገዝታለች። ከመዲናው ግንብና ከአሮጌው ከተማ አጥር ውጪ ያለው የፌዝ ዘመናዊ ክፍል (villes Nouvelles) በዚሁ ወቅት ሲገነባ በአገሪቱ ከኦፊሴል የሥራ ቋንቋዎች ከሆኑት አረብኛና የበርበር ቋንቋ ተስተካክሎ በስፋት የሚነገረው ፈረንሳይኛም የዚሁ ውጤት ነው። በቋንቋ ረገድ ከሱቅ እስከ ታክሲ ነጂ በእንግሊዝኛ ለመግባባት አዳጋች ነው። ታክሲዎቹን ባለሜትሮቹን እየለየን፣ አድራሻ ለመንገር ሆቴላችን ኤሌክትሮኒክ ካርድ ላይ ያለውን ጽሑፍ እያሳየን ዘልቀናል።

ከተማዋን የጎበኘሁት በዓለም ዋንጫ ወቅት እንደመሆኑ ኹለቱን ከስፔንና ከፖርቹጋል ያደረጉትን ጨዋታ ከአገሬው ጋር (በካዛብላንካና ፌዝ) የማየት እድል ገጥሞኝ ነበር። ከጨዋታዎቹ በኋላ የነበረው ፌሽታ አጀብ የሚያስብል ነበር። የከተማው ሰዎች ፌዝ በነበረው ግጥሚያ ወቅት በኩራት ኹለቱ የብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች የፌስ ተወላጆች መሆናቸውን ሲነገሩን ነበር።

ከተማዋ በአገሪቱ ከፍተኛው ሊግ “ቦቶላ” የሚጫወቱ ማስ ፌዝ እና ዋይዳድ ደ ፌዝ የሚባሉ ኹለት የእግር ኳስ ክለቦች ሲኖሯት፣ የከተማዎቹ ጨዋታዎች የሚደረጉት 45 ሺሕ ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው “ኮምፕሌክስ ስፖርቲፍ ደ ፌዝ” የተሰኘው ስቴዲየም ነው።

ጽሑፌን ሳጠቃልል፤ ፌዝ ያደኩባትን ከተማ መስላ ውበቷም የእጅ ሙያተኞችዋም ማርከውኝ በሰፊው ብጽፍላትም በግሌ ስፖንሰሮቼ ካሰናዱት የጉዞ ፕሮግራም በፊት ደርሼ የፋይናንስ ማዕከል ናት የሚሏትን ካዛብላንካን ዞር ዞር ብዬባታለሁ። ከተማዋ የምትታወቅበትና በአፍሪካ ትልቁንና በዓለም የሰባተኛ ደረጃ እንዳለው የሚነገርለትን የንጉሥ ሐሰን ኹለተኛን መስጊድ ዐይቻለሁ። መስጊዱ ከሚከፈት ከሚዘጋ ጣራና በማይታይ ሁኔታ ከተገጠሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድምጽ ማጉያዎች ከፍተኛ ዘመናዊ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚታይበት፣ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የፈሰሰበት፤ ሙስሊም ላልሆኑ ሰዎች ለጉብኝት ክፍት የሆነ መሆኑንም በጉብኝቴ ወቅት ተረድቻለሁ። ፎቶ ሊያስቀረው ከሚችለው በላይም ግርማ ሞገሳም ነው።

 *የተጠቀሱት ዓመተ ምህረቶች በሙሉ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ናቸው

ጸሐፊዋ የአዲስ ማለዳ የቀድሞ ዓምደኛ ሲሆኑ የሚዲያኮምዩኒኬሽና የአድቮኬሲ ባለሙያ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው Bethlehemne@gmail.com  ማግኘት ይቻላል

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here