ብፁአን አባቶች በአዋሽ ሰባት የታሰሩ ወጣቶችን ሊጎበኙ ነው

0
1411

አርብ የካቲት 17 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ወቅታዊ ችግር ምክንያት አዋሽ ሰባት በእስር ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ሁኔታ ለመመልከት ብፁአን አባቶች የሚመሩት ልዑክ በማረሚያ ቤቱ ጉብኝት እንደሚያደርግ ቤተክርስትያኗ ያቋቋመችው ጊዜያዊ የሕግ ኮሚቴ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በማረሚያ ቤቱ የታሰሩ ወጣቶች ያሉበትን ሁኔታ ለመከታተል አስቸጋሪ እንደሆነ የተናገሩት የኮሚቴው አባል የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አያሌው ቢታኒ፣ ወጣቶች ያሉበትን ሁኔታ ለማየትና ተከታይ የሕግ ሂደቶችን ለማስጀመር ቦታው ድረስ መሄድ አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በቦታውም ከበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከአዲስ አበባና በዙሪያዋ ካሉ አካባቢዎች ታፍነው የተወሰዱ በርካታ ወጣቶች እንደሚገኙ ተግሯል፡፡

የሕግ ኮሚቴው እስካሁን ድረስ በአዋሽ ሰባት የታሰሩ 268 ወጣቶች እንዳሉ ሪፖርት የደረሰው ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የአቃቂ ቃሊቲ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ሕብረት ሰብሳቢ የሆነው ዳዊት ጉታ ብቻ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንደታየለት ጠበቃው ተናግረዋል። ወጣቱም በፍርድ ቤት የዋስ መብቱ ተከብሮለት እደተፈታ የተናገሩት ጠበቃው፤ ከእሱ ውጭ ጉዳያቸው በፍርድቤት የታየላቸው ወጣቶች እንደሌሉ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና አዋሽ ሰባት ታስረው ከነበሩ ወጣቶች መካከል የተፈቱ ስለመኖራቸው ቢወራም ማረጋገጥ አልተቻለም ብለዋል፡፡

በአዋሽ ሰባት የፌደራል ፖሊስ ማሰልጠኛ ውስጥ በርካታ ወጣቶች እንደታሰሩ የሚያነሱ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የታሳሪ ቤተሰቦችም እስካሁን በሕግ የተያዘ ጉዳይ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ይህንኑ ለማስተካከልም የደህንነት ጉዳዮች እንደተጠናቀቁ በብጹአን አባቶች የተመራ ልዑክ በቦታው ጉብኝት ያደርጋል ያሉት ጠበቃው፤ ጉብኝቱ በቀጣይ ሳምንት ውስጥ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስን ትዕዛዝ አክብረው ከጥር 29 እስከ የካቲት 1 በዋለው ጾመ ነነዌ ጥቁር ልብስ ለብሰው ወደ መስሪያ ቤታቸው በመግባታቸው ምክንያት እርምጃ የተወሰደባቸውን ምዕመናን ጉዳይ የሚከታተል 15 ጠበቆችን ያካተተ ግብረ ኃይል መቋቋሙን የተናገሩት ጠበቃው፣ የተበዳዮችን ቃል እየተቀበሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ በአስተዳደራዊ መንገድ የሚመስተካከሉ ጉዳዮችን ከለየ በኋላ በሕግ መያዝ ያለባቸው ጉዳዮች ከተገኙም ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያመራ ተነግሯል፡፡

ጊዜያዊ የሕግ ኮሚቴው ከካህናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ሆነው በቤተክርስትያኗ ጉዳይ ከታሰሩ ምዕመናንና በተጨማሪም፣ ቤተክርስትያኗ ባጋጠማት ችግር ከጎኗ በመቆማቸው ምክንያት የታሰሩ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ታሳሪዎችን ጉዳይንም ይዞ በፍርድ ቤት እየተከታታለ እንደሚገኝ ጠበቃ አያሌው ተናግረዋል፡፡

በፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው እንዲከበር የተወሰነላቸው ታሳሪዎች እየተፈቱ እንደሚገኙ የተናገሩት ጠበቃው አጠቃላይ ያለውን የሕግ ሂደት በመግለጫ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here