አስገድዶ መድፈር በሕክምና ቦታዎች ለፈውስ ሔዶ ሌላ ህመም?

0
733

ቤተልሔም ነጋሽ በሕክምና ተቋማት ውስጥ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚሔዱ ሴቶች የሚያጋጥማቸውን የመደፈር አደጋ አንድ የፍርድ ውሳኔ የተሰጠበትን የፍርድ ሒደት (‘ኬዝ’) እንደማሳያ በማድረግ አቅርበዋል። ከዚሁ ርዕስ ጋር በተያያዘ አንድ በሕፃናትና ሴቶች ጥቃት ላይ ከሚሠራ የፖሊስ ባልደረባ ያገኙትን የፍርድ ቤት ውሰኔ መረጃ በማኅበራዊ ትስስር መድረክ አጋርተውት ያገኙት ምላሽ ግን አሁንም ችግሮቻችንን ከመጋፈጥና ከመፍታት ይልቅ መካድና ማስመሰልን ስለመምረጣችን ማሳያ ነው ሲሉ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።

 

ከታመመች ጓደኛዬ ጋር ወደ ሐኪም ቤት ስንሔድ የሕክምና ካርድ አውጥተን፤ ተራ ጠብቀን ወደ ዶክተሩ ቢሮ ስንገባ “ታማሚዋ ብቻ ትግባ ውጪ ጠብቂ” ስለተባልኩ ጓደኛቼ ከዶክተሩ ጋር ከነበረችበት ክፍል ፊት ለፊት ካለው ወንበር ተቀምጬ ቴሌቪዥን እያየሁ መጠባበቅ ጀመርኩ። ትንሽ ቆይተው ወጡና ወደ ሌላኛው ክፍል ገብተው በሩ ተዘጋ። ከዚያ በሩ ሳይከፈት ከአርባ ደቂቃ በላይ ሆነው። ለምን ዘገየች ምን ሆና ነው ብዬ ወደ ተዘጋው በር ሔጄ ጆሮዬን አስጠግቼ ስሰማ የሚያቃስት የወንድ ድምጽ ሰማሁ። ግራ ገባኝ፤ ወዲያው “ምን እያደረከኝ ነው” የሚል ድምጽ ሰማሁ። አሁን ታግሼ መቆየት ተሳነኝና የበሩን እጄታ ይዤ ለመክፈት ስሞክር ከውስጥ ተቆልፏል አንኳኳሁ፤ ዶክተሩ በሩን ከፈተውና ወደ ወንበሩ ሔዶ ተቀመጠ።

“ወደ ውስጥ ስገባ ክፍሉ የተዘበራረቀ የታፈነ ሽታ ያለው ነበር። ጓደኛዬን ከምርመራ አልጋው ቁጭ ብላ፣ ፊቷ ቀልቶ ደንግጣ አየኋት። ዐይኖቿ እንባ አቅርረው ደንዝዛም ነበር። ቶሎ ብላ እጄን ያዘችኝ ዶክተሩም ተደናግጦ ብዕር የያዙት እጆቹ ይንቀጠቀጡ ነበር ገልመጥ እያለም በፍርሀት እያየን ነበር አንድ ድርጊት እንደፈጸመና እንደታወቀበት ዓይነት ነገር ይመስል ነበር።”

ይህ አንዲት ሕክምና ፍለጋ ከጓደኛዋ ጋር ወደ ሆስፒታል የሔደች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በሐኪሟ አስገድዶ መድፈር ከተፈጸመባት በኋላ ምስክር የሆነች ጓደኛዋ ለፖሊስ ከሰጠችው ቃል የተወሰደ ነው።

ፖሊስ የተበዳይዋንና የጓደኛዋን ቃል እንደሰማ ጊዜ ሳይወስድ አባላቱ የወሰዱት እርምጃ ቢኖር ተበዳይን በቀጥታ ወዲያው ወደ ጋንዲ ሆስፒታል ወስደው ማስመርመር ነበር። ውጤቱ ሲደርስም ሆስፒታሉ የሰጣቸው መረጃ “የግል ተበዳይ ብልት አዲስና ትኩስ የክብረ ንጽሕና መገርሰስ ያሳያል የብልቷ የውስጠኛው ክፍል ላይ የመላላጥና የመሰንጠቅ የመቅላት ጉዳትን ያሳያል በውስጠኛው የማሕጸኗ አካባቢ ላይ የወንድ የዘር ሴሎችን (ስፐርም) ተገኝቷል” የሚል ነበር።

የምርመራ ቡድኑ አባል የነበረ ፖሊስ እንዳጫወተኝ ቀጣዩ የፖሊስ እርምጃ ተጠርጣሪ ሐኪሙ ለታማሚዋ መድኀኒት ካዘዘበት ወረቀት ላይ ሥሙን ከለየ በኋላ ለወንጀል ተከታታይ ሲቪል አባላት ደውሎ የተከሳሹን ሥም ጠቅሶ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ማድረግ ነበር።

ሆኖም ሐኪሙን ለመያዝ የተንቀሳቀሰው ኀይል የሚሠራበት ቦታ ሲደርስ የተሰጠው መልስ “ተከሳሹ ዶክተር ቅድም ልብሱን ቀይሮ ከክሊኒኩ ጠፍቶ ሔዷል” የሚል ነበር።

ታሪኩ ጉዳት ከደረሰባት ወጣት አንጻር ሲተረክ ደግሞ
“አዕምሮዬ ምንም ነገር እንድጠራጠር አልፈቀደልኝም ምክንያቱም እኔ አሁን የማስበው ከህመሜ እንዲያላቅቀኝ አንድ ሕዝባዊ ኀላፊነት ካለበት አንድ ዶክተር ጋር እንዲረዳኝና ሙያዊ ኀላፊነቱን በአግባቡ ከሚወጣ ሕጋዊ ክኒሊክ ውስጥ እንዳለሁ ብቻ ነው የማውቀው።
ሐኪሙ ከህመምተኛ መተኛው አልጋ ላይ እንድቀመጥ አዘዘኝና ወለም ያለኝን የግራ ክንዴን መነካካት ጀመረ አብጦ ስለነበር ህመም ተሰማኝና ጮሁኩኝ በጣም ስለተጎዳሽ አጥንቶችሽን ወደ ነበሩበት ስፍራ ለመመለስ የማደንዘዣ መርፌ ያስፈልግሻል አለኝ እኔም ተስማማሁ መርፌውን አንስቶ ክንዴ ላይ ወጋኝ በቃ ትንሽ ከቆየሁ በኋዋላ ራሴን አላውቅም።

የት እንደነበርኩ ሳላውቅ ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ዐይኖቼ ተገለጡ። ነገር ግን ነገሮች በሰመመን ይታዩኝ ነበር። ከወደ ጡቴ አካባቢ ህመም ተሰማኝ ከላይ የለበስኩት ልብስ እንደወለቀና ራቁቴን ከአልጋው ላይ መተኛቴ ከጀርባዬ በኩል ያለው የቆዳ ፍራሽ በጣም ይቀዘቅዘኝ ነበርና ምንም ልብስ አለመልበሴ ይታወቀኛል።
እንደምንም ቀና ብዬ ስመለከት ዶክተሩ ሱሪውን ዝቅ አድርጎ እየገፋኝ አየሁት ህልምም መሰለኝ ወይም ደግሞ የማደንዘዣው መርፌ የፈጠረብኝ ቅዠት ነውም ብዬ አሰብኩ። ግን ያሰብኩት ነገር አልነበረም ብቻ ወደ ብልቴ አካባቢ የበዛ ህመም ይሰማኝ ነበር። ምክንያቱም እኔ ከዚያ በፊት ከማንም ጋር ወሲብ ፈጽሜ አላውቅም ነበር። የማስበው የቤት ሠራተኛ ሆኜ ተቀጥሬ የምረዳቸው ቤተሰቦቼን ብቻ ነበር። እየቆየሁ በደምብ ነቃሁ።

“ዶክተር ምን እያደረከኝ ነው?” ብዬ ጮኬ ጠየቁት እሱ መንቃቴን አላወቀም ነበርና ደንግጦ ሱሪውን ለብሶ የኔንም ቀሚስ አስተካክሎ ደንግጦ በሩን ከፈተና ወንበሩ ላይ ሔዶ ምንም እንዳላደረገ ቁጭ አለ።

ጓደኛዬ በሩ ሲከፈት እኔ ወደ ነበርኩበት ክፍል ገባችና “ምን አደርግሀት ነው ያለቀሰችው?” ስትል አንቧረቀችበት እሱም እየፈራ እየተባ ምን አደርጋታለሁ ህመምዋ ከባድ ስለሆነ አሟት ይሆናል ሲል መለሰላት። አባቴን ጥሩልኝ ብዬ ስጮህ ጓደኛዬ አባቴጋ ደወለች። ቀጥሎ ዶክተሩ የክሊኒኩን የጥበቃ አባላቱን ጠራቸው “እነዚህን እብዶች አስወጡልኝ!” ሲል በቁጣ አዘዛቸው እነሱም እንደታዘዙት እያዳፉ ከክሊኒኩ አስወጡን አባቴም ደረሰ።

ፖሊስ የታዳጊዋን የመደፈር የሕክምና ማስረጃ ካየ በኋላ ሁሉም ማስረጃዎች በደፋሪው ዶክተር ላይ ተሰባስቦ አበቃ ቀጣዩ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከፍርድ ቤት ማዘዣ ወስዶ ማፈላለጉ ላይ ተሰማራ።

ነገር ግን ዶክተሩ ወደ ሥራ ገበታውና ወደ መኖሪያ ቤቱ ከዚያን ቀን ወዲህ አላመራምና የድብብቆሽ ጨዋታውን መርጦ በመሰወሩ ቶሎ ማግኘት አልተቻለም። ሆኖም ፖሊስ በዙሪያው ያሉ የቅርብ ወዳጆቹን እንደ ወጥመድ በመጠቀም ሌት ከቀን ማሳደዱን ተያያዝው።

እንደምንም በቁጥጥር ሥር ዋለና በፈጸመው ከባድ ወንጀል እና የአስገድዶ መድፈር ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርቦ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው ሲል ወሰነና በሃያ አንድ ዓመት እስራት ፈረደበት።

ይሔ አንድ የምርመራ ቡድን አባል የሆነ ፖሊስ በሕክምና ተቋማት እየተስፋፋ የመጣውን አስገድዶ መድፈር በሚመለከት እስቲ ለሚመለከታቸው አጋሩ በማስተማር በማንቃት ወጣት ሴቶች ወደ ሕክምና ሲሔዱ ከሰዎች ጋር እንዲሔዱ እንዲሁም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያግዛል በሚል ያካፈለን ታሪክ ነው።
ይሔን ታሪክ ትዊተር ላይ በጥቅሉ ሳካፍል ስለተሰጠኝ ምላሽና አሁንም ችግሮቻችንን ከመጋፈጥና ከመፍታት ይልቅ መካድና ማስመሰል የተሸለ እንዲሆን ስለመምረጣችን ምሳሌ ከማስከተሌ በፊት የጻፍኩትን መረጃ ላጋራችሁ።

“ትናንት በሕፃናትና በሴቶች ጥቃት ላይ ከሚሠራ የፖሊስ ባልደረባ የሰማሁት። ሴት ታካሚዎችን ማደንዘዣ መርፌ እየወጉ መድፈር ተበራክቷል። እሱ በሚሠራበት ክፍለ ከተማ ብቻ ባለፈው ዓመት ስድስት ‘ኬዞች’ ፍርድ ቤት ቀርበው እልባት አግኝተዋል። ከተደፋሪዎቹ አንዷ እርጉዝ ነበረች። ሌሎቹ ኹለቱ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች። ኹለት የመንግሥት ሆስፒታሎችና አንድ የጤና ጣቢያ እንዲሁም አንድ የግል ክሊኒክ ወንጀል የተፈጸመባቸው ቦታዎች ናቸው፣ ባለሙያዎች ለባልደረቦቻቸው አድልተው ታይተዋል። ሕክምና ቦታ ስትሔዱ ጥንቃቄ አድርጉ። ቢቻል ከቤተሰብና ጓደኛ ጋር ሒዱ የምርመራ ክፍልም ብቻችሁን እንዲቆለፍባችሁ አትፍቀዱ። መርፌ ተወጉ ስትባሉ ደጋግማችሁ አስፈላጊነቱን ጠይቁ።”

ሃምሳ ሦስት የሚሆኑ የትዊተር ተከታዮቼ መልሰው ባጋሩትና ከመቶ በላይ አይተው እንደወደዱት በገለጹት በዚህ ትዊተት ከአስተያየት ሰጪዎች የነበሩት ምላሾች የተለያዩ ነበሩ። የተወሰኑትን ለማየት ያህል፡-

“በሥመ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ! ወይ ጤና ጥበቃ ሚንስትር? ምን የማይሰማ ጉድ አለ?? እንደዚህ ዓይነቶቹን ቃል ኪዳን አፍራሾችን የሕክምና ባለሙያዎች ወዲያውኑ ለሕግ አቅርቦ እኔን ያየህ ተቀጣ እንዲሉ ማድረግ አለበት! ወይ ክፉ ጊዜ?”
“እነዚህን ማስረጃ ለመስጠት ፍላጎት የሌላቸውን የጤና ባለሙያዎች እነሱም በወንጀሉ ተባባሪ ናቸው።
“በጣም አሳፋሪ፣ የሕክምናን ቃለ መሐላ ክህደት፣ የሕክምና ባለሙያን ሥነ ምግባር የሚጥስ የሚያበላሽ ኢሰብኣዊ ድርጊት ፣ ወንጀል ነው።”
“አንዳንድ እንዲህ የዘቀጡ ሞያተኛ ተብዬዎች በሚሠሩት ዝቅጠት ሳቢያ ብዙኀኑ ነጭ ለባሽ ባለሞያ በእነዚሁ አዘቅቶች ሲፈረድበት ይኖራል!! ይህም አንዱ ገጽታ ነው…ብዙ ይቀረናል።”
“እምነት በሚጣልበት ተቋም እንዲህ በደል መፈጸሙ ያሳዝናል።”
ሌሎች የተገለጸውን እውነትነት የተጠራጠሩ ወይም ፈጽሞ አይሆንም ያሉም ነበሩ።
“ይሔ እውነት ከሆነ አሰቃቂ ነው። ግን እንዲህ ዓይነት ታሪክ ብታጣሪ ነው የሚሻለው። እሳት ላይ ቤንዚን ለመጨመር የሚፈልጉ ስላሉ። የት ነው ለመሆኑ ይህ የተፈጠረው?”
“ምናልባት ሴቶች የተደፈሩት ሊስወርዱ ሔደው ይሆናል።”
“ስለጠቀስሻቸው ኬዞች ግን እርግጠኛ ነሽ? ማነው የሚከታተላቸው? እርግጠኛ ሳትሆኚ የጤና ባለሙያዎችን መወንጀል ትክክል አይደለም። ታሪኩ አላሳመነኝም ምክንያቱም ማደንዘዣ መድኀኒቶች በሐኪም ብቻ ነው የሚታዘዙት”

ከላይ የጠቀስኩት ታሪኩን ያጋራኝ የፖሊስ ባልደረባ ግን እሱ በሚሠራበት ክፍለ ከተማ ፖሊስ ክትትል ካደረገባቸው መዝገቦች ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ስድስት ጉዳዮች ፍርድ ቤት ቀርበው የፍርድ ውሳኔ እንደተሰጠባቸው ገልጾልኛል። ወንጀሉ የተፈጸመባቸው ደግሞ የመንግሥትም የግልም ሕክምና መስጫ ተቋት ናቸው።
ሌሎችም አስተያየቶች እኛም ሐኪም ነን ብለው በፍጽም ውሸት ነው ብለው የሞገቱ ነበሩ፤ ሌላው ቀርቶ ባለፈው ስንት ሰው ሞቶ አንቺ ስለ መደፈር ታወሪያለሽ ወይ ያለ ነበረ። በአንጻሩ ደግሞ የአንዲት ሴት የሥራ ባልደረባውን ገጠመኝ ያጋራ ሰው በሕክምና ላይ በደረሰባት መደፈር ለእርግዝና ስለተዳረገችና በወቅቱ ራስዋን ስታ ስለነበር የተፈጸመውን ድርጊት ያለ ወንድ ግንኙነት (እስዋ በወቅቱ ለረጅም ጊዜ ግንኙነት አድርጋ የማታውቅ በመሆኑ) ማርገዟ አስደንግጧት ስታስብ ያንን አጋጣሚ እንደምትጠረጥር አካፍሏል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ በአንድ የሕክምና ትምህርት የሚሰጥ ተቋም ተለጥፎ የነበረን አንድ ደብዳቤ ነበር ከአስተያየቱ ጋር ያሰፈረው። ደብዳቤው ለአንድ የውስጥ ደዌ ትምህርት ክፍል ተለማማጅ የተጻፈ ሲሆን ይዘቱ የሚለው ተማሪው የጽንስና ማሕጸን ትምህርት ክፍል ሔዶ ራሱን የማሕጸን ሐኪም በማስመሰል በሴቶች ላይ ተደጋጋሚ የመድፈር ሙከራ በማድረጉ ከትምህርቱ መታገዱን የሚገልጽ ነበር።

ስለ እንደዚህ ዓይነቱ የማይጠበቅ ወንጀል የራሴን ትንተና ለዛሬ ባቆየው ይህንን ባጋራሁበት ወቅት አዲስ ማለዳን ጨምሮ ኤፍ ኤም ጣቢያዎችና ሌሎች ሚዲያዎች ጉዳዩ ላይ የምርመራ ጋዜጠኝነትና ቀጣይ ዘገባ ለመሥራት ፍላጎት ስላሳደሩና ተጨማሪ መረጃዎችም ስለወሰዱ እያመሰገንኩ በእነዚህ ሚዲያዎች የተጠናከረና የተሟላ ዘገባ የተሻለ ግንዛቤ እንዲሁም ለሚመለከተው የተቋማቱ ተቆጣጣሪ አካል እርምጃ ለመውሰድ የሚሆን ግብዓት ይገኛል፤ በዚህም ፈውስ ፍለጋ የሚሔዱ ሴቶች ተጨማሪ ህመም አያገኛቸውም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here