የአማሮ ልዩ ወረዳ ፍትህ ፅ/ቤት በበኩሉ ”የታራሚዎች ቅሬታ የተሳሳተ ነው” ብሏል
ረቡዕ ግንቦት 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ኬሌ ተብሎ በሚጠራ ፖሊስ ጣቢያ፤ ከ125 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ያለፍርድ ከአራት ወር እስከ አንድ ዓመት ታስረው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
እስር ላይ ከሚገኙ መካከል የአማሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ፅሕፈት ቤት ባለሙያ እንደነበሩ የገለጹትና ቅሬታቸውን በስልክ ለአዲስ ማለዳ ያቀረቡት መንግሥቱ መለሰ ይገኙበታል፡፡ እርሳቸውም የካቲት 14/2015 ከሚሠሩበት ጤና ተቋም ‹‹የጤና ተቋሙን መድኃኒት ለግል ጥቅም እየተጠቀመ ነው›› በሚል እንደተወሰዱ ገልጸዋል፡፡
ባለሙያው አክለውም ከ125 በላይ ሰዎች ያለምንም ፍርድ በፖሊስ ጣቢያው ታስረው እንደሚገኙ በመግለጽ፤ ከታሰሩ አራት ወራትን ያስቆጠሩ ቢሆንም እስካሁን ክስ እንዳልተመሰረተባቸው ተናግረዋል፡፡
የአማሮ ልዩ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ታጋሽ ሰጠኝ እንዲሁ፤ የተከሰሱበትን ጉዳይ ሳያውቁ በኬሌ ፖሊስ ጣቢያ ያለ ክስ እና ፍርድ ከታሰሩ ስድስት ወራት ያስቆጠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኬሌ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት እስረኞች አብዛኛዎቹ የመንግሥት ሠራተኞች መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ ምንም ዓይነት መፍትሄ ሳይሰጣቸው አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም፤ በፖሊስ ጣቢያው የሚገኙት መፍትሄ ሳያገኙ ሌሎች ሰዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየገቡ ናቸው ተብሏል። በልዩ ወረዳው በፍትህ እጦት የሚሰቃዩ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
የአማሮ ልዩ ወረዳ ፍትህ ፅ/ቤት ሃላፊ ሙሉቀን በቀለ በበኩላቸው፤ መንግስቱ መለሰ እና ሌሎች ኹለት ሰዎች የሕክምና መድኃኒት ግዥና አቀራረብ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዉ በኦዲት ግኝት በቁጥጥር ሥር ዉለዉ የወንጀል ክስ በእጃቸው ላይ ደርሷል ብለዋል።
ተከሳሽ ታጋሽ ሰጠኝ ደግሞ በሰዉ ነፍስ ግድያ ወንጀል ተጠርጥረዉ የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ ለዐቃቤ ሕግ ተላልፎ ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፤ በተከሰሰበት ክስ መከላከያ ማስረጃ አቅርቦ እንዲያሰማ ለሰኔ 12 ቀን 2015 የተቀጠረለት የባሕል ጽ/ቤት ኃላፊ የነበረና በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ በሕጋዊ መንገድ በፖሊስ ማረፍያ ቤት ቀጠሮዉን እየተጠባበቀ የሚገኝ እንጂ ያለክስ እና ያለ ምክንያት የታሰሩ አለመሆኑ ተረጋግጧል።
ስለሆነም አብዛኛዎቹ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ ሰዎች የፈጸሙት ወንጀል ሳይታወቅ ለወራት በፖሊስ ማረፍያ ቤት ታስረዉ እንደሚገኙ የተናገሩት ከአማሮ ወረዳ ፍርድ ቤት በ2 የክስ መዝገቦች 3 ሰዎች፣ ከኬሌ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ጽ/ቤት በአንድ መዝገብ 5 ሰዎች፣ ከጤና ጽ/ቤት 2 ሰዎች በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረዉ ተከሰዉ በቀጠሮ ያሉ ናቸው ተብሏል።
የባሕል ጽ/ቤት ኃላፊ ታጋሽ ሰጠኝ እና ሌሎቹ ታራሚዎች በሰዉ ነፍስ ግድያ ወንጀል ተከሰው በቀጠሮ ያሉ እንጂ የመንግሥት ሠራተኛ ስለሆኑ ተለይተዉ የታሠሩ የሌሉ መሆኑን የአማሮ ወረዳ ፍትህ ፅ/ቤት ሃላፊ ሙሉቀን በቀለ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።
እስር ቤት ለሚገኙ ኹሉም ሰዎች ምግብ እና የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠበት ሁኔታ የለም የተባለ ሲሆን፤ የፍርድ ውሳኔ ተሰጥቷቸው ማረሚያ ቤት ሲሄዱ አገልግሎቱን የሚያገኙ ይሆናል ተብሏል።



