በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በዳውሮ ዞን ዲሳ ወረዳ ከ200 የሚበልጡ መምህራን የወር ደመወዝ እየተቆረጠ ነው በሚል ጥያቄ ሲያስነሳ የነበረውን የመምህራን ደመወዝ፤ ተበድሮ ሊከፈል መሆኑን የዲሣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የዲሣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ እዮብ ቶማስ ከ211 መምህራን መካከል ባለፈው መስከረም ወር የ14 ርዕሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች የደመወዛቸው 50 በመቶ የተቆረጠባቸው፤ በበጀት እጥረት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ወረዳው ችግሩን ተረድቶ ደመወዛቸውን ለተቆረጠባቸው ተበድሮ ለመክፈል ውሳኔ ማሳለፉንም አስተዳዳሪው ጠቁመዋል፡፡
ነገር ግን ከ14ቱ ርዕሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ውጭ በሌሎች መምህራን ላይ አስር በመቶ ደመወዛቸው ያለአግባብ እየተቆረጠ ነው ተብሎ የሚቀርበው ቅሬታ የተሳሳተ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በሌሎች መምህራን ደመወዝ ላይ አስር በመቶ እየተቆረጠ መሆኑን ለሚዲያዎች ሲገልጽ የነበረውን የዲሣ ወረዳ መምህራን ማኅበር ሊቀመንበር ስንታየው ስለሺ፤ ባለፈው አርብ ሰኔ 29/2015 ከመኖሪያ ቤቱ በፖሊሰ ተወስዶ መታሰሩን አስተዳደሪው ተናግረዋል፡፡
ሊቀመንበሩ የታሰረው በኹሉም ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ያለውን የትምህርት ስርዓት እንዲቋረጥ በማነሳሳቱና ለሚዲያዎች በመምህራኖች ላይ ከደመወዛቸው 10 በመቶ እየተቆረጠ ነው በማለቱ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዲሳ ወረዳ መምህራኖች በበኩላቸው፤ ከግንቦት ወር ጀምሮ የደመወዛቸው አስር በመቶ እየተቆረጠ መሆኑንና ለእስር እየተዳረጉ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናገረዋል፡፡
ደመወዙ ኢ-ፍትሃዊ እና ሕግን ባልተከተለ አሰራር ያለፈቃዳቸው እንደሚቆረጥ ጠቁመው የደመወዝ ክፍያው በጥሬ ገንዘብ ስለሚፈጸም ብሩ ለምን ጉዳይ እንደሚቆረጥ የሚገልጽ ደረሰኝ እንደማይሰጥ አክለዋል፡፡
ድርጊቱ መምህራኑን ለከፍተኛ የኑሮ ቀውስ በመዳረጉ ለምን በለው የሚጠይቁ መምህራንን ማሰር እና ማሳደዱ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡



