በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በጸጥታ ችግር ምክንያት ነዋሪዎች እየተፈናቀሉ መሆኑ ተገለጸ

0
375

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ፤ በጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሥም ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ ታጣቂዎች በፈጠሩት የጸጥታ ስጋት የኩጂ እና ጎንጎ ቀበሌ ነዋሪዎች የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎች ሰምታለች።

በዚህም የኹለቱ ቀበሌ ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ሃብት ንብረታቸውን ትተው ወደ ቡለን ወረዳ ዋና ከተማ ተፈናቀለው መሄዳቸው ተነግሯል።

“ታጣቂዎቹ በኩጂ እና ጎንጎ ቀበሌዎች በየዕለቱ ስብሰባ ያደርጋሉ፤ ነዋሪውም አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ዛቻና ማሰፈራሪያ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡” ሲሉ ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎም ወደ ወረዳው ዋና ከተማ የገቡ ተፈናቃዮች ማረፊያ የሚሆን የሚከራይ ቤት ባለማግኘታቸው ምክንያት በከተማው በሚገኝ የአውቶቢስ መነሃሪያ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

ታጣቂዎቹ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጽሙት ተደጋጋሚ ጥቃት ምክንያ ብዙ ሰዎች መገደላቸው እንዲሁም መፈናቀላቸው ይጠቀሳል።

በቅርቡም (ሰኔ 30/2015) በመተከል ዞን ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ፓዊ መወጫ ቻይና ካምፕ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ፤ 18 ሰዎች መገደላቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡

ከኹለት ዓመት በፊት እንዲሁ (ታኅሣሥ 13/2013) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ታጣቂዎቹ ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ሌሊት ላይ በፈጸሙት ጥቃት 207 ሰዎች መገደላቸውን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይ ራሳቸውን የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ እንዲሁም የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች በተለያዩ ጊዜ በሚፈጽሙት ጥቃት፤ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ መቆየታቸው ይነሳል።

ታጣቂዎቹ በሰላም ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው ለመኖር ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የሰላም ስምምነት አድርገው የነበረ ቢሆንም፤ አብዛኞቹ እስካሁን ድረስ ትጥቅ አለመፍታታቸውና በመንግሥት አመራሮች ጭምር የተለያየ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚንቀሳቀሱ የክልሉ ነዋሪዎችና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሲገልጹ ይደመጣል።

አዲስ ማለዳ በቡለን ወረዳ በዚህ ወቅት ነዋሪዎችን እያፈናቀለ ባለው የጸጥታ ችግር ዙሪያ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ማብራሪያ ለማግኘት በተደጋጋሚ ብትደውልም ስልክ ባለመነሳቱ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here