በአማራ ክልል ለሚሊሻና ለፖሊስ ሠላም አስከባሪ ኃይል እንዲሁም ለመደበኛ ፖሊስ ኃይል ከትናንት ሐምሌ 10/2015 ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ሊሰጥ የነበረው ስልጠና፤ የተወሰኑ የሚሊሻ አባላት ስልጠናውን ለመውሰድ ፈቅደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡
ስልጠናው በክልሉ 18 ዞኖች ለሚገኙ የሚሊሻና የፖሊስ ሰላም አስከባሪ አባላት እንዲሁም ለመደበኛ ፖሊስ ኃይል ለመስጠት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ “ስለስልጠናው በቂ መረጃ ሳይሰጠን አንሰለጥንም” ያሉ የሚሊሻ አባላት በመኖራቸው እንዲራዘም መደረጉን መረዳት ተችሏል።
የክልሉ መንግሥት የስልጠናው ዋነኛ ዓላማ በክልሉ በየጊዜው የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ነው መሆኑን ቢገልጽም፤ “ችግር የሚፈጥረው አካል ማነው ለሚለው ጥያቄ፤ ቅድሚያ ማብራሪያ ሊሰጠን ይገባል” በማለት ስልጠናውን ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልሆኑ የሚሊሻ አባላት መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡
የስልጠናው ዓላማ የመንግሥት የጸጥታ አካላቱ ከፋኖ አባላት ጋር እንዲዋጉ ታስቦ ከሆነ፤ ሃሳቡን የማይቀበሉ የሚሊሻ አባላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ተመላክቷል።
በዚህም በስልጠናው ወቅት ችግር ሊፈጠር እንደሚችል አመላካች ነገር በመገኘቱ ስልጠናው እንዲራዘም መደረጉን ነው አዲስ ማለዳ ከሚሊሻ አባላትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት መረዳት የቻለችው።
በሌላ በኩል ሥማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በክልሉ የሚገኙ አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ፤ ሥልጠናው የተራዘመው ለሥልጠናው የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በጊዜ ባለመጠናቀቃቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
ስልጠናው የሚሰጠው ለ40 ሺሕ 486 ሰልጣኞች መሆኑን ጠቁመው፤ “ለሰልጣኞች ምግብ እና የማረፊያ ቦታ ባለመመቻቸቱ ነው እንዲራዘም የተደረገው።” ብለዋል፡፡
ለስልጠና የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ በመሆኑም አንድ ሳምንት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ስልጠናው እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።
ከትናንት ሰኞ ሐምሌ 10/2015 እስከ እሁድ ሐምሌ 17/2015 ለተከታታይ ሰባት ቀናት ሊሰጥ ታስቦ ለነበረው የጸጥታ አካላት ስልጠና፤ የክልሉ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ጠይቋል።
ስልጠናው የጸጥታ ኃይሉን በክልሉ በየጊዜው ለሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል መንገድ ለማጠናከር ያስችል ዘንድ እንዲሁም በወታደራዊ ስነምግባር፣ እውቀትና ክህሎት ለማብቃትና በስነልቦና ለማዘጋጀት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።



