የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በትግራይ ክልል ኹሉም ትምህርት ቤቶች እንደማይሰጥ ተገለጸ

0
795

በትግራይ ክልል በኹሉም ትምህርት ቤቶች የአማርኛ ቋንቋ እየተሰጠ አለመሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ ከ2012 ጀምሮ ትምህርት ተቋርጦ በመቆየቱ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት ዘርፎችን እንዳይሰጡ መደረጉን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የትግራይ ሕጻናት ማግኘት የሚገባቸውን ትምህርት አላገኙም ያሉት ኃላፊው፣ ብዙዎች አምስተኛ ክፍል መሆን ሲገባቸው አንደኛ ክፍል እንደሚማሩ እንዲሁም የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት እየተማሩ ያሉት ዩኒቨርሲቲ መመረቅ የሚገባቸው ተማሪዎች ናቸው ብለዋል።

ስለሆነም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ እና ለወደፊት ህይወታቸው ይጠቀማቸዋል ተብሎ የሚታሰቡትን የትምህርት ዘርፎችን ብቻ እንዲማሩ እያደረግን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአማርኛ ቋንቋ ጨምሮ የተወሰኑ የትምህርት ዘርፎች በትምህርት ቤቶች እንዳይሰጡ የተደረገውም፣ ተማሪዎች እድሜያቸው አስተምሯቸዋል ተብሎ ሰለሚታሰብ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ አካባቢ ሳይንስ፣ ሙዚቃ፣ ስነጥበብ እና ሌሎች ትምህርቶች እንዳይሰጡ መደረጉን ገልጸው፣ ከ2012 እስከ 2015 ድረስ የተቋረጡትን ሰባት መንፈቀ ትምህርቶችን ለማካካስና ቶሎ ለመጨረስ ጠቃሚ ናቸው ተብሎ የሚታሰቡት የትምህርት ዘርፎችን ብቻ ለማስተማር ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

የአማርኛ ቋንቋ በክልሉ ትምህርት ቤቶች አለመሰጠቱን በተመለከተ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንድ የተማሪ ወላጅ ‹‹አማርኛ ቋንቋ የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ በመሆኑ ልጆቻችን ሊማሩት የሚገባ ነው፡፡ የትግራይ ልጆች ቋንቋውን መናገር፤ ማንበብ እና መጻፍ ካልቻሉ እንደሌላው የኢትዮጵያ ዜጋ በአገሪቱ ተዘዋውረው ሥራ መሥራት እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል›› ብለዋል፡፡

አክለውም፤ በክልሉ የአማርኛ ቋንቋ መሰጠት የሚጀመረው ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ኹሉም ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ እንዳይማሩ መደረጉ የትግራይ ተወላጆች ቋንቋውን እንዲረሱት ያደርጋል ሲሉ ተደምጠዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here