በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ዕሁድ ሐምሌ 16/2015 ከምሽት ኹለት ሰዓት ገደማ የፖሊስና ሚሊሻ አባላት ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ የጸጥታ አካላት እና ንጹሃን መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
በከተማው ፒያሳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የምሽት ተረኛ በነበሩ የፖሊስና ሚሊሻ አባላት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ መንገድ ዳር በቆሎ ስትጠብስ የነበረች የኹለት ልጆች እናት እና ኹለት ወጣቶች መገደላቸው ተጠቅሷል።
ለሰዓታት በቆየው የተኩስ ልውውጥ ከሟቾች ባለፈ የጸጥታ አካላት ላይም የአካል ጉዳት መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።
የወልዲያ ከተማ ከንቲባ ዱባለ አብራሬ በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ፤ ዕሁድ ምሽት በከተማዋ በነበረው የተኩስ ልውውጥ አንዲት በቆሎ በመጥበስ የምትተዳደር የኹለት ሕጻናት እናት ሕይወት በአሳዛኝ ሁኔታ ማለፉን ገልጸው፤ ተኩሱ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት በኋላ መረጋጋቱን አስታውቀዋል።
በተኩስ ልውውጡ ስለተገደሉት ሌሎች ሰዎችና የጸጥታ አካላት ለቀረበላቸው ጥያቄ “በጸጥታ አካላትና በንጹሃን ላይ ስለደረሰው ጉዳት በጸጥታ አካላት በኩል መግለጫ እንሰጣለን፡፡” ሲሉም ከንቲባው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።



