በትግራይ ክልል የሚገኙ የሜቴክ ሠራተኞች ለኹለት ዓመታት ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው ተናገሩ

0
417

ረቡዕ ሐምሌ 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የሚገኘው የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ሜቴክ ሠራተኞች ለ24 ወራት ደምወዝ እንዳልተከፈላቸው እና በዚሁ ምክንያት ለከፋ ረሀብ መጋለጣቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለኹለት ዓመት ደሞዝ ያልተከፈላቸው ሠራተኞች በኢንጂነሪንግ ግሩፑ ሥር ከሚገኙ ፋብሪካዎች መካከል የመቀሌ ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ፣ ውቅሮ ኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማምረቻ እና መገጣጠሚያ ፋብሪካ እንዲሁም መቀሌ ኢንጂን ፋብሪካ ከ440 በላይ ሠራተኞች መሆናቸው ተገልጿል።

በፋብሪካዎቹ የሚሰሩት ሠራተኞች አብዛኞቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እና ሌላ የገቢ ምንጭ የሌላቸው በመሆኑ ለከፍተኛ ረሀብ እና ችግር መዳረጋቸውን ነው የገለጹት።

“ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከተቋማቱ አስተዳደር አካላት ምላሽ ለማግኘት በአካል፣ በደብዳቤ እንዲሁም በስልክ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምንም አይነት መፍትሄ ሊሰጠን የቻለ አካል የለም፡፡” ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

“በመሆኑም ሰኞ ሐምሌ 24/2015 ባለ ስድስት ነጥብ መግለጫ አውጥተን ለኢንጂነሪንግ ግሩፑ እና ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስገብተናል” ያሉት ሠራተኞቹ፤ “ምላሻቸውን በሚቀጥሉት አምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ያሳውቁናል ብለን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡” ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም መሠረት የኹለት ዓመታት የሠራተኛ ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም ባስቸኳይ እንዲከፈላቸው፣ እንዲሁም በትግራይ የሚገኙ ሦስቱ ፋብሪካዎች ተጠግነው እና ማሽነሪዎች ተሟልተው ወደ ሥራ ለመግባትም ጥያቄ አቅርበናል ነው ያሉት።

ይህ የማይሆን ከሆነ በአገሪቷ አሰሪና ሠራተኛ አዋጅ መሰረት የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን ሲሉም አስረድተዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ሠራተኞች ባቀረቡት ቅሬታ ማብራሪያ ለማግኘት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር አንዱ ለሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ብትደውልም፤ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናውቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here