“በተፈጸመው የድሮን ጥቃት 70 ሰዎች ሞተዋል፣ ከ55 በላይ ሰዎች ቆስለዋል” የዞኑ አመራር

"ሆስፒታል መጥተው 26 ሰዎች ሞተዋል፣ ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ የሞቱም አሉ" የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ

0
566

ማክሰኞ ነሐሴ 9 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተሰላም ከተማ እሁድ ነሐሴ 07/2015 ከቀኑ አምስት ሰዓት ገደማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በትንሹ 70 ሰዎች መሞታቸውንና ከ55 በላይ ሰዎች ቆስለው ወደ ሆሰፒታል መላካቸውን ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዞኑ የሥራ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው በመሀል ከተማ በሚገኘው አደባባይ በጭነት መኪና ላይ በነበሩ ወጣቶች ከመኪናው እየወረዱ ባሉበት ወቅት መሆኑን ነው የሥራ ኃላፊው የተናገሩት።

በመኪናው ውስጥ ተሰባሰበው የነበሩት የከተማዋ ወጣቶች፤ ሕጻናት እና የኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መሆናቸውን በመግለጽም፤ “በተፈጸመው የድሮን ጥቃት በትንሹ የ70 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን አረጋግጠናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በጥቃቱ ከሞቱ ሰዎች በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኙ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ አንበሳ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዋሽ ባንክ ሕንፃዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተጠቁሟል፡፡

የሥራ ኃላፊው አክለውም፤ ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 06/2015 በቡሬ ከተማ በነበረው የተኩስ ልውውጥ በከባድ መሳሪያ አራት የቤተሰብ አባላት መገደላቸውን ገልጸዋል።

የፍኖተ ሰላም አጠቃላይ ሆሰፒታል ሥራ አስኪያጅ ማናየ ጤናው፤ እሁድ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት 26 አስከሬኖች እና ከ55 በላይ ቁስለኞች ወደ ሆሰፒታል መግባታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

“የሞቱትም የቆሰሉትም የታጠቁ ወታደሮች አይደሉም።” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ “ወጣቶችና ህጻናት ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

በጥቃቱ ሆሰፒታል የመጡት 26 አስክሬኖች ይሁኑ እንጂ ጥቃቱ ከተፈጸመበት ቦታ ሞተው ወደ ቤተሰቦቻቸው የተወሰዱ መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አክለውም፤ ወደ ፍኖተሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል ከዚህ በፊት በደንበጫ እና በቡሬ አካባቢ በነበረው የተኩስ ልውውጥ ከ160 በላይ ቁስለኞች መግባታቸውን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቀት የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ እንዲሁም የኦክስጅን እና የደም እጥረት በማጋጠሙ መዳን የሚችሉት ሰዎች እየሞቱ ነው ብለዋል፡፡

“ደም እና ኦክስጅን ለጤና ተቋማት እንዲቀርብ ካለተደረገ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል።” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

እሁድ ዕለት በአካባቢው በተለይም በቡሬ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ተራራ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ ሲደረግ እንደነበርም ተመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here