ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ጉንደ መስቀል ከተማ በአሸባሪነት በተፈረጀው በኦነግ ሸኔ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተገልጿል።
የከተማዋ ነዋሪች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ ከቅዳሜ ነሐሴ 20/2015 ጀምሮ በኹለቱ ታጣቂ ኃይሎች መካከል በከፍተኛ የጦር መሳሪያ የታገዘ የተኩስ ለውውጥ እየተደረገ ነው።
ይህም በወረዳው ዋና መቀመጫ ጉንደ መስቀል ከተማ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት መደቀኑ ነው የተገለጸው፡፡
እንዲሁም አደሬ ገመቹ፣ ባቡ ድሬ እና ሰለልኩላ በተባሉ ሥፍራዎች በኩል ግንቢ እንዳቆ እና ባላ ወደተባሉ ቦታዎች ከገቡ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በርካታ የቡድኑ አባላት መገደላቸውን የዓይን እማኞች አስረድተዋል፡፡
በትናንትናው ዕለት በጉንደ መስቀል ከተማ በርካታ የፋኖ ታጣቂዎች መኖራቸው የተነገረ ሲሆን፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ቦታው እያቀና መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም ቀደም ሲል የኦነግ ሸኔ አባል ናችሁ በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉ እና የተሀድሶ ስልጠና የወሰዱ ከ180 በላይ ግለሰቦች በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ታጅበው ቅዳሜ ዕለት ከፊቼ ወደ ደራ መግባታቸው ተመላክቷል።
በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ የሚገኘው ደራ ወረዳ ተደጋጋሚ በሚነሱ የወሰን ጥያቄዎች በርካታ ውዝግብ እና ግጭቶች ሲደረጉ ቆይቷል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ከደራ ወረዳ አስተዳደር እንዲሁም የሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በሌላ በኩል ከትናንት ረፋድ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንዲዳ ከተማ እና ከአማራ ክልል ጋር አዋሳኝ በሆኑ ቦታዎች በኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መኖሩን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች።



