ዳሰሳ ዘ ማለዳ ኅዳር 11/2012

0
748

1-የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር የመንገዶች ባለስልጣን ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት ቶላ ገዳ ትናንት ኅዳር 10/2012 ከጠዋቱ አምስት ለሥራ ጉዳይ ወደ ምዕራብ ወለጋ ቄለም ወለጋ ዞን እየሄዱ ባሉበት ወቅት ላሎ አሳቢ ወረዳ ውስጥ ጋራ ቶሬ ተብሎ በሚታወቀው ቦታ እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት ኤሊያስ ኡመታ ገልጸዋል ።(ቢቢሲ)
……………………………………………………………………..
2-በአዲስ አበባ ካርል አደባባይ አካባቢ በደረሰ የትራፊክ አደጋ በ13 ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደረሰ።አደጋው የደረሰው ዛሬ ረፋድ 5 ሰዓት ገደማ ከፒያሳ አትክልት ተራ 13 ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ሚኒባስ በልደታ አዲሱ አስፓልት ወደ ካርል አደባባይ መሄጃ ፍርድቤቱን ወረድ እንዳለ ፍሬን በጥሶ ከቆመ አይሱዙ ጋር በመጋጨቱ ነው።በአደጋውም ሹፌሩን ጨምሮ ሁሉም ተሳፋሪዎች ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተወስደዋል።(ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8)
……………………………………………………………………..
3-በዳርፉር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት ጥምር ተልእኮ ስር ለተሰማራው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይል በሰላም ማስከበር ላበረከተው የግዳጅ አፈጻጸም የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶለታል።በሱዳን የኢፌዴሪ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ሽልማቱን ባበረከቱበት ስነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ሰራዊት በሱዳንና በሌሎችም አገራት በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሕዝባዊ ተቀባይነት ያለውና በተባበሩት መንግስታት ድርጅትም አድናቆትን ያተረፈ ነው ብለዋል።(ኢቢሲ)
……………………………………………………………………..
4-የጀርመኑ ቮይዝ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኩባንያ ለኢትዮ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአማካሪነት ለመስራት ስምምነት ፈርሟል።ስምምነቱ በትናንትና ኅዳር 10/2012 በጀርመን በርሊን በተካሄደው የቡድን 20 አገራት ኢንቨስትመንት ጉባኤ ጎን ለጎን የተፈረመ ሲሆንስምምነቱን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) እና የቮይዝ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ ማርክ ክለሴን ተፈራርመውታል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)
……………………………………………………………………..
5- የኬንያ ፓርላማ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በትብብር መስራት እንደሚፈልግ ገለፀ።በኬንያ ፓርላማ የመንግስት ተጠሪ የተከበሩ አደን ዱዋሌ በኬንያ የኢፌዲሪ አምባሳደር መለስ ዓለምን በፓርላማ ጽሕፈት ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት የኢትዮ-ኬንያ የፓርላማዎች ወዳጅነት ማህበር እንዲመሰረት ጥሪ አቅርበዋል።
……………………………………………………………………..
6-አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለቀጣዩ ምርጫ የምርጫ ማኔፊስቶ ከማዘጋጀት ጀምሮ የክልል እና የፌደራል ፓርላማ ተመራጭ እጩዎችን በመመልመል ላይ መሆኑን አስታወቀ።የአገሪቷ የሰላም ሁኔታ በእንቅስቃሴያችን ላይ ተጽዕኖ ቢፈጥርብንም ለምርጫው ግን እየተዘጋጀን ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ገልጸዋል።(ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8)
……………………………………………………………………..
7-በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደቻለ የፌዴራል የመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አስራት አሳሌ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለመንገድ ጥገና እና የመንገድ ደህንነት እርምጃ የሚውል 820,722,500 ብር ለማሰባሰብ አቅዶ 665,375,459.61 ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።በሩብ ዓመቱ ለመጠገን ከተያዘው እቅድ 94 በመቶ ማሳካት መቻሉን ሃላፊው ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
……………………………………………………………………..
8-የዘይት ምርት አቅርቦትንና ስርጭትን የሚያሻሽል ማስፈጸሚያ አዲስ መመሪያ ማዘጋጀቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።የሕብረተሰቡን የመሠረታዊ ሸቀጥ ፍላጎት ለማሟላት ሚኒስቴሩ የተለያዩ አሰራሮችን በመተግበር ላይ መሆኑን አስታውቋል።የሕረተሰቡን የመሠረታዊ ፍጆታ እቃ የሆነውን የዘይት ምርት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማሟላት አዲስ መመሪያ አውጥቶ ወደ ክልልና ከተማ አስተዳደር በማውረድ ላይ መሆኑን ገልጿል።(ኢቢሲ)
……………………………………………………………………..
9-የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሴኔጋል በተካሄደው የአፍሪካ ሲቪል አቬሽን ኮሚሽን (AFCAC) 50ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ላይ ተሸለመ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካውያንን እርስ በርስ ብሎም ከመላው ዓለም ጋር በማገናኘት ከምስረታው ጀምሮ ላበረከተው ግንባር ቀደም አስተዋፆ ሽልማት ተበርክቶለታል።(አዲስ ማለዳ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here