ከሱዳን ተፈናቅለው የመጡ ኢትዮጵያውያን ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ተገለጸ

0
153

ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በደባርቅ ከተማ እና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በፌደራልም ሆነ በክልሉ መንግሥት በኩል ምንም ዓይነት የመጠለያና የምግብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ፤ ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል ሲል የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ፤ “በሱዳን ጦርነት ተፈናቅለው ለመጡ የስደት ተመላሾች ድጋፍ የሚያደረገው የፌደራል መንግሥቱ በመሆኑ በአማራ ክልል በኩል የምግብ እና መጠለያ ድጋፍ እየተደረገላቸው አይደለም፡፡ ይህም ለከፋ ችግር ዳርጓቸዋል።” ብለዋል፡፡

አክለውም፤ “በእኛ በኩል ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ወደ ደባርቅ የሚሄዱበት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲመቻች ከማድረግ ውጭ ሌላ ድጋፍ እያደረግን አይደለም፡፡ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ብናመለክትም አጥጋቢ ምላሽ አልተገኘም።” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሰላምይሁን ሙላት በበኩላቸው፤ “አራት ሺሕ የሚደርሱ የሱዳን ስደት ተመላሾች በደባርቅ ከተማ በከፋ ችግር ላይ ወድቀው ይገኛሉ” ካሉ በኋላ፤ ወቅቱ ክረምት በመሆኑና መጠለያ ባለመኖሩ በከተማው ባሉ ቤቶች ጥግ እና አስፓልት ዳር ወድቀው እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የምግብ እርዳታ የሚያደርግላቸው ባለመኖሩም ሕጻናትና ሽማግሌዎች በረሃብ ምክንያት ለሕመም እየተጋለጡ ነው ያሉት ኃላፊው፤ “አብዛኞቹ በሞት አፋፍ ላይ ናቸው።” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን ከሱዳን ስደት ተመላሾች በተጨማሪ ከትግራይ እና ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በደባርቅ ከተማ እና አካባቢው የሚገኙ 145 ሺሕ 981 ተፈናቃዎች እንደነበሩ ገልጸው፤ ከእነዚህ ውስጥ 104 ሺሕ ያክሉን ወደ ትግራይና ኦሮሚያ ክልል የተላኩ ቢሆኑም ቀሪዎቹ 41 ሺሕ ተፈናቃዮች በደባርቅ ከተማ እና አካባቢው እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

“በመሆኑም በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በሚነሳው ግጭት ተፈናቅለው ወደ ሰሜን ጎንደር ለገቡ 41 ሺሕ ተፈናቃዮች የሚፈልጉትን ድጋፍ እያደረግን ቢሆንም፤ ለሱዳን ሰደት ተመላሾችን እርዳታ ለማቅረብ ግን አቅማችን የማይፈቅድ በመሆኑ ድጋፍ እየተደረገላቸው አይደለም።” ሲሉ ተደምጠዋል።

“የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደርን ጨምሮ ለፌደራል መንግሥቱ በተደጋጋሚ ብናመለክትም መፍትሔ ሊገኝ አልተቻለም።” ያሉት ኃላፊው፤ “በመንግሥት በኩል ድጋፍ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ ቀይ መስቀልም ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ብንጠይቅም ከአቅሜ በላይ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቶናል።” ሲሉ አክለዋል፡፡

በሱዳን ጦርነት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በደባርቅ የሚገኙ የስደት ተመላሾች በበኩላቸው፤ “ከሱዳን ተፈናቅለን ወደ ደባርቅ ከተማ ከመጣን አራት ወር ቢሆነንም እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ እየተደረገልን ባለመሆኑ በአራት ወራት ውስጥ ከአስራ አንድ በላይ የሕጻናት እና አረጋዊያን ሕይወት ጠፍቷል።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የስደት ተመላሾቹ አክለውም፤ ከሱዳን ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሱዳናዊያን በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ መጠለያ ጣቢያ ተሰጥቷቸው በረጅ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ “ኢትዮጵያውያን የስደት ተመላሾች ግን ሜዳ ላይ እንድንወድቅ ተፈርዶብናል።” ሲሉ ነው የገለጹት።

“ችግራችንን ለሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር፣ ለአማራ ክልል መንግሥት እንዲሁም ለፌደራል መንግሥት በተደጋጋሚ ብናመለክትም ጠብ ያለ ነገር የለም።” ሲሉም ጠቁመዋል።

አራተኛ ወሩን ባስቆጠረው የሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውና ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡት ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸው ይነገራል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here