አርብ ነሐሴ 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭት በአስደንጋጭ ሁኔታ በ10 ነጥብ 5 በመቶ ጨምሯል ሲል የክልሉ ጤና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ርእየ ኢሳያስ በሰሜኑ ጦርነት ወቅትም ሆነ ከጦርነቱ በኋላ ልቅ በሆኑ ወሲባዊ ጥቃቶች ምክንያት የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በክልል በሚገኙ 37 የጤና ተቋማት በተደረገ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ፤ እስከ ጦርነቱ ጅማሮ 1 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው የቫይረሱ ስርጭት አሁን ላይ 10 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል፡፡
በክልሉ ከ120 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት መድረሱን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው፣ ከእነዚህ መካከል አምስት በመቶ በሚሆኑት ላይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደተገኘ ገልጸዋል።
“በተለይም ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች በሆኑ ወጣቶች ላይ ቫይረሱ በከፍተኛ መጠን መገኘቱ ጉዳዩን እጅግ አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ያደርገዋል፡፡” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
አክለውም፤ በየዕለቱ ከ20 እስከ 25 የሚሆኑ ሰዎች የኤች አይ ቪ ቫይረስ ምርመራ እንደሚያደርጉ እና ከእነዚህም ውስጥ ቢያንስ በኹለት ሰዎች ላይ ቫይረሱ እንደሚገኝባቸው ተናግረዋል።
“በአሁኑ ወቅት ሰዎች በሚፈለገው ልክ ወደ ጤና ተቋማት መጥተው ምርመራ እያደረጉ አይደለም፡፡” ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ ይህም ለቫይረሱ ስርጭት ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
“ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረ ምርመራ የሚያሳየው በወራት ውስጥ ውስን ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙ ሲሆን፤ አሁን ግን በቁጥር በርከት ያሉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የሚያሳይ መረጃ ከጤና ተቋማት እየደረሰን ነው፡፡ ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ እንደ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ሾፌሮች፣ ወላጅ አልባ ሕጻናት እንዲሁም በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን የመመርመር ሥራ እደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
“በክልሉ ሰዎች ምርመራ ሳያደርጉ እየተጋቡ ነው፡፡” ያሉት ርእየ፤ ይህም የቫይረሱ ስርጭት እንዲስፋፋ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ከፍተኛ የሆነ የኮንዶም እጥረት መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም ከኤች አይ ቪ ኤድስ በተጨማሪ ጠፍተው የነበሩ እና በግብረሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች በአንዳንድ ሰዎች ላይ መታየታቸው ነገሩን እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የመጠጥ፣ የጫት እንዲሁም የሌሊት ጭፈራ ቤቶች ከጦርነቱ በፊት ከነበረው በእጥፍ መጨመራቸውን ጤና ቢሮው አመላክቷል።
ቢሮው አክሎም ለኤች አይ ቪ ቫይረስ መመርመሪያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች እጥረት በየጤና ተቋማቱ መኖሩን በመጥቀስ፤ የሚመለከታቸው የፌደራል እና ሌሎች አካላት ለጉዳዩ አጽንዖት በመስጠት የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ አሳስቧል።



