የራክሲዮ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል ከኹለት ወራት በኋላ በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገለጸ

0
201

ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የራክሲዮ ኢትዮጵያ የደረጃ ሦስት አገልግሎት ሰጪ ገለልተኛ መረጃ ማዕከል በሚቀጥሉት ኹለት ወራት ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ዛሬ መስከረም 29/2016 በሸራተን አዲስ ሆቴል በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ራክሲዮ ኢትዮጵያ በአገራችን የመጀመሪያው “ሃይፐር ስኬል” የተሰኘ የደረጃ ሦስት ተሸካሚ ገለልተኛ ዳታ ማዕከል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የራክሲዮ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ በእውቀት ታፈረ፤ “ራክሲዮ ኢትዮጵያ የተሰኘ ዘመናዊ የዳታ ማዕከል በኢትዮጵያ ለመገንባት እና የዲጂታል መሰረተ ልማት ለውጥን ለማምጣት እንዲሁም በዳታ ሴንተር አማካኝነት የፋይናንስ ተቋማት የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት አልሞ እየተንቀሳቀሰ ያለ ማዕከል ነው፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ እና አስተማማኝ የመረጃ ማከማቻ አገልግሎት ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ የፋይናንስ ሴክተሮች ከፍተኛ ተደራሽነት ባለው የመረጃ ቋቶች ላይ እየተመሰረቱ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን ፍላጎት ለመፍታት ደህንነቱ የተጠበቀ ስነ ምህዳር በማቅረብ ኢ-ኮሜርስን እና ዲጂታል ክፍያዎችን ለማገዝ በመረጃ የተደገፈ የዳታ ሴንተር አገልግሎቶችን የሚሰጥ ማዕከል መሆኑ ተመላክቷል፡፡የራክሲዮ ኢትዮጵያ የመረጃ ማዕከሉ ለንግድ ሥራ ተደራሽነት እና እድገትን ለማረጋገጥ ያለውን ጠቀሜታ አመልክተዋል። “ራክሲዮ ኢትዮጵያ ለፋይናንሺያል አገልግሎት ዘርፍ የዕድገት መሰረትን በመገንባት ጉልህ ሚና ያለው ማዕከል ነው፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡

በመጪዎቹ ኹለት ወራት ውስጥ ሥራ ይጀምራል ተብሎ የታቀደው የራክሲዮ ኢትዮጵያ፤ የፋይናንስ ተቋማት የዳታ ሴንተር አገልግሎቶችን ወደ ራክሲዮ ኢትዮጵያ በማሰራጨት የተሻሻለ የደንበኛ አገልግሎት እንዲሰጥና የካፒታል ወጪን ወደ ዋና የሥራ ክንውኖች ውጤታማ በሆነ መንገድ ማዞር እንደሚያስችልም ተጠቁሟል፡፡

ማዕከሉ በኢንዱስትሪ መር ቴክኖሎጂ የታጠቀ ዘመናዊ፣ ሊሰፋ የሚችል ግብዓት፣ ጥብቅ የደህንነት እርምጃዎች እና ደንበኞችን ከአገር ውስጥ እና ከአለም አቀፍ አገልግሎት አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝ የመገናኛ ክፍሎችን ያማከለ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እየተፋጠነ ባለበት በአሁኑ ወቅት ትራንስፎርሜሽን የሚደግፉ መረጃዎች የሚከማቹበት እና የሚቀነባበሩበትን ሰፊ እና እያደገ ያለውን የፋሲሊቲ ፍላጎት ለመቅረፍ የመረጃ ማዕከሉ በአዲስ አበባ እየተገነባ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here