በኢትዮጵያ በኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት 327 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ በኮሌራ ወረርሽኝ ከአስሩም ክልሎች 327 ሰዎች መሞታቸውን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም ዓቀፍ የሕጻናት ነፍስ አድን ፈንድ (ዩኒሴፍ) አስታውቋል።

ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ ኹኔታ አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት፤ በኢትዮጽያ 327 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት መሞታቸውን ያስታወቀ ሲሆን፤ እስከ መስከረም 19/2016 ድረስ የተረጋገጡ 24 ሺሕ 929 የኮሌራ ተጠቂዎች መመዝገባቸውንም ገልጿል።

የተከሰተው ወረርሽኝ በነሀሴ 2022 በኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ ደቡብ ክልል እና ሌሎች አካባቢዎች መዛመቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ከመጋቢት 2023 ጀምሮ አሳሳቢነቱ እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል።

በቂ ያልሆነ የመጸዳጃ ቤት፣ የተበከለ ዉሃ እና ደካማ የሆነ የንጽህና አጠባበቅ ለኮሌራ ወረርሽኝ እንዲስፋፋ ዋነኛ ምክንያት መሆኑም ተመላክቷል።

እንደ ተመራማሪዎች ገለጻ በየዓመቱ ከ 1 ነጥብ 3 እስከ 4 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በኮሌራ የሚጠቁ ሲሆን፤ በዓለም ዙሪያ ከ21 ሺሕ እስከ 143 ሺሕ  ያህል ሰዎች በኮሌራ ምክንያት ይሞታሉ።

በተመሳሳይ ዜና በኢትዮጵያ በአራት ክልሎች ከ102 ሺሕ 700 በላይ አዳዲስ የወባ ታማሚዎች መመዝገባቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አስታውቋል።

ቢሮው ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል 774 ሺሕ ሰዎች በወባ መያዛቸውን እንዲሁም፤ 180 ያህል ሰዎች በበሽታው መመሞታቸውን ነው ቢሮው የገለጸው።

በሽታው ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመዘገበው በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም ምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ሲሆን፤ ነዋሪዎቹ ለከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ እና የመድሃኒት እጥረት መጋለጣቸውም ተነግሯል።

ለትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ትንንሽ የውሃ ኩሬዎችን ለወባ ስርጭት መጨመር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን፤ እንዲሁም የአልጋ አጎበር በአግባቡ የመጠቀም ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ለበሽታው መዛመት እንደምክንያት ተጠቁሟል።

በተጨማሪም የወባ በሽታ ባለባቸውን አካባቢዎች የሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች፤ በሽታው ቀድሞ ከነበረው ኹኔታ ይበልጥ እንዲባባስ ምክንያት መሆናቸው ተመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here