በኢትዮጵያ በዓመት 3 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች በዉሻ እብደት በሽታ እንደሚሞቱ ተገለጸ

ሐሙስ ጥቅምት 8 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ በዓመት ሦስት ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች በዉሻ እብደት በሽታ እንደሚሞቱ የግብርና ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሕክምና ከኅብረተሰብ ጤና ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ ጌታቸው፤ “የዉሻ እብደት በሽታ የገዳይነቱና አስፈሪነቱን ያህል ተገቢው ትኩረት አለተሰጠውም፡፡” ሲሉ ገልጸዋል።

በሽታው በብዛት ወደ ገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል በስፋት እንደሚስተዋል የገለጹት ሃላፊው፤ በተለይም ሴቶችና ሕጻናት ይበልጥ ተጋላጮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም በዚሁ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን አመላክተዋል።

“የዉሻ እብደት በሽታ ሕክምና አለው ለማለት ይከብዳል” ያሉት ዶ/ር ሲሳይ፤ ለበሽታው ለኹለት የተከፈለ የሕክምና አይነት መኖሩን ገልጸዋል።

“የመጀመሪያው ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን ከገባ በኋላ ስርጭት የማቆምና የመከላከልና የማዳን ሲሆን፤ ኹለተኛው ደግሞ በበሽታው ሊጠቁ ይችላሉ ተብሎ የሚታሰቡትን የማህበረሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ክትባት እንዲወሰዱ ማድረግ ነው።” ሲሉ አብራርተዋል።

ዶ/ር ሲሳይ፤ በኢትዮጵያ በሽታው በብዛት ከሚከሰትባቸው እና ከበሽታው ጋር የሚኖሩ ሰዎች ካሉባቸው አገራት ዉስጥ እንደምትመደብ ገለጹ ሲሆን፤ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ትኩረት ያላገኙ (neglected disease) የሆኑትን በሽታዎች በ2030 ከአለም ላይ ለማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አመላክተዋል።

ዕቅዱን ኹሉም አገራት ወደ ራሳቸው ይዘት መመለሳቸውንም በማንሳት፤ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና ጥበቃ ዘርፍ፣ የግብርና ሚኒስቴር ከሌሎች ተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን <<የአንድ ጤና መርህ>>ን የተከተለ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት ኅብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች እንዲሁም የንቅንቄ ሥራዎች መጀመራቸውን በመግለጽ፤ ዉሾችን መከተብ ዋነኛው በሽታውን መከላከያ መንገድ በመሆኑ ሰፊ የአገር አቀፍ የሆነ የክትባ ዘመቻ ባለፉት ኹለት ዓመታት ሲካሄድ መቆየቱን አብራርተዋል።

የዉሻ እብደት በሽታ በማደግ ላይ ባሉ እንደ አፍሪካና ኤዥያ እንዲሁም ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላይ የሚገኙ አገራት ላይ በስፋት ይስተዋላል።

የአለም ዓቀፍ የዉሻ እብደት በሽታ ቀን “አንድ ጤና ለኹሉም፥ ኹሉም ለአንድ ጤና” (All for 1, One Health for all) በሚል መሪ ቃል በዓለም ለ17ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ12ኛ ጊዜ መስከረም 21/2016 ተከብሯል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here