አስር አገራት የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ጥሪ አቀረቡ

አርብ ጥቅምት 23 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ከሰሜኑ ጦርነት በኃላ የተደረሰው የፕሪቶሪያ ስምምነት አንደኛ ዓመት አስመልክቶ የፕሮቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር አስር አገራት ጥሪ አቅርበዋል።

ጥሪውን ያቀረቡት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ አስር አገራት ማለትም አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድ፣ ኒውዝላንድ፣ ኖርዌ፣ ሲውዲን እና ዩናይትድ ኪንግደም ሲሆኑ፤ አገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ የፕሪቶሪያው ስምምነት ያስገኘው ዉጤት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ስምምነቱ ክልሉን ወደ ነበረበት ለመመለስና የመሳርያ ድምጽ እንዳይሰማ መሰረት የጣለ መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን፤ በቀጣይ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንዲሁም ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለማጎልበት እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

አገራቱ በመግለጫቸው የዜጎችን ሰላም ለመጠበቅ እና ለማስቀጠል ብዙ ሥራ መሰራት አለበት እንዳለበት በመግለጽ፤ ትጥቅ ማስፈታት፣ መልሶ ማቋቋም እንዲሁም አገራዊ ምክክሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

እንዲሁም የኤርትራና መንግሥታዊ ያልሆኑ ሀይሎች የትግራይ ክልልን ለቀው እንዲወጡ፣ ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶችን እንዲጀመሩ፣ ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደረግ እንዲሁም የሽግግር ፍትህ ትግበራና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ከግጭት እንድትወጣ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ አፍሪካ ኅብረት እና ከሲቪል ማህበረሰብ አጋሮች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

በተመሳስይም “በአሁኑ ሰዓት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚስተዋለው ግጭት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ነው” ያሉት አገራቱ፤ ግጭት እንዲቆምና ኹሉን አቀፍ ዉይይት ሊካሄድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፕሮቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ትናንት ጥቅምት 22/2016 አንደኛ ዓመቱን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በስምምነቱ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ለሕዝባችን ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቁርጠኛ መሆናችንን እናረጋግጣለን” በማለት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

እንዲሁም የትግራይ ክልል ሕዝብ ችግር ላይ መሆኑን የተናገሩት የሕህወሃት ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው፤ “የሕዝባችን ስቃይ እስካሁን ቀጥሏል፤ ዛሬ ለስምምነቱ ቁርጠኝነታችንን የምናረጋግጠው የሕዝባችን ስቃይ ያበቃል በሚል ተስፋ ነው” ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ሆኖም ግን በስምምነቱ የተካተቱ ነገሮች በሙሉ ተግባራዊ መሆን እንዳልቻሉና የጦር ወንጀሎችን ጨምሮ በርካታ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙ በተለያየ ጊዜ የሚወጡ ሪፖርቶች ያመላክታሉ።

በሰላም ስምምነቱ መሠረት ለትግራይ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ እንዲሁም ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ ሕይወታቸው የመመለሱ ሥራ የተዘነጋ ይመስላል ሲሉም በርካቶች ይደመጣሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here