አማራ ክልል ውስጥ በታጣቂዎች መንገድ ላይ “እየተዘረፍን” እና እየተንገላታን ነው ሲሉ ተማሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ

0
1802

በአማራ ክልል ከተለያዩ ስፍራዎች ወደ መቅደላ አምባ ዩንቨርስቲ የሚገቡ ተማሪች በመንገድ ላይ በታጣቂዎች የሚደረግ ፍተሻ መኖሩንና ተማሪዎች እንዲሁም መምህራን እንዳያልፉ እየተከለከሉ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ለአዲስ ማለዳ ሃሳባቸውን የሰጡ ተማሪዎች እንደገለጹት ታጣቂዎቹ “ተማሪዎች እና መምህራን እንዲያልፉ አይፈልጉም”። 

ከጎንደር መነሻውን ያደረገ ሌላ የመቅደላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪም ደብረ ታቦር ሲደርሱ ከፊት ለፊታቸው በመኪና መንገድ እንደተዘጋባቸው ይገልጻል። “ከተሳፋሪዎቹ መካከል የሱዳን ስደተኞች ሲቀሩ ሌላውን ተሳፋሪ ስልክ፣ ገንዘብ እና ሌሎች ነገሮችንም” እንደወሰዱ ገልጾ ከዛ በኋላ ግን ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን መጓዛቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። 

ተማሪዎች በተለይም ከመካነ ሰላም እና መርጡ ለማርያም አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡ ጥቂት ሲሆኑ፤ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ከመንገድ እንዲመለሱ መደረጋቸውን አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች።

 

 

 

 

 

ዲስ ማለዳ “ታጣቂዎቹ እነማን ናቸው? ምን ዓይነት ናቸው?” በሚል ለተማሪዎች ላቀረበችው ጥያቄ “ማንነታቸውን በእርግጠኝነት መናገር ይከብዳል፤ ነገር ግን ሬንጀር ዩኒፎርም የለበሱም፤ ሲቪሎች እንዲሁም ልብስ ያልበሱ ጭምር አሉ” መኖራቸውን ተማሪዎቹ ያነሳሉ።

በተጨማሪም ታጣቂዎቹ “ተማሪዎች ወደ ተቋማት እንዳይገቡ ብለን ነበር፤ አንድ ዩኒቨርሲቲዎቹ ላይ ችግር ቢፈጠር የምትጎዱት እናንተ ናቹ፤ ለዚህ ነው የምንመልሳቹ” ሲሉ ለተማሪዎች መናግራቸውን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ሲመጡ ለደህንነታቸው ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው እራሳቸው ተማሪዎቹ እንደሆኑ በይፋ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት ጥር 15 ቀን 2016 ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዘንዘልማ ካምፓስ ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በካምፓሱ ያለው ሁኔታ አስጊ በመሆኑም ተማሪዎችን በጊዜያዊ ምደባ ወደ ፖሊ ካምፓስ እንዲዘዋወሩ የተደረገ ሲሆን ተማሪዎች ጊቢውን ለቀው እንዲወጡ የሚያዝ ወረቀት መለጠፉን አዲስ ማለዳ ከተማሪዎች ብትሰማም ወረቀቱን ዩኒቨርሲቲው አልያም ሌላ አካል ይለጥፈው ማወቅ አልተቻለም።

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን ለመቀበል ሶስት ቀናት ሲቀረው የአዲስ እና የሬሜዲያል ተማሪዎችን መግቢያ ቀን ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙን ሲገልጽ ለምን እንድተራዘመ የሰጠው ማብራሪያ የለም። በተያያዘ ከቀናት በፊት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በማንኛውም ጊዜ የፀጥታ ችግር ቢከሰት ሃላፊነቱን አልወስድም ማለቱም አይዘነጋም። 

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተማሪዎች ከመርጡ ለማርያም ተነስተው ወደ መካነ ሰላም ለመጓዝ ዓባይ ወንዝ ላይ ከባድ ፍተሻ በታጣቂዎች እንደሚከናወን ገልጸው ከመርጡ ለማሪያም ወደ መቅደላ ለመሄድ ሾፌሮችም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል። 

“የተማሪነት መታወቂያ እና የትምህርት ማስረጃ የያዘ ሰው ማለፍ ቀርቶ፣ የሚወርድበት የዱላ መዓት አይጣል ነው” የሚለው የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለመጀመሪያ ዓመት ምዝገባ የሚያስፈልገውን የትምህርት ማስረጃ ይዞ በመጓዝ ላይ ነበር። መንገድ ላይ መኪናውን ያስቆሙት ታጣቂዎች ግን ቦርሳውን በመፈተሽ ማስረጃዎቹ በሙሉ ከፊቱ ለፊቱ ቀደው እንደጣሉበት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ዩኒቨርሲቲ ከደረሰ በኋላ የትምህርት ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ መታወቂያ እና ምዝገባ ማካሄድ አትችልም ተብሎ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መቆየት አትችልም ተብሏል። ይሄው ወጣት፤ ባለው አስቸጋሪ የኢንተርኔት መቆራረጥ ማስረጃውን ከቤተሰብ እንዲላክለት ማድረጉን ጨምሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ታጣቂዎቹ ሾፌሮችን ገንዘብ እንደሚቀበሏቸው የተገለጸ ሲሆን የተወሰኑ መምህራን የሥራ መታወቂያቸውን ደብቀው በነዋሪነት መታወቂያ ማለፍ ችለዋል ተብሏል። ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያቀኑ ተማሪዎች በታጣቂዎች የመታገት፣ የዘረፋ እና ወደመጡበት እንዲመለሱ እየተደረጉ መሆኑን ተማሪዎች ያነሳሉ።

በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በ2016 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያዉ ወሰነ ትምህርት ተማሪዎቻቸውን ለመጥራትና መደበኛ የመማር ማስተማር ስራቸዉን ሙሉ ለሙሉ ለመጀመር አለመቻላቸው አይዘነጋም።

ሆኖም የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአስሩ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ ጸጥታ አካላት ታህሳስ 18 ቀን 2016 አደረጉ በተባለው ምክክር ተቋማቱ ተማሪዎችን እንዲቀበሉ መወሰኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝንን ለማነጋገር ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

በውሳኔያቸው ግን “በክልሉ አንጻራዊ ሰላም የተፈጠረ በመሆኑ ዩኒቨርስቲዎቹ ተማሪዎችን መጥራትና ማስተማር ይችላሉ” የተባለ ሲሆን ከጥር 1 ቀን 2016 ጀምሮ ባሉ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ዩኒቨርስቲዎቹ ተማሪዎችን ጠርተው የመማር ማስተማር ስራቸውን እንደሚጀምሩ ተገልጾ ነበር።

ይሁን እንጂ በክልሉ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራዎች ለመስራት አስቸጋሪ ስለመሆኑ ለአዲስ ማለዳ የደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ። የሚኒስቴሩን ውሳኔ የአማራ ክልል ተማሪዎች ማህበር በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር ባለበት እንደቀጠለ መሆኑ እየታወቀ የትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ይጀምሩ ማለቱ ትክክል አይደለም በማለት ተቃውሞ ነበር። 

ከምንም ነገር በላይ የተማሪዎቹን ደህንነት መጠበቅ የሚቀድም በመሆኑ ማህበሩ እንደ ተቋም ከሚኒስቴሩና ከትምህርት ተቋማት ጋር በመነጋገር ውሳኔውን ለማስቀልበስ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም አስታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here