“ወደኢትዮጵያ እንዳይገባ” የተከለከለው ግለሰብ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ሆኖ ሊሾም ነው- ቅሬታ አቅራቢዎች

0
1328

በእስራኤል ነዋሪ የሆኑ “ስለ ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት “የአገሪቱን ስም በማጉደፍ በከባድ ወንጀል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዳይገባ የታገደው የእስራኤል ዜጋና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነዉ አብርሃም ንጉሴ በኢትዮጵያ የአስራኤል መንግስት አምባሳደር እንዲሆን ሾሞታል” ብለዋል።

 

በጥቂት ጊዜ ውስጥ “ይፋ” እንደሚደረግ ይጠበቃል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች አብረሃም ንጉሴ የተባለው ግለሰብ ከአንድ ሌላ እስራኤላዊ ዜጋ ጋር በመሆን “በኢትዮጵያ ግዛት ጎጆ አቃጥለው በፊልም ከቀረጹ” በኋላ የተቀረጸውን ተንቀሳቃሽ ምስል በአሜሪካ እና በእስራኤል ለሚገኙ ‘ይሁዲዎች’ በማሳየት “በኢትዮጵያ የይሁዲ ዘር ጥላቻ” እንዳለ በማስመሰል “ቅሰቀሳ በማድረግ ተጠቅመዉበታል” ሲሉ ወንጅለዋል።

አዲስ ማለዳ በአብረሃም ንጉሴ ላይ የቀረበውን ትችት በተመለከተ ለማጣራት በወቅቱ የተሰሩ ዘገባዎች እንዲሁም የነበሩ መረጃዎች እና ሰነዶች ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። በተጨማሪም አዲስ ማለዳ ውንጀላው የቀረበባቸውን ትውልደ ኢትዮጵያዊ የእስራኤል ዜጋ የሆኑትን አብረሃም ንጉሴ ለማግኘት ወደ ስልካቸው በምደወል እና የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ምላሻቸውን ለማካተት ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል።

ከእስራኤል ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ሰዎች እንደሚሉት በነ’አብረሃም ንጉሴ “የተቀረጸውን” ተንቀሳቃሽ ምስል የተመለከቱ የአይሁድ እምነት ተከታዮች “በተደረገዉ አስቃቂ ወንጀል በማዘን” በእስራኤል ለሚገኘው የኢትዮጵያ አምባሳደር አቤቱታቸውንና ህጋዊ እርምጃ መንግስት እንዲወስድ” እንዲሁም ውጤቱን እንዲያሳዉቃቸዉ ጠይቀው ነበር።

በቀረበዉ ክስ መሠረት ኤምባሲው የተቀበለውን ተንቀሳቃሽ ምስል ወይም ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት “ፊልም” እንዲሁም የክሱን ደብዳቤ በማያያዘ በወቅቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛዉ ምስራቅ ክፍል ኃላፊ ለነበሩት ነጋሽ ክብረት (አሁን ጡረታ ላይ የሚገኙ) ክሱን እንዲያጣሩና ዉሳኔያቸዉን እንዲሰጡበት መተላለፉን አዲስ ማለዳ ከቅሬታ አቅራቢዎች ሰምታለች።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛዉ ምስራቅ ክፍል ኃላፊ የነበሩት ነጋሽ ክብረት የክሱን ደብዳቤና “ፊልሙ”ን በማያያዝ በይሁዲዎች ላይ “አሰቃቂ የዘር ልዩነት ወንጀል ተፈጽሟል” ለተባለበት የአማራ ክልል አስተዳዳሪ ለነበሩት አዲሱ ለገሰ እንዲያውቁ መደረጉን እና ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ ወደቦታው ተልኮ ነበር ተብሏል።

ለአዲስ ማለዳ መረጃውን ያደረሱት “ተቆርቋሪዎች” ጉዳዩን በተመለከተ ኮሚቴ ተቋቁሞ “በኢትዮጵያውያን ከባድና አስቃቂ የየሆነ ወንጀል ተፈጽሟል” የተባልበትን ገጠር ጎብኝተው የአካባቢውን ህዝብ አሰባስበው እንደነበረ ይገልጻሉ። የተቀረጸውን ተንቀሳቃሽ ምስል እና የወንጀሉን ዝርዝር ሲሰሙ “ያዩትን ባለማመን እኛ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻቸን ይሁዲዎቸ ጋር አንድ ላይ አድገን አንድ ላይ በፍቅር በሰላም የኖርን እንጂ በመካከላችን ምንም አይነት ልዩነት ኑሮን አያዉቅም” ሲሉ በወቅቱ ምላሽ እንደሰጡ ይገልጻሉ። 

እንደቅሬታ አቅራቢዎቹ “እንዲህ ያለ አሰቃቂና የሰዉ ልጅ ፍጡር ሊፍጽመዉ የማይችል ግፍ ሰርታችኋል ተብለን በእስራኤልና አሜሪካ መንግስት እንከሰሳለን?”ብለው መጠየቃቸውን ገልጸዋል። 

ይህ ውይይት መደረጉን ተከትሎ ኮሚቴው የዉይይቱን ፕሮቶኮል ጭምር ይዞ ወደ አማራ ክልል የወቅቱ አስተዳዳሪ አዲሱ ለገሰ (የአማር ክልል ከ1984 እስከ 1993 ዓ.ም ያስተዳደሩ) ከተወሰደ በኋላ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራክ ክፍል ኃላፊ ነጋሽ ክብረት ጋር ደርሶ እንዲያዩት ተደርጓል ተብሏል። 

የአዲስ ማለዳ ተጨማሪ ማረጋገጫዎች ለማግኘት የተደረገው ጥረት አብረሃም ንጉሴ ስልክ ባለመመለሳቸው ባይሳካም፤ ከተወሰኑ ቀናት በፊት የእስራኤሉ ‘ዘ ታይም ኦፍ እስራኤል’ ግለሰቡ ለአምባሳደርነት መታጨቱን በተመለከተ ባወጣው ዘገባ ለቃለ መጠይቅ ፈልገውት ምላሽ እንዳልሰጣቸው ገልጸው “በአፍሪካ ውስጥ ካሉት የእስራኤል ቁልፍ አጋሮች በአንዱ ውስጥ ለማገልገል መሾሙ በአብረሃም ንጉሴ ብዙም ባልታወቁ የህይወት ታሪክ ዙሪያ ትኩረት እንዲስብ አድርጓል፤ ያለፈ ታሪኩን እሱ እምብዛም አይናገራቸውም” ሲል አስነብብቧል።

ጉዳዩን ከእስራኤል ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት አካላት እንደሚሉት የተፍጸመው ድርጊት የኢትዮጵያንና የእስራኤልን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካና ከሌላዉም ዓለም ጋር “ሊያራርቀን የሚችል ስለሆነ በቀላሉ መታየት የለበትም” ተብሎ “ለወንጀሉ” ለግል ጥቅሙ ሲል ላሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል “ወደ ኢትዮጵያ ዳግመኛ ተመልሶ እንዳይግባ ለአስፈላጊዎቹ ክፍሎችና ለኢትዮጵያ ኤምባሲ በእስራኤል ጥብቅ ትእዛዝ ተላለፏል” በማለት ገልጸዋል። 

የኢትዮጰያ መንግስት “ክብሩንና ህልውናውን መጠበቅና ማስከበር መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታው ጭምር ነው” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች “አብርሃም ንጉሴ በአምባሳደርነት በኢትዮጵያ አንዲያገለግል ከእስራኤል መንግስት የሚቀርበውን ጥያቄ መቀበል የለባትም። አገሪቱን ከናዚዎች ተግባር ጋር አወዳድሮ የሚወነጅል በኢትዮጵያ ምድር እንኳንስ በአምባሳደርነት በክብር ሊስተናገድ ቀርቶ በኤምባሲዎች አካባቢ መገኘት የሚገባው ሰው አይደለም” አይደለም በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል። 

አብረሃም ንጉሴ በእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ በተለይም ቤተ እስራኤላውያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ በማድረግ ስሙ ከፍ ያለ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ አመራር እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪም ሆኖ አገልግሏል።

አዲስ ማለዳ በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ እድገቶችን የምትዘግብ ሲሆን በጉዳዩ ላይ የሁሉንም አካላት ምላሽ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ትገልጻለች።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here