በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ) ለዘጠኝ ዓመታት ያገለገለው ወገን አበበ የተባለ ግልሰብ በኢቢሲ የተለያየ የሥራ ዘርፍ ላይ ያሉ “400 የሚሆኑ ሠራተኞች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ” እንዳላቸው አጋልጠሃል በሚል ከስራ መባረሩን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ከዓመታት በፊት ይኼው ውዝግብ እንደተጀመረ የሚገልጸው ወገን፤ በተለያየ ጊዜ የተቋሙ የሠው ሃብት አስተዳደር እንዲሁም ለቀድሞው የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሐ ይታገሱ በተቋሙ ውስጥ በርካታ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን ሲያሳውቅ እንደቆየም ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት “በተሻለ ተቋሙን ለመቀየር እና አገሪቱን የሚመጥን ብሔራዊ ሚዲያ ለማድረግ የሪፎርም ስራ እየሰራ ሲሆን፤ በሪፎርሙም በዋናነት የሠው ኃይል አቅም ማሳደግ፣ የሥራ ባህልን ማሻሻል እና በአገር ደረጃ የተጀመረውን የሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ ማጣራት” ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ መሆኑን በህዳር ወር መጨረሻ 2015 ላይ አስታውቆ ነበር።
ኢቢሲ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ለሆኑ 136 ሰዎችን የስም ዝርዝር በማስፈር “ዲግሪያችሁን የወሰዳችሁበትን ቅርንጫፍ እንድትሞሉ እናሳስባለን” የሚል ማስታወቂያ አውጥቶ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ማቅረብ የቻለ እንዳልነበረ ወገን አበበ ተናግሯል።
ቀጥሎም “ሪፎርሙን” ተከትሎ በተቋሙ ውስጥ የቀረበው የሐሰተኛ እና እውቅና ያልተሰጠው የትምህርት ማስረጃ ጉዳይ በተቋሙ አመራር ደረጃ ያሉ እና ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋዮችን የሚነካ በመሆኑ “ለመሸፋፈን ጥረት መደረግ መጀምሩንም” ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።
ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዕድል ሰጥቶ ከኢቢሲ 35 የሚሆኑ ሠራተኞች ተልከው እንደነበር የሚያስታውሰው ወገን አበበ፤ “ዩኒቨርሲቲው የተላኩት ሠራተኞች ያላቸው የትምህርት ደረጃ መስፈርቱን ያላሟላ በመሆኑ ውድቅ አድርጎ መልሶታል” ሲል ገልጾልናል።
በተመሳሳይም በድህረ ምረቃ በድጋሚ የትምህርት ዕድል ተገኝቶ የተላኩት ሠራተኞች “(withdraw) ሞልተን መጣን ቢሉም ዩኒቨርሲቲው በድጋሚ እንዳልተቀበላቸው ማሳያ ነው” ሲል ወገን ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
አዲስ ማለዳ ወገን አበበ ጉዳዩን ለማሳወቅ ለኢቢሲ ከጻፈው ደብዳቤ እንደተመለከተችው “ተቋማት በተቋም ደረጃ ትምህርት ማስረጃ ማጣራታቸው ዋነኛ ጥቅሙ በግለሰቦች ስህተት የተቋሙ ሥም ከመጥፋት ይታደጋል። ኢቢሲ ይሄን ያክል በመቶ ዲግሪ ሐሰተኛ ሆነ ከመባል ሰበር ዜና ያድናል። እንዲሁም ብቁ የሠው ኃይል እንዲኖረው ያደርጋል። የሠው ሀብት አሥተዳደር ቀድሞ ትምህርት ማስረጃን ጉዳት ሳያደርስ ውድቅ እንዲያረግ ያስችለዋል አቅሙን ያሳድጋል” በማለት ገልጿል።
በተጨማሪም “ዛሬ እኛ የምናውቃቸውን እርግጠኛ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ያረጋገጥነውን ሥም ዝርዝር አቅርበናል። ተቋሙ በዚህ መንገድ ተጠቅሞ እዲያጸዳ በርካቶች በመኖራቸው አጣርቶ እዲያወጣና ዲግሪውን ውድቅ እንዲያረግ” ሲል ወገን ከጥቂት ሠዎች ጋር አብሮ በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል።
እንደ መፍትሔ ሃሳብም “በምክትል ሥራ አስኪያጁ የሚመራ ሚስጥራዊ ኮሚቴ ይዋቀር። ምክትል ሥራ አስኪያጁ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) እንደመምጣቱ በደንብ ነው የሚያውቀው አሰራሩን። እኛም አለን ከተቻለ ከኦቢኤን [ኦቢኤን ከዓመታት በፊት በዚሁ ጉዳይ ላይ በርካታ ሰራተኞቹ ላይ እርምጃ ወስዷል] የሠው ኃብት አንድ ሰው ይምጣ” ብለዋል።

አክለውም “በጉዳዩ ላይ ልምድ ስላላቸው በ15 ቀን ውስጥ በተቋም ደረጃ የተቋማችን ሥም ሳይጠፋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጭበርባሪውን ጠርገን እናወጣለን። በተጭበረበረ መንገድ ለሚማሩትም ትምህርት እንዲሆን እንዲቀጡ እናደርጋለን” በማለትም እንደገለጹ አዲስ ማለዳ ከደብዳቤው ተመልክታለች።
ይኽ ጉዳይ ወደ ውጪ እንዳይወጣ በውስጥ በኩል ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም “የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችም ሆነ የሠው ኃብት አስተዳደሩ፤ ይኼን ጉዳይ ከመፍታት ይልቅ ጉዳዩን ለመሸፈን እኛ ላይ ጫና ማሳደር ጀመሩ” ሲልም ቅሬታውን ይገልጻል።
የትምህርት ማስረጃዎቹ በኢፌድሪ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ማጣራት መደረጉን ያነሳው ወገን፤ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች መሆናቸውን ባለስልጣኑ አረጋግጧል ብሏል። ከዚ በኋላም ጥቆማው ለፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በደብዳቤ የተላከ ሲሆን አዲስ ማለዳ ደብዳቤውን ተመልክታለች።
በዚህም በኢቢሲ ውስጥ ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ጀምሮ ላሉ አካላት ጉዳዩን እና ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸውን ሠራተኞች ሥም ዝርዝር ማስገባታቸውን ገልጸዋል። በጥቆማውም የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የትምህርት ማስረጃዎቹን ሐሰተኛ መሆን እንዳረጋገጠ ለኮሚሽኑ የተጻፈው ደብዳቤ ይገልጻል።
ሆኖም ግን “መካከለኛ አመራሮች እንደማይቀርላቸው ሲያወቁት ጉዳዩን ለማፈን እየጣሩ ነው። ምክትል ሥራ አስፈፀሚ እና የሠው ኃብት አስተዳደር እዲቀጡ ቢያዝም የሥነ ምግባር መኮንን ክፍሉ ምንም ሊያረግ አልቻለም። ክስም አልመሰረተም ብዙ ስለሆኑ የማናጅመንት ውሳኔ ይፈልጋል በማለት እያረሳሳ ይገኛል” ሲል ቅሬታ አቅራቢው ወገን ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።
በተጨማሪም “እኛ ከምንሰራበት ክፍል በጥናት አረጋግጠን ለአመራሩም ያሳወቅናቸውን ከ30 ሠው 23 ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ከተገኘ ሰራተኛው ከ2000 በላይ ነው፤ ስንት ፎርጅድ እንደሚኖር በየሥራ ክፍሉ ቢጣራ” የሚል ይገኝበታል። ከዚህ ጥቆማ በኋላ ሐሰተኛ ሰነድ የተገኘባቸው ሰዎች ጋር በማበር ዛቻና ማስፈራርት “መጀመራቸውን” ገልጿል።
ወገን ከአመራሮች እና ሌሎች ሠራተኞች የሚደርስበትን ዛቻ በመፍራት ለሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የህግ ከለላ ጥያቄ በማቅረቡ ኮሚሽኑ “ጥቆማ ያቀረቡት ግለሰብና ቤተሰቦቻቸው በኮሚሽኑ እምነት የህግ ከለላ እንደሚያስፈልጋቸው ያመነበት ስለሆነ በሙስና ምስክርና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ መሰረት፤ በእናንተ በኩል የህግ ከለላ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው” በማለት ለወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የተላከውን ደብዳቤም አዲስ ማለዳ ማየት ችላለች።
የዚህ ደብዳቤ ግልባጭ “እንዴት እንደሆነ ባልታወቀ መንገድ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ባንዴ ተሰራጨ” ብሎ የገለጸው ወገን፤ “በቀጥታ እኔ እንደሆንኩ ነው ያሰቡት፤ ሆኖም ግን በወቅቱ እኔ ደብዳቤውን ለማንም አልላኩም ነበር” ሲል ተናግሯል።

በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተሰራጨውን ደብዳቤ ተከትሎ የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ነሐሴ 27 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ “ከኮሚሽኑ የከለላ ደብዳቤ የተሰጠውን አላግባብ ትርጉም መስጠት፤ ገና ማስረጃ ባልተደራጀበትና በጥቆማ ያለውን ጉዳይ መነሻ በማድረግ የተቋሙን ስም ማጠልሸት ተጠያቂ ያደርጋል” በማለት የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ያረጋገጠውን ጉዳይ አስተባብሏል።
ኮሚሽኑ “በኢቢሲ ጫና ተደርጎበታል። ለዛም ነው ወደ ኢቢሲ ወገን በመሆን ያስተባበለው” ሲል በዚህ ጉዳይ ላይ ወገን ግምቱን አስቀምጧል። ኢቢሲ በበኩሉ “እስካሁን ግማሽ የሚሆነው ሠራተኛ የትምህርት ማስረጃ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ጋር በመሆን የተጣራ ሲሆን፤ በዚህም ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ሠራተኞች አልተገኙም” ሲል በተመሳሳይ አስተባብሏል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በወገን አበበ ላይ “ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት” ወንጀል ክስ የመሰረተበት ሲሆን፤ ወገን አበበ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ሠዎችን ሥም ዝርዝር በማቅረብ ተከራክሮ ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 7 ቀን 2016 በዋለ ችሎት ወገን አበበ በነጻ እንዲለቀቅ ወስኗል።
ፍርድ ቤቱ በነጻ ቢያሰናብተውም ወደ ሥራ ሲመለስ የሥራ ስንብት ደብዳቤ እንደተሰጠው ወገን ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል። “ለምንድን ብዬ ስጠይቃቸው ለሚዲያ ተናግረሃል” የሚል ምላሽ እንደሰጡት እና “ብናገርም ሃሰተኛ መረጃ አይደለም የሰጠሁት” ሲል ምላሽ እንዳላገኘ ገልጾልናል።
በተደጋጋሚ ጉዳዩን ለማስረዳት ወደ ተቋሙ በመሄድ አዲሱን ዋና ስራ አስፈጻሚ ጌታቸው ታደሰን ለማነጋገር መሞከሩን የገለጸ ሲሆን ወደ ተቋሙ እንዳይገባ መከልከሉን ጨምሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
ከሥራ ከተሰናበተ በኋላ በተቋሙ የሚገኙ 80 የሚሆኑ ሠራተኞች ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንዳላቸው የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን መግለጹን ተከትሎ “እኛ ብቻ አይደለንም” በሚል ሌሎችን ማጋለጥ እንደተጀመረ ጠቁሟል።
በ “ሪፎርሙ በተቋሙ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ አንጋፋ ባለሙያዎችን ወደታች በማውረድ የሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸውን በነዚ ሰዎች ተክቷል” የሚለው ወገን “ሚዲያው ወይ ለህዝብ ወይ ለመንግስት ሳይጠቅም መሀል ላይ ቀረ” ይላል።
የሠው ኃብት አሥተዳደሩ መዋቅር ሲሠራ፣ ሪፎርም፣ የደረጃ ዕድገት እና የትምህርት ዕድል ሲሰጥ ነገሮችን አስቀድሞ ማጣራት ቢኖርበትም እንደዛ ባለመደረጉ አሁን ያለበት ሁኔታ ላይ ደርሷል ሲል ወገን ለሚዲያችን ተናግሯል።
“በተቋሙ ውስጥም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያነሳና ቅሬታ የሚያቀርብ ካለ ከሥራ እንደሚባረሩ እንደተገለጸላቸውም” አክሏል።
የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የሰጠውን የሕግ ከለላ በመተላለፍ ከሥራ በመባበሩ ለዘጠኝ ዓመታት የሰራበትን የአገልግሎት ክፍያ ለመጠየቅ ለፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቁን የገለጸ ሲሆን፤ ክርክሩ ተጀምሮ ለየካቲት 12 ቀን 2016 ቀጠሮ ተሰጥቶ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
ተቋሙ “ለራሱ የሚሻለውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ”፤ ለእራሱ ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያና ካሳ እንዲሰጠው ጠይቋል። አዲስ ማለዳ በዚህ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ጌታቸው ታደሰ ጋር የደወለች ሲሆን “መልሳችሁ ደውልሉኝ” ቢሉም በድጋሚ የተደረገላቸውን ተደጋጋሚ ጥሪ ሳይመልሱ በመቅረታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።
በተመሳሳይም የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምላሽ አዲስ ማለዳለ ለማካተት ያደረገችው ሙከራ ባይሳካም በጉዳዩ ላይ ምላሽና መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑ ከወዲሁ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።


