አዲስ አበባ ውስጥ በተደረገ ክትትል ከ161 ማሳጅ ቤቶች 125ቱ መስፈርት ያላሟሉ ናቸው

0
2204

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በ2016 በጀት ዓመት ቁጥጥር ካደረገባቸው 161 ማሳጅ ቤቶች ውስጥ 36 የሚሆኑት ብቻ መስፈርቱን አሟልተው ተገኝተዋል ተባለ።

አዲስ ማለዳ ከባለስልጣኑ ባገኘችው መረጃ በአገር አቀፍ ደረጃ ‘CES 322 Compulsory Ethiopian standard’ የተባለ የማሳጅ ቤት መስፈርቶች የተቀመጠ ቢሆንም በማሳጅ አገልግሎት “ስም 24 ሰዓት አገልግሎት እንሰጣለን በሚል አፀያፊና ኢ- ሞራላዊ ድርጊት እየተፈጸመ ” ይገኛል።

የቤቱን ሁኔታ፣ የክፍሉን ስፋት፣ የመታሻውን አልጋ፣ የባለሙያውን የስልጠና ደረጃና የልብስ አለባበስ ሁኔታ፣ እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎች በዝርዝር የተገለጹበት መስፈርት ቢኖርም ቦታዎቹ ወሲባዊ ንግድ የሚፈጸምበት፣ የተለያዩ ሱሶች መጠቀሚያ ስለመሆናቸው ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን፤ የምግብና ጤና ነክ ቁጥጥር ዳይሬክተር ምሬሳ ምዴቅሳ “ተማሪዎችና አምራች ዜጋ የሆኑ ወጣቶች በማሳጅ ቤቶች ውስጥ ሲጋራና ሲሻ የሚያጨሱበት፣ ስነ ምግባራዊ ያልሆኑ ድርጊቶች የሚከናወኑበት እንዲሁም ወሲባዊ ድርጊቶች የሚፈጸሙበት በመሆኑ ሁሉም አካላት ትኩረት በመስጠት ድርጊቱን” እንዲያስወግድ አሳስበዋል።

የጉዳዩን አሳሳቢነት አስመልክቶ በተደረገ የውይይት መርሃ ግብር ላይ የአሻራ ዊልነስ ባለቤት ያሬድ ሲሳይ “በማሳጅ ቤት ሠራተኞችና በሴተኛ አዳሪዎች መካከል ያለው ምንም አይነት ልዩነት ያለ እስከማይመስል ድረስ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል” ማለታቸውን አዲስ ማለዳ ከባልስልጣኑ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ይህን ሁኔታ ለመለወጥ የማሳጅ ቤቶች ሲከፈቱ አማራጭ የህክምና መስጫ ብቻ እንደሆኑ እንዲታሰብ እና ባለቤቶቹም ይህን እንዲያምኑ ማድረግ፣ የስራ አካባቢው ለወሲብ እንዳይገፋፋ ማድረግ እንዲሁም በውስጡ የሚሠሩ ሠራተኞች በማሳጅ ሙያ የሰለጠኑ ብቻ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ማሳጅ ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ሳምሶን ሲሳይ ማህበራቸው ህዳር 2016 ላይ ህጋዊ እውቅና ማግኘቱን ገልጸው፤ ማህበሩ ሙያው እና ባለሞያዎች እንዲከበሩ የሚሰራ ነው ብለዋል።

የማሳጅ አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ አውጥተው በተግባር ግን አገልግሎቱን የማይሰጡትን ተቋማት በመለየት ከባለስልጣኑ እና ከሌሎች ህጋዊ አካላት ጋር በመተባበር ወደ ትክክለኛው አሠራር የሚገቡበትን መንገድ የማመቻቸት ሥራ ለመሥራት መታቀዱን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here